በሳምንቱ መጨረሻ የተኪያሄዱ የስፖርት ክንውኖች | ስፖርት | DW | 08.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

በሳምንቱ መጨረሻ የተኪያሄዱ የስፖርት ክንውኖች

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ ቅዳሜ ዕለት የመጀመሪያውን ሽንፈት ቀምሷል። በጆሴ ሞሪንሆ የሚመራው ቸልሲን ጉድ ያደረገው በ7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኒውካስል ዩናይትድ ነው። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባየር ሙይንሽን እየመራ ነው፤ ዶርትሙንድ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ተደጋጋሚ ሽንፈት ለምን?

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት ዌስትሐም ዩናይትድ በ10 ተጨዋቾች የተወሰነው ስዋንሲን 3 ለ1፣ እንዲሁም አስቶን ቪላ ላይስተር ሲቲን 2 ለ1 አሸንፈዋል። ዌስትሐም ዩናይትድ የትናንቱን ጨዋታ ሲያሸንፍ ባሳለፈው ሣምንት ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በዚህም መሠረት ዌስትሐም በ15 ጨዋታዎች 27 ነጥቦችን በመሰብሰብ ከማንቸስተር ዩናይትድ ዝቅ ብሎ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ለመስፈር ችሏል።

በቅዳሜው ጨዋታ ከቸልሲ በተጨማሪ አርሰናልም በስቶክ ሲቲ 3 ለ 2 እጅ ሰጥቷል። ኩዊንስ ፓርክ በርንሌይን 2 ለዜሮ ሸኝቷል። ማንቸስተር ሲቲ ኤቨርተንን 1 ለባዶ አሸንፏል። ሊቨርፑል ከከሰንደርላንድ፣ ሁል ሲቲ ከዌስት ብሮሚች አልቢኖ እንዲሁም ቶትንሐም ሆትስፐር ከክሪስታል ፓላስ በተመሳሳይ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል።

የደረጃ ሠንጠረዡን ቸልሲ በ36 ነጥቦች እየመራ ነው። ማንቸስተር ሲቲ በሦስት ነጥብ ልዩነት ይከተላል። ዌስትሐም 27 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ማንቸስተር ዩናይትድ ከዌስትሐም ዩናይትድ በአንድ ነጥብ ዝቅ ብሎ በ25 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ነው። አሰናል በ23 ነጥብ ማንቸስተር ዩናይትድን ይከተላል። ሊቨርፑል 21 ነጥብ ይዞ 9ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው።

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን እና የባየር ሙይንሽን ግብ ጠባቂ ማኑኤል ኖየር

የጀርመን ብሔራዊ ቡድን እና የባየር ሙይንሽን ግብ ጠባቂ ማኑኤል ኖየር

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የትናንትና ጨዋታ ደግሞ አይንትራኅት ፍራንክፉርት ብሬመንን 5 ለ2 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ረትቷል። ሰሜን ጀርመን የሚገኘው ሐምቡርግ ማይንትስ 2 ለ1 አሸንፏል። ከትናንት በስትያ ሻልካ ሽቱትጋርትን በሰፊ የግብ ልዩነት 4 ለዜሮ ጸጥ አሰኝቷል። ዎፍስቡርግ ከማን አንሼ በሚል ሐኖቨርን 3 ለ 1 ሸኝቷል። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ እና ሔርታ ቤርሊን በጠባብ ልዩነት 3 ለ2 ተለያይተዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ከባድ ተገዳዳሪ ቡድን የገጠመው ኃያሉ ባየር ሙይንሽን በኹለተኛው አጋማሽ እንደምንም ባየር ሌቨርኩሰንን በጠባብ የግብ ልዩነት አንድ ለባዶ ማሸነፍ ችሏል። የባየር ሙይንሽኑ አማካይ ተጨዋች፣ ኔዘርላንዳዊው አሪየን ሮበን የቅዳሜው ጨዋታ ከባድ እንደነበር ገልጧል።

«ዛሬ የተጫወትነው በጣም ጥሩ ከሆነ ተጋጣሚ ጋር ነበር። ጠንካራ ጨዋታ ነው ያከናወኑት። ጨዋታው ከባድ ስለነበር በ1 ለዜሮው ውጤት መደሰት ያስፈልጋል።»

የባየር ሌቨርኩሰኑ አምበል ሲሞን ሮልፍስ በበኩሉ ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረውን ጥንካሬ ሳይጠቀምበት በመቅረቱ መቆጨቱን ጠቅሷል።

የባየር ሙይንሽን እና የማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾች

የባየር ሙይንሽን እና የማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾች

«በረዥም ቅብብል ጥሩ ተጫውተናል ብዬ አስባለሁ። መልካም አጋጣሚዎችንም ፈጥረን ነበር። በእንዲህ አይነቱ ጨዋታ ብዙም ዕድል አለመኖሩ ግልፅ ስለሆነ፤ በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኘናቸውን ዕድሎች መጠቀም ነበረብን። የሚያሳዝነው የመጀመሪያው አጋማሽ እንደተጀመረ 1 ለዜሮ መመራታችን ነው። ከዚያ በኋላ ወደ ቀድሞው ጥንካሬያችን መመለስ አልቻልንም።»

አውስቡርግ ኮሎኝን 2 ለ1 ሲያሸንፍ፤ ፍራይቡርግ ፓዴርቦርን አንድ እኩል ተለያይተዋል። ሰሞኑን ተደጋጋሚ ሽንፈትን ሲያስተናግድ የከረመው እና ወራጅ ቃጣና ውስጥ ለመቆየት የተገደደው ቦሩስያ ዶርትሙንድ፥ በለስ ቀንቶት፥ በጠበበ ልዩነትም ቢሆን ዓርብ ዕለት ሆፈንሐይምን 1 ለዜሮ ለማሸነፍ ችሏል። በዚህም መሠረት ዶርትሙንድ ከስጋት ቃጣናው ለጊዜውም ቢሆን ወጥቶ 14ኛ ደረጃ ላይ ለመስፈር ችሏል። ነጥቡ እንደደረጃው 14 ነው። ባየር ሙይንሽን በ36 ነጥብ አሁንም መሪነቱን እንዳስጠበቀ ነው። ዎልፍስቡርግ በ29 ነጥብ ይከተለዋል። አውስቡርግ 24 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባየር ሌቨርኩሰን እና ሻልካ እኩል 23 ነጥብ ይዘው፥ ሆኖም በግብ ልዩነት በተከታታይ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ቬርደር ብሬመን እና ሽቱትጋርት በ17ኛ እና 18ኛነት የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ላይ ተቃቅፈዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድንን በተመለከተ ወዳደረግነው ቃለምልልስ እንለፍ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሠጣኝ ሰውነት ቢሻው እና የስፖርት ጋዜጣ አዘጋጅ ነው ያነጋገርነው በመጀመሪያ የሀትሪክ ጋዜጣ ባለቤት እና ዋና አዘጋጅ ኢሳቅ ከአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዎች ከምድቡ የመጨረሻ ሆኖ ከተሰናበተው ቡድን ምን ትምህርት ሊወሰድ ይችላል የሚል ጥያቄ ነበር ያቀረብኩለት።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች በደቡብ አፍሪቃ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን ደጋፊዎች በደቡብ አፍሪቃ

ብሔራዊ ቡድኑን ለተደጋጋሚ ድል አብቅተው የነቡት የቀድሞው አሠልጣን አቶ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው የቀድሞውን ቡድን እንደ ብነት በመጥቀስ ወደፊት ምን መሠራት እንዳለበት በዚህ መልኩ ይገልጣሉ።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አሠልጣኝ ማሪዮ ባሬቶን ወደ ኢትዮጵያ ሲያስመጣ አሠልጣኙ በቀዳሚነት የተሰጣቸው ግብ ቡድኑን ለአፍሪቃ ዋንጫ ጨዋታ ማቅረብ ነበር። ይክ አለመሳካቱ ይታወቃል። እናስ የአሠልጣኙ የወደፊት ዕጣ ምን ይመስላል? ወደ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ደውለን ለማጣራት ሞክረን ነበር። የአሠልጣኙን ጉዳዩ በተመለከተ በሣምንቱ መጨረሻ ላይ ውሳኔ ስለሚሰጥ መልሰን እንድንደውል ነግረውናል። ሣምንት የሚመከታቸውን የፌዴሬሽን ባለሥልጣናት ለማናገር እንሞክራለን።

የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በነገው ዕለት ይካሄዳሉ። ሊቨርፑል ከባዝል፣ ሪያል ማድሪድ ሉዶጎሬትስ ራዝጋርድ፣ አርሰናል ከጋላታሳራይ እንዲሁም ባየር ሌቨርኩሰን ከቤኔፊካ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

በስፔን ላሊጋ ትናንት ባርሴሎና ኤስፓኞልን 5 ለ1 በሆነ ሰፊ ልዩነት ረትቷል። በዚህም መሠረት ሪያል ማድሪድ የደረጃ ሠንጠረዡን በ36 ነጥብ እየመራ ይገኛል። ባርሴሎና በ34 ነጥብ ይከተላል። አትሌቲኮ ማድሪድ 32 ነጥብ ይዞ ሦስተና ደረጃ ላይ ይገኛል።

በመካከለኛ ክብደት የቡጢ ፍልሚያ ዮርገን ብሬህመር ትናንት ባደረገው ፍልሚያ ቀበቶውን ለማስጠበቅ ችሏል። ዮርገን ለዓለም ቡጢ ማኅበር ውድድር ባደረገው ጨዋታ ፓወል ግላሲቭስኪን በ43 ሠከንድ በዝረራ ለማሸነፍ ችሏል። የትናንቱ ድል ለ36 ዓመቱ ቡጢኛ ከ47 ፍልሚያዎች 45ኛው ድል ሆኖ ተመዝግቦለታል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic