1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሳፋሪኮም እና ኢትዮ-ቴሌኮም የገበያ ፉክክር ማን ያተርፋል?

ረቡዕ፣ ነሐሴ 25 2014

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የኔትወርክ ሙከራ ሲጀምር በ07 የሚጀምረውን ሲም ካርድ የገዙ ደንበኞች፣ የኩባንያ ባለቤቶች እና የዘርፉ ባለሙያዎች ከኢትዮ-ቴሌኮም አገልግሎቶች ማመዛዘን ጀምረዋል። በ30 ብር ሲም ካርድ የገዙ የኢንተርኔት ፍጥነቱ የተሻለ መሆኑን ይናገራሉ። በሳፋሪኮም እና ኢትዮ-ቴሌኮም የገበያ ፉክክር ማን ምን አይነት ጥቅም ያገኛል?

https://p.dw.com/p/4GHej
Äthiopien Safaricom Dire Dawa
ምስል Messay Teklu/DW

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ በሳፋሪኮም እና ኢትዮ-ቴሌኮም የገበያ ፉክክር ማን ያተርፋል?

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራውን ከአዲስ አበባ ርቆ ሲጀምር የቪያብል ሶሉሽንስ ተባባሪ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኖህ ፈቃደ ወደ ድሬዳዋ አቀኑ። ኩባንያቸው ቪያብል ሶሉሽንስ ያዘጋጀው ኢፎን የተባለ መተግበሪያ የተለያዩ ኩባንያዎች የሚያቀርቡትን የቴሌኮም አገልግሎት በአንድ ላይ መጠቀም የሚያስችል  ነው። ደንበኞች በዚህ መተግበሪያ ስልክ መደዋወል፣ የጽሁፍ መልዕክት መለዋወጥን ጨምሮ በቴሌኮም አማካኝነት የሚቀርቡ የተለያዩ አገልግሎቶችን ማግኘት ይችላሉ። የቪያብል ሶሉሽንስ ዋና መሥሪያ ቤት በአዲስ አበባ ቢሆንም ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለፈው ሰኞ ባስጀመረው ኔትወርክ ኩባንያው ደንበኞች የኢፎን አገልግሎት መጠቀም እንዲችሉ ማድረጉን ኖህ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለፈው ሰኞ የደንበኞች የኔትወርክ ሙከራውን በድሬዳዋ ከተማ ሲጀምር ከአዲስ አበባ ከተጓዙት ኖህ በተጨማሪ እንደ አቶ በረከት መገርሳ ያሉ የከተማው ነዋሪዎች ሲም ካርድ ገዝተዋል። አቶ በረከት ወደ ሳፋሪኮም መደብር ብቅ ባሉበት ቅጽበት "ብዙ ህዝብ" በቦታው እንደነበረ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የሳፋሪኮም ሲምካርድ ገዝተው ሙከራውን የተቀላቀሉት አቶ በረከት "ኢንተርኔቱ ዋጋው [ከኢትዮ-ቴሌኮም] ትንሽ ይጨምራል። ነገር ግን በጣም ፈጣን ነው። ወደ የትኛውም ክልል ስትደውልበት ጥራቱም ቆንጆ ነው። ከሳፋሪኮም ወደ ኢትዮ-ቴሌኮም እንዲሁም ከኢትዮ-ቴሌኮም ወደ ሳፋሪኮም ይሰራል" ሲሉ ተናግረዋል። ከሰኞ ጀምሮ የኢትዮ-ቴሌኮም እና የሳፋሪኮም ደንበኛ የሆኑት አቶ በረከት "ሁለቱም በአንድ ቀፎ ውስጥ ናቸው። እንግዲህ ተስማምተው አሉ" ሲሉ ፈገግ እያሉ ተናግረዋል።

ሌላው የድሬዳዋ ነዋሪ አቶ ዳንኤል ታደሰ ወደ ሳፋሪኮም መደብር ብቅ ሲሉ "ከመጀመሪያዎቹ ገዢዎች ተርታ" ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢጠብቁም የገጠማቸው ግን የተለየ ነበር።  "ብዙ ሰው አዲስ ነገር ለማግኘት በጉጉት ተሰልፎ ነበር። ግፊያ ሁሉ ነበረው" የሚሉት አቶ ዳንኤል ሲም ካርድ በ30 ብር ገዝተው ሙከራውን ተቀላቅለዋል። "ሙከራ ላይ እንደመሆኑ አንዳንድ የሚያጋጥሙ የተወሰኑ መቆራረጦችን ማየት ችያለሁ። ከዚያ በተረፈ ግን የኢንተርኔት ፍጥነቱ እና የድምጽ ጥራቱ እንደ መጀመሪያ ቀንም አይደለም። ጥሩ ነበር" ብለዋል።  

Äthiopien Safaricom Dire Dawa
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለፈው ጥር ወር ገደማ አገልግሎት መስጠት ለመጀመር አቅዶ የነበረ ቢሆንም ሙከራው እስከ ነሐሴ ዘግይቷል።ምስል Messay Teklu/DW

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ለመሆን ከበቃው ሳፋሪኮም ቀዳሚ ደንበኞች መካከል የተቀላቀሉት ኖህ፣ ዳንኤል እና በረከት በገዟቸው ሲም ካርዶች "በሳፋሪኮም የሙከራ ኔትወርክ ዳታ መጠቀም፣ ጥሪዎች እና የጽሁፍ መልዕክቶችን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና ከኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ጋር መለዋወጥ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጥሪዎችን ማድረግ ይችላሉ።" ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በድሬደዋ ከተማ የጀመረው የደንበኞች የኔትወርክ እና አገልግሎቶች ሙከራ ሒደት በ2ጂ፣ 3ጂ እና 4ጂ ኔትወርኮች የሚከወን ነው። በ07 በሚጀምረው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መስመር የስልክ ቁጥሮቻቸውን መርጠው ሲም ካርድ መግዛት እንደሚችሉ ኩባንያው አስታውቋል።

ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2014 የተጀመረው "ሙከራ ኩባንያው በአገር አቀፍ ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት ከሚዘጋጅበት ጊዜ አስቀድሞ በተለያዩ ክልሎች እና ከተሞች የኔትወርክ የአገልግሎቱ ጥራቱን ሁኔታ የሚፈትሽበት ወቅት ነው።" ኩባንያው በአማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግሪኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎች በጥሪ ማዕከሉ በኩል የደንበኞች ድጋፍ አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጿል።

ለምን ድሬዳዋ?

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ባለፈው ጥር ወር ገደማ አገልግሎት መስጠት ለመጀመር አቅዶ የነበረ ቢሆንም ሙከራው እስከ ነሐሴ ዘግይቷል። በድሬዳዋ የተጀመረው ሙከራ እስከ ሚያዝያ 25 ቀን 2015 ድረስ በ25 ከተሞች ከመንግሥት፣ ከንግድ ድርጅቶች፣ ከየአካባቢው ማኅበረሰቦች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ኔትወርኩን ወደ ሥራ የማስገባት ሒደት አካል እንደሆነ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ገልጿል።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ አንዋር ሶሳ የድሬዳዋውን ሙከራ "በኔትወርኩ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ከማስጀመራችን በፊት የቴክኒክ እና ኮሜርሺያል ተግባራት ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ድረስ ዝግጁ መሆናቸውን ኔትወርኩን ለደንበኞች በመክፈት ሙከራ የምናካሒድበት ጠቃሚ ምዕራፍ ነው" ሲሉ ገልጸውታል። ኩባንያው ለምን ሙከራውን በድሬዳዋ እንደጀመረ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መግለጫ የሰጠው ማብራሪያ የለም። ዶይቼ ቬለ የኩባንያውን ኃላፊዎች ለመጠየቅ ያደረገው ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል።

Äthiopien Safaricom Dire Dawa
ምስል Messay Teklu/DW

ወደ ኢትዮጵያ ለሚያመሩ ኩባንያዎች በቴሌኮም እና በባንክ ጉዳዮች ላይ የማማከር አገልግሎት የሚሰጠው አስኪቤዝ ድርጅት መሥራች አቶ እስክንድር መስፍን "ያ አካባቢ በኮምዩንኬሽን እና በመረጃ ልውውጥ በጣም ያምናል። ኢንተርኔትን መሠረት ላደረጉ ቴክኖሎጂዎች በጣም ቅርብ ነው። በዚያ አካባቢ ከአዲስ አበባ እና ከሌላው በተለየ የሞባይል የባንክ አገልግሎት በጣም እየሰፋ ነው። በብዛት ከአጎራባች ሶማሊያ፣ ከአጎራባች ኬንያ ከጅቡቲ ጋ በቀላሉ መረጃ የመለዋወጥ ተፈጥሮ አላቸው። ስለዚህ እዚያ አካባቢ መጀመሩ ቢዝነሱን በቀላሉ ለማስኬድ ይጠቅመዋል ብዬ አስባለሁ" ሲሉ  ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ማማተሩ ሊጠቅመው እንደሚችል ያስረዳሉ። የኢንፎርሜሽን ኮምዩንኬሽን ቴክኖሎጂ አማካሪ የሆኑት አቶ እስክንድር ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገር አቀፍ ሙከራውን ከዋና ከተማዋ ርቆ በድሬደዋ መጀመሩ ሌላው ትኩረት እንዲስብ ሊያግዘው የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ የተባለው የአምስት ኩባንያዎች ጥምረት ወደ ኢትዮጵያ ገበያ የሚያስገባውን የቴሌኮም ጨረታ በ850 ሚሊዮን ዶላር ያሸነፈው ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት ግንቦት 14 ቀን 2013 ነበር። ይኸ ጥምረት ከኬንያ ሳፋሪኮም፣ ከደቡብ አፍሪካ ቮዳኮም፣ ከብሪታኒያ ቮዳፎን የተካተቱበት ነው። የብሪታኒያው ዓለም አቀፍ የመዋዕለ ንዋይ ተቋም (British International Investment) እና የጃፓኑ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን (Sumitomo Corporation) የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ አባላት ናቸው።

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ እና የኢትዮ-ቴሌኮም ውድድር

እንደ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ያሉ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች ባንኮችን የመሳሰሉ ከፍ ያለ ግልጋሎት የሚሹ ተቋማት እና ግለሰብ ደንበኞች ይኖሯቸዋል። በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ወደ ሥራ መግባት "ኢንተርፕራይዞች አገልግሎቶቻቸውን የሚያቀርቡበት የተሻለ አንድ መሠረተ-ልማት ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ" የሚሉት አቶ እስክንድር አምስት የቴሌኮም እና የመዋዕለ ንዋይ ተቋማትን ያጣመረው ዓለም አቀፍ ትብብር ያቋቋመው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ "ዓለም የደረሰበትን የመጨረሻውን ቴክኖሎጂ" ሥራ ላይ ማዋል እንደሚችል ጠቁመዋል።  

በገበያው ከሳፋሪኮም ውድድር የሚጠብቀው ኢትዮ-ቴሌኮም ባለፈው በጀት ዓመት 61 ቢሊዮን ብር እንዳገኘ አስታውቋል። ኩባንያው ከዓመት በፊት ገቢራዊ ባደረገው የቴሌ ብር አገልግሎት ወደ 22 ሚሊዮን ደንበኞች እንዳፈራ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወይዘሮ ፍሬሕይወት ታምሩ ተናግረው ነበር። ይኸው የቴሌ ብር አገልግሎት ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ዝውውር ተፈጽሞበታል። ሳፋሪኮም በኬንያ ከፍተኛ ስኬት ያገኘበትን በሞባይል የገንዘብ አገልግሎት በኢትዮጵያ ለመጀመር ፈቃድ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በኢትዮጵያን ላለፉት ለ128 ገደማ ዓመታት ነግሶ የቆየው ኢትዮ-ቴሌኮም እና አዲሱ ሳፋሪኮም ከሚያደርጉት ፉክክር አቶ ዳንኤል ታደሰ ብዙ የተሻለ አገልግሎት ይጠብቃሉ።

አቶ ዳንኤል ታደሰ "በሁለቱ መካከል በሚኖረው ውድድር እና መገፋፋት እኛ ጥሩ አማራጮች እና ብዙ ዓይነት አገልግሎቶችን እናገኛለን። አገልግሎቱንም ቶሎ የማግኘት ነገር ይኖራል" ሲሉ ተናግረዋል። አቶ በረከት በበኩላቸው ከውድድሩ የዋጋ ቅናሽ ይጠብቃሉ። ይኸ ግን ብቻ አይደለም። በኢትዮ ቴሌኮም እና በሳፋሪኮም መካከል የሚደረግ ውድድር በአቶ በረከት እምነት አገልግሎቱ ያልደረሳቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የቴሌኮም ተጠቃሚ የሚያደርግ ዕድል ሊፈጠር ይችላል። ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የአገሪቱ "የዲጂታል ሽግግር እና አካታች አጀንዳ ላይ አስተዋጽዖ ለማበርከት በቁርጠኝነት" የመስራት ውጥን አለው። እንዲህ አይነቱ አቋም እንደ ኖህ ላሉ የጀማሪ ኩባንያ መሥራቾች በበጎ የሚመለከቱት ነው።

የኢንፎርሜሽን ኮምዩንኬሽን አማካሪው አቶ እስክንድር ሳፋሪኮም የኢትዮጵያን ገበያ በቅጡ ማጥናቱን ይናገራሉ። የገበያ ጥናት እና የማስታወቂያ ሥራዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ልምድ እና ክህሎት ባላቸው ኩባንያዎች የሚያሰራው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለኢትዮ-ቴሌኮም ኃይለኛ ተገዳዳሪ ሊሆን እንደሚችል አቶ እስክንድር እምነታቸው ነው።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ