በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያውያን ስቃይ | ኢትዮጵያ | DW | 13.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

በሳውዲ አረቢያ የኢትዮጵያውያን ስቃይ

ሳዉድ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ዛሬም የድረሱልን ድምጻቸዉን እያሰሙ ነዉ። የሀገሪቱ መንግስት ላለፉት ወራት ሰጥቶ የቆየዉ የምህረት ቀነገደብ ካለፈ ወዲህ በዜጎችና የጸጥታ ኃይሎች ይፈጸምብናል የሚሉት በደልም ገደብ ማለፉን ይናገራሉ።

በሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ከ24ዓመታት በላይ እዚያ እንደኖሩ ለዶቼ ቬለ የገለጹት አንድ ዜጋ ደግሞ ኢትዮጵያዉያኑ ላይ ሀገሬ የሚያሳየዉ ጥላቻ ዛሬ አልተጀመረም ባይናቸዉ። ከያሉበት ታፍሰዉ በመጠለያ ስፍራ እንደተሰበሰቡ ያመለከቱ ወገኖች ደግሞ ኤምባሲዉ አልደረሰልንም፤ ካለንበት የሚያወጣን አጣን ይላሉ።

ከእነልጆቻቸዉ ታፍሰዉ መጠለያ ከተከተቱ እናቶች አንዷ ናቸዉ። እንባቸዉን እየታገሉ የሚሉት አንድ ነገር ነዉ፤ ድሃም ብትሆን ሀገር አለን። ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት በርካቶች በአዉቶብስ ያለ ሕጋዊ መኖሪያ ፈቃድ ሀገሪቱ ዉስጥ የተገኙትን የተለያዩ ሀገር ዜጎች በመሰብሰብ ወደመጠለያ ስፍራ ያጓጉዛሉ። በስልክ ያነጋገርኳቸዉ ኢትዮጵያዉያን የት ቦታ እንዳሉ ማወቅ እንደተሳናቸዉ ቢናገሩም ወንዶችና ሴቶችን ለየብቻ ተደርገዉ በመጠለያ መታጎራቸዉን ገልጸዉልኛል። ሴቶቹ ሶስት ሺህ እንሞላለን ባዮች ናቸዉ። ይህንም በአንድ አካባቢ ብቻ መሆኑ ነዉ። እዚህ ቦታ ካሉት አንዷ እሷ ብቻ ሳትሆን ሌሎችም በተሰባሰቡበት መጠለያ ስፍራ ባለዉ መጥፎ ሽታ ምክንያት ድምፃቸዉ መዘጋቱን ለበሽታም መዳረጋቸዉን ገልጻልኛለች። ወንዶች ትላለች ወጣቷ ከአረብ ወጣቶች ጋ ጸብ ዉስጥ ገብተዋል። እንደእሷ ገለጻም ሸባቦቹ ግራ የተጋቡትን ኢትዮጵያን ሴቶች ባገኙበት አስገድደዉ ይደፍራሉ፤ ከመጠለያዉም አፍነዉ ይወስዳሉ።

ወደሳዉዲ ከተሻገረ ብዙም ወራት እንዳልሆነዉ የገለፀልኝ ከስልጤ ነዉ የመጣሁት ያለኝ ሽፋ ሸምሱ ደግሞ ወደሀገሩ ለመመለስ ተዘጋጅቷል፤ ግን ወደአዉሮፕላን ማረፊያ ይወስዳችኋል የተባለዉን አዉቶብስ መጠበቅ ቀጥሏል የተባለዉ ግን የለም ይላል።

ሳዉዲ ዉስጥ ኢትዮጵያዉያን ብቻ ሳይሆን በርካታ የዉጭ ዜጎች በሠራተኝነት ይገኛሉ። መንግስት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸዉ በሰጠዉ የምህረት ጊዜ የተጠቀሙ የባንግላዴሽ፤ ፊሊፒንስ፤ ህንድ፤ ኔፓል፤ ፓኪስታንና የመን ዜጎች ቁጥር በርካታ መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ። እንደአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘገባ ከሆነም ወደአንድ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ተጠሪ የሚሆኗቸዉ ቀጣሪዎች አግኝተዋል። ዘጋቢዎች ያነጋገሯቸዉ ኢትዮጵያን ግን ለዓመታት ያፈሩትን ንብረት በርካሽ ለመሸጥ ተገደዋል ገሚሱንም ለሰዎች ሰጥተዋል። በእጅ የቋጠሯትን ገንዘብም መኖሪያ ፈቃድ ለማስተካከል በደላልነት ለቀረቧቸዉ የሳዉዲ ብልጣብልጦች አጉርሰዋል። ተስፋ ያደረጉትን ግን አላገኙም።

በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃዉያን ስደተኞች በሳዉዲ መንግስት ኃይሎች ታስሰዉ ቢያዙም የኃይል ጥቃቱ የበረታዉ ኢትዮጵያዉያኑ ላይ ነዉ ይላሉ እዚያ የሚገኙት ወገኖች።

ሳዉዲ የሚገኙ ወገኖች ዛሬም ኤምባሲዉ ላይ የሚያቀርቡት ቅሬታና ለመንግስትም የሚያቀርቡትን አቤቱታ በማስመልከት ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ያደረግነዉ ተደጋጋሚ ሙከራ ባለመሳካቱ የባለስልጣናቱን ሃሳብ ማካተት አልቻልንም።

ከሃገሪቱ መውጣት ያልቻሉ ዜጎች በዋና ከተማይቱ በሪያድና በሌሎችም ከተሞች በጎዳናዎች ላይ እየወጡ መንግሥት በአስቸኳይ ወደ ሃገራችው እንዲልካቸው ሲጠይቁ ከየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ጋር መጋጨታቸውን የጂዳው ወኪላችን ነብዩ ሲራክ ዘግቧል ።
በርካታ ኢትዮጵያውያን ዛሬም ሳውዲ አረቢያ ውስጥ በመሰቃየት ላይ መሆናቸውን እየተናገሩ ነው ። እነዚሁ ከሃገሪቱ መውጣት ያልቻሉ ዜጎች በዋና ከተማይቱ በሪያድና በሌሎችም ከተሞች በጎዳናዎች ላይ እየወጡ መንግሥት በአስቸኳይ ወደ ሃገራችው እንዲልካቸው ሲጠይቁ ከየአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ጋር መጋጨታቸውን የጂዳው ወኪላችን ነብዩ ሲራክ ዘግቧል ። ሳውዲ አረቢያ ውስጥ ያለህጋዊ የስራና የመኖሪያ ፈቃድ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ህጋዊ ሰነድ እንዲያወጡ አለያም ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ መንግሥት የሰጠው የምህረት ቀነ ገደብ ካበቃ ዛሬ 10ኛ ቀኑን ይዟል ። በነዚህ 10 ቀናት ውስጥ ወደ 23 ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ለሳውዲ መንግሥት እጃቸውን መስጠታቸው ተዘግቧል ። የጂዳውን ወኪላችንን ነበዩ ሲራክን ስለ አጠቃላዩ ሁኔታ በስልክ አነጋግሬዋለሁ ።

ሸዋዬ ለገሠ / ነበዩ ሲራክ
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic