በሳህል የጀርመን አሸባሪነትን የመከላከል ጥረት  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 25.05.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

በሳህል የጀርመን አሸባሪነትን የመከላከል ጥረት 

ጀርመን በሳህል የጀመረችውን ጥረት መቀጠል እንጂ ማቋረጥ አትፈልግም።የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት፣ ባለፈው ረቡዕ የጀርመን መከላከያ ሠራዊት የማሊ ተልዕኮን ለተጨማሪ አንድ ዓመት አራዝሟል።የአውሮጳ ኅብረት የማሊ ስልጠና ተልዕኮ EUTMም በማሊ የሚሰማራውን ወታደሮቹን ቁጥር ከከዚህ ቀደሙ 450 አሁን ወደ 600 ከፍ ማድረግ ይችላል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:51

በሳህል አካባቢ ሃገራት የጀርመን ፖለቲካ መርህ

ጀርመን በሳህል አካባቢ ሃገራት አሸባሪዎችን የመከላከል ዓላማ ይዞ በሚንቀሳቀሰው የአውሮጳ ህብረት የሳህል ሃገራት ተልዕኮና፣ በተ.መ የማሊ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ውስጥ ትሳተፋለች።የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት የጀርመን ጦር የማሊ ተልዕኮን በአንድ ዓመት አራዝሟል።ይሁንና በሳህል አካባቢ ሃገራት አሸባሪነትን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ለአካባቢው ፀጥታ ያደረገው አስተዋጽኦ አናሳ መሆን እያነጋገረ ነው። ጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 18  ቀን 2020 ዓም ለጀርመን የሳህል ፖለቲካ መጥፎ ቀን ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።በዚያን እለት ነበር በምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሃገር ማሊ ለሳምንታት ከተካሄደ የጎዳና ተቃውሞ በኋላ በማሊው ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ቡባከር ኬይታ ላይ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደው።ጀርመን ይህን መሰሉን ፖለቲካዊ ቀውስ ማስቀረት ትፈልጋለች።ለዚህም ነው የማሊን ወታደሮች ለማዘመን ፣ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ በሚካሄደው የአውሮጳ ኅብረት የማሊ የስልጠና ተልዕኮ በእንግሊዘኛው ምህጻር EUTMም የጀርመን  ጦር  የሚሳተፈው  ።እስካሁን በዚህ ተልዕኮ ከ13 ሺህ በላይ የጀርመን ወታደሮች ተካፍለዋል።ከዚህ ሌላ የጀርመን ጦር ማሊን ለማረጋጋት በተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮም ይሳተፋል።በእንግሊዘኛው ምህጻር MINUSMA ሚኑስማ በመባል የሚጠራው ይህ ተልዕኮ ከተመሰረተ 8 ዓመታት አልፎታል።ዓላማው የሃገሪቱን ፖለቲካዊ ሂደቶች መደገፍና ከጸጥታ ማስከበር ስራ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ተግባራትንም መከናወን ነው።ከዛሬ 7 ዓመት ወዲህ ደግሞ ተልዕኮው በማሊ ፀጥታን የማስፈን ሃገሪቱን የማረጋጋት፣ለሲብሎች ጥበቃ የማድረግ፣ ብሄሔራዊ መግባባትና እርቅን የመደገፍና፣ የፀጥታ ኃይሉን መልሶ የማቋቋም ተጨማሪ ሃላፊነቶች ተሰጥተውታል።ታገስሽፒግል የተባለው የጀርመን እለታዊ ጋዜጣ እንደዘገበው ጀርመን ለአምስቱ የሳህል አካባቢ ሃገራት ማለትም ለሞሪቴንያ ለማሊ ለኒዠር ለቡርኪናፋሶና  ለቻድ ከጎርጎሮሳዊው 2016 እስከ 2020 ዓም ሲቭሎችን  ለማረጋጋት የሚውል 3.2 ቢሊዮን ዩሮ አውጥታለች።ለመሆኑ ጀርመን ለሳህል ሃገራት ይህን ሁሉ ድጋፍ የምታደርግበት ምክንያት ምን ይሆን?ዶቼቬለ ስለጉዳዩ የጠየቃቸው በአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ምክር ቤት የሳህል አካባቢ ሃገራት ጉዳይ አዋቂ እንድሪው ሌቦቪች ምክንያቱን ያስረዳሉ።

«የጀርመን መንግሥት በውጭ የፖለቲካ መርሁ ሳህል ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠው አካባቢ አድርጎ ነው የሚያየው።ከፈረንሳይ ጋር ላለው አጋርነት እንዲሁም በአውሮጳ ኅብረት ውስጥ በሚጫወተው ሚናም  የሚያስቀድመው ጉዳይ ነው።እንደሚመስለኝ እነዚህ ሁለ በጣም አስፈላጊ ናቸው። በአጠቃላይ የጀርመን መንግሥት አሁን በማሊ በሲቭሎች አማካይነት የሚካሄዱትን አንዳንድ ጥረቶች፣ ሊያከናውን ቆርጦ ለተነሳባቸው ተግባራት ወሳኝ ጥረቶች አድርጎ ነው የሚያያቸው። ሆኖም አንዳንድ ጊዜያት ስለተልዕኮዎቹ፣ ስለውጤታማነታቸው ፣መቀጠል አለባቸው የለባቸውም የሚሉ ጥያቄዎችም በርግጠኝነት ይነሳሉ።»

ሆኖም ይህ እስካሁን ለአካባቢው ጸጥታ ያደረገው አስተዋጽኦ ጥቂት ብቻ ነው። ከዛሬ 4 ዓመት ወዲህ በአካባቢው አክራሪ ሙስሊም በመባል የሚጠሩ ቡድኖች የሚፈጽሙት ጥቃት በሰባት እጥፍ አድጓል።የተመድ እንደሚለው ከ29 ሚሊዮን በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።ይህ ደግሞ ከእስከዛሬው እጅግ ከፍተኛው ነው።ያም ሆኖ ጀርመን በሳህል የጀመረችውን ጥረት መቀጠል እንጂ ማቋረጥ አትፈልግም።የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት፣ ባለፈው ረቡዕ የጀርመን መከላከያ ሠራዊት የማሊ ተልዕኮን ለተጨማሪ አንድ ዓመት አራዝሟል።የአውሮጳ ኅብረት የማሊ ስልጠና ተልዕኮ EUTMም በማሊ የሚሰማራውን ወታደሮቹን ቁጥር ከከዚህ ቀደሙ 450 አሁን ወደ 600 ከፍ ማድረግ ይችላል።ይሁንና ለአካባቢው ችግር ወታደራዊ ድጋፍ መፍትሄ ይሆናል አይሆንም የሚለው ጥያቄ አሁንም የሚነሳ ነው። የበርሊን ፖለቲካ ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን ከዚህ ውጭ ሌላ አማራጭ ያየ ወይም ያገኘ አይመስልም። ባለፈው ረቡዕ በጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በተካሄደው ክርክር ላይ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት ፓርቲ አባል ጆአን ዴቪድ ዋደፑል በሰጡት አስተያየት የሳህል አካባቢ የአውሮጳ ትልቁ የፀጥታ ስጋት እንደሆነ ተናግረዋል።

«ለኛ አውሮጳ ላለነው በሳህል አካባቢ ያለው ሁኔታ አሁን ካሉት የፀጥታ ፖለቲካ ተግዳሮቶች ግዙፉ ነው።የሳህል ጸጥታ ለኛ ለአውሮጳውያን ትልቅ ጉዳይ ነው።ይህ የመላ አካባቢውን አመረጋጋት የሚመለከት ነው። ሳህል  ለአሸባሪዎችና ለወንጀለኛ ቡድኖች ከተተወ የሰብዓዊው ቀውስ ስጋት አለ።በመጨረሻም ጉዳዩ የአውሮጳ ዋነኛ ፍላጎት ነው፤የጸጥታችን ጉዳይ።»

ያም ሆኖ ይህ ቀውስ በወታደራዊ መንገድ ይፈታ ይሆን የሚለው አሁንም ማጠያየቁ ቀጥሏል።የጉዳዩ አዋቂዎች፣ አውሮጳውያን እስካሁን ልዩ ትኩረት የሰጡት ጽንፈኛ ቡድኖችን መዋጋቱ ላይ ብቻ በመሆኑ ማሊን የመሳሰሉ ሃገራት ለተለያዩ የሃገር ውስጥ ግጭቶች ተዳርገዋል ሲሉ ይተቻሉ።በነርሱ አስተያየት በተፈጥሮ ሃብት ምክንያት የሚነሱ ግጭቶች ትኩረት ተነፍጓቸዋል።በመሬት ጥበትና በውኃ እጥረት ሰበብ እንዲሁም በተለያዩ ጎሳዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ተረስተዋል ይላሉ።ይህን ከሚሉት አንዱ በጀርመን የሳይንስና የፖለቲካ ተቋም የሳህል ጉዳይ አዋቂ ዴኒስ ቱል ናቸው ።

«አሸባሪ የሚባሉትን ቡድኖች መዋጋት ፀጥታን ወይም መረጋጋትን አያመጣም።ምክንያቱም በርካታ ግጭት ቀስቃሾችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፈጻሚዎች አሉ።ስለዚህ እኔ እንደሚመስለኝ ይህን መሰሉ ሃሳብ ወይም ጉዳይ ለውጥ ሊደረግበት ወይም ሊታሰብበት ይገባል።ፀጥታ ማስከበር ብቻ የችግሩ መፍትሄ  አይደለም።ምናልባትም በማሊ የረዥም ጊዜ ልምድ በሆነው በሀገር ውስጥ ደረጃ ፖለቲካዊ ስምምነቶችን ማምጣትም ችግሩን ለመፍታት ሊያግዝ ይችላል።»

ይህ በትክክል የሳህል አካባቢ ችግር ነው ይላል የዶቼቬለው ዳንኤል ፔልስ ።ማሊን እንደ ምሳሌ እንውሰድ የሚለው ፔልስ በጎርጎሮሳዊው 2015 የያኔው የቀድሞ የማሊ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም አቡበከር ኬይታ ከአንዳንድ  ታጣቂ ቡድኖች ጋር የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውን ስምምነቱ ግን ተግባራዊ እንዳልሆነ አስታውሷል።ባለፈው ዓመት ደግሞ  የቡርኪናፋሶ የሲቪክ ማኅበራት ፍላጎት የነበረ ቢሆንም፣የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ሮሽ ካባሬ ከአማጺ ቡድኖች ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።በዚህ የተነሳም የጀርመን ተቃዋሚ ፖለቲከኞች መንግሥታቱ ላይ ግፊት እንዲደረግ ጥሪ እያስተላለፉ ነው።ከጀርመን የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ የፓርላማ አባል አገኒስዝካ ቡርገር፣ የሰላም ሂደቶች የሚሳኩት በአካባቢው ፖለቲካው የተዋቀረበት ሁኔታም ትክክለኛ ሲሆን ብቻ እንደሆነ፣ በረቡዕ የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ክርክር ላይ አስረድተው ነበር።

«የሰላም ሂደቶች እና ከርሱም ጋር የተያያዙት ዓለም አቀፍ ጥረቶች የልማት ትብብሮችም ሆነ የፀጥታ ኅይላት ተሃድሶ፤ ሁሉም ሊያሳኩ የሚችሉት ለፖለቲካው ማዕቀፍ የሚያስፈልጉ ሁኔታዎች ትክክል ሲሆኑ ብቻ ነው።በዚህ የተነሳም የጀርመን ፌደራል መንግሥት የቀድሞዎቹን ስህተቶች መድገም የሌለበት።ያም ማለት የሰብዓዊ መብቶችን ጉዳይ በግልጽ ማስቀመጥና፣በወታደሩ ላይም ዓለም አቀፉን ጫና አጠናክሮ መቀጠል ይገባል፣መንግሥትም በስተመጨረሻ እውነተኛ ፖለቲካዊ ለውጦችን እውን እንዲያደርግ ግፊት ማድረግ ያስፈልጋል።»

የጀርመን ፌደራል መንግሥትም ቡድን አምስት በመባል የሚታወቁት የሳህል አካባቢ ሃገራት ሞሪቴንያ ማሊ ኒዠር ቡርኪናፋሶና ቻድ ከአሁኑ የበለጠ ሃላፊነት የሚሰማቸው እንዲሆኑ ይፈልጋል።ይህ ደግሞ በብድን አምስት መንግሥታት ላይ የተጣለ ነው። ባለፈው የካቲት በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሳህል ሃገራት ጉባኤ ላይ የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀይኮ ማስ መንግሥታቱ ሥራቸውን በሃላፊነት ከመወጣት ጋር ሙስናንና ሰዎች ተጠያቂ አለማድረግን  እንዲከላከሉ አሳስበዋል።ሆኖም የሳህል አካባቢ ህዝቦች በዚህ ረገድ አንድም ለውጥ አላዩም።በሁለት ሃገራት ማለትም በማሊና በቻድ ወታደሩ ሥልጣኑን ቀምቷል።በቀሪዎቹ ሃገራት ደግሞ ህዝቡ በፀጥታ አስከባሪ ኃይላት ጭካኔ ተማሯል።እነዚህ ችግሮች መፍትሄ እስካላገኙ ድረስ በሃገራቱ ፣ህዝቡ በመንግስት ላይ የሚኖረው አመኔታ እየተሸረሸረ መሄዱ አይቀርም።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች