በሱማሊያ የባለስልጣናቱ ሽኩቻ | አፍሪቃ | DW | 19.11.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በሱማሊያ የባለስልጣናቱ ሽኩቻ

በሱማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሳን ሼይክ ሞሐሙድ እና በጠቅላይ ሚንስትር አብዲዋይል ሼይክ አኽመድ መካከል የተፈጠረው ውዝግብ መባባሱ ተነግሯል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ያቀረቡትን የሚንስትሮች ምክር ቤት መዋቅር ፕሬዚዳንቱ እንዳልተቀበሉት ተገልጿል።

እጎአ በ1991 ዓም የያኔው የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ ዚያድ ባሬ ሀገሪቱን ጥለው ከኮበለሉበት ጊዜ አንስቶ ሶማሊያ የሰከነ አስተዳደር በዘላቂነት መመስረት ተስኗታል። በሶማሊያ የሚመሰረት መንግስት በተደጋጋሚ የባለስልጣናት ሽኩቻ የሚስተዋልበት ነው። ሰሞኑን የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲዋይል ሼይክ አኽመድ የሚንስትሮች ምክር ቤት ላይ ለውጥ በማድረጋቸው ከሱማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሳን ሼይክ ሞሐሙድ ጋር መወዛገባቸው ተጠቅሷል። በኹለቱ ባለስልጣናት መካከል የተፈጠረው ውዝግብ መባባሱም ተነግሯል። በሱማሊያ የዶቸቬለ ዘጋቢ መሀመድ ዑመር ሑሴን

«ሶማሊያ ውስጥ የሽግግር መንግስቱ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ በፕሬዚዳንት እና ጠቅላይ ሚንስትር መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች ተስተውለዋል። ይኽ ያሁኑ ግጭት የእዛ አንድ አካል ነው።»

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲዋይል ሼይክ አኽመድ

የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲዋይል ሼይክ አኽመድ

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለፕሬዚዳንቱ ቅርብ የሆኑትን ሰው ከስልጣናቸው ማንሳታቸውን ፕሬዚዳንቱ እንዳልተቀበሉት፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ በበኩላቸው ያን የማድረግ ሥልጣን የእሳቸው መሆኑን በመጥቀሳቸው ውዝግቡ በዋናነት እንደተቀሰቀሰ መሀመድ ዑመር ሑሴን ጠቅሷል።

የአሁኑ ግጭት የተከሰተው ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚንስትሮች ምክር ቤትን እንደ አዲስ በማዋቀራቸው ነው። በመዋቅሩ ደግሞ የፕሬዚዳንት ሐሳን ሼይክ ሞሐሙድ ወዳጅ የሆኑት የፍትኅ እና የእኩልነት ሚንስትሩ አብዱልቃድር ሼይክ ከስልጣናቸው እንደሚነሱ ይጠቅሳል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ሶማሊያን መልሶ ለመገንባት ለማድረገው ጥረት ደስተኞች ካልሆናችሁ ስልጣኔን ልለቅ እችላለሁ ሲሉ የሚንስትሮች ምክር ቤት ላይ መዛታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። የሶማሊያ ድረ-ገፆች ሰኞ ዕለት እንደዘገቡት ከሆነ ደግሞ 14 የሚንስትሮች ምክር ቤት አባላት ጠቅላይ ሚንስትር አብዲዋይል ሼይክ አኽመድ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ የሚጠይቅ ደብዳቤ ማስገባታቸው ተገልጿል።

የሶማሊያ ወታደር መዲና ሞቃዲሾ ውስጥ ሲዘዋወር

የሶማሊያ ወታደር መዲና ሞቃዲሾ ውስጥ ሲዘዋወር

በሌላ ዜና በተመድ የሶማሊያ ልዩ ልዑክ ኒኮላስ ኬይ ከምዕራባውያን የአምባሳደሮች ልዑካን ጋር በመሆን የሶማሊያ ጠቅላይ ሚንስትር እና ፕሬዚዳንቱን ለማነጋገር መጣራቸው ተገልጧል። ልዑካኑ «በሶማሊያ የተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስጥ ሌላ ነገር ለማስከተል የሚችል ከባድ አደጋ ነው» ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic