በሰ/ኬንያ በተደጋጋሚ የሚደርሰዉ ጥቃት | አፍሪቃ | DW | 24.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በሰ/ኬንያ በተደጋጋሚ የሚደርሰዉ ጥቃት

ባለፈዉ ሳምንት መጨረሻ በኬንያ በተከሰተ የጎሳ ግጭት ቢያንስ 16 ተገደሉ ወደ 20 የሚሆኑ ሰዎች ደሞ ቆሰሉ። በሰሜናዊ ኬንያ ማንዴራ በተሰኘዉ መንደር በሚገኝ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣብያ የተቀሰቀሰዉ ይህ የጎሳ ግጭት፤ በሶማልያ ጎሳዎች መካከል እንደሆነም ታዉቋል።

ትናንት እሁድ በሶማሊያና በኢትዮጵያ ድንበር አጠገብ በሚገኘዉ በኬንያ ሰሜን-ምሥራቃዊ ዳርቻ ባለ የተፈናቃዮች መጠለያ መንደር በደረሰ የቦንብ ጥቃት ቢያንስ 16 ሰዎች ተገድለዋል። ፖሊስ እንዳስታወቀዉ ጥቃቱ የተፈፀመዉ የጋሪ እና የዴጎዲያ ጎሳ ለወራት የዘለቀ ግጭት ባደረጉበት ቦታ ሲሆን ይህ የጎሳ ግጭት ዋጂር ጎሳ በሚገኝበት ወደ አጎራባች ክልልም ተዛምቶአል።  በጥቃቱ የተገደሉት የዉስጥ ተፈናቃዮች እንደሆኑም የኬንያ ፖሊስን ጠቅሶ የፈረንሳዩ የዜና ወኪል አዣንስ ፍራንስ ፕሪስ ዘግቦአል።  በሰሜናዊ ኬንያ የሚገኙ የተለያዩ የጎሳ አባሎች በአካባቢዉ የሚገኘዉን የግጦሽ ሳር በየግል ለመጠቀም በማሰብ በተደጋጋሚ ሲጋጩ ረጅም ግዜያትን አስቆጥረዋል። ባለፉት ቀናት የተቀሰቀሰ ሌላ ግጭት ከሃያ ለሚበልጡ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ህይወት መጥፋት ሰበብ ሆንዋል፤ ለግጦሽ ሳር የሚጋጩት የጎሳ አባላት ሁኔታንም ዳግም ለከባድ ዉጥረት ማጋለጡ ነዉ የሚገለፀዉ። አካባቢዉ ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞች የየጎሳዉ ሚሊሽያዎች በአካባቢዉ አስተዳደር ላይ የበላይ እንዲሆኑ በመገፋፋት ብቀላ እንዲፈጸም ይጥራሉ ሲሉ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ይከሳሉ።  በኬንያ የራድዮ ሶማልያ  ጋዜጠኛ ኬንያዊዉ አብዱሰላም አትመን ስለግጭቱ እንዲህ ይላል፤
«የዋጅራ ወረዳ በሆነዉ በማንዴራ ነዉ ግጭቱ የተቀሰቀሰዉ። በሁለቱ ከተሞች መካከል የጋራ የሆነ ድንበር ይገኛል። በማንዴራ ክልል  ጋርሌ እና ዴጎድያ የተሰኙ ሁለት ጎሳዎች ይገኛሉ። ጋርሌ ጎሳ ዴጎድያን ከቦታዉ ማስለቀቅ ይፈልጋል በሚል ነዉ፤ በሁለቱ ጎሳዎች ዘንድ ግጭቱ የተባባሰዉ።»
 ከመዲና ናይሮቢ 800 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኘዉን የማንዴራ አካባቢ ያጠቁት ታጣቂዎች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር በኩል መሸሻቸችዉና፤ ክትትል እየተደረገባቸዉ መሆኑን  የማንዴራ መንደር ተጠሪ ሚሻኤል ታይላል አስታዉቀዋል።  የኬንያ የቀይ መስቀል ድርጅት እንደገለጸዉ 15 ሰዎች በእጅ ቦንብ ጥቃት ተገድለዋል፤ ሰባት ግልሰቦች ደግሞ በጽኑ ቆስለዋል። የኬኒያ ዋና የፖሊስ አዛዥ ዴቪድ ኪማዮ ዉጥረቱ የሚታይበት  የማንዲራን መንደር እና የአጎራባችዋን የዋጂር ተጠሪዎችን ፧ካነጋገሩ በኋላ  ጥቃቱ ፖለቲካዊ መንስኤ እንዳለዉ መናገራቸዉን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግቦአል። የኬንያ መንግስት ባለፉት ሳምንታት ልዩ የጸጥታ ኃይል ወደዚሁ ቦታ መላኩ ተነግሮአል። የጎሳ ግጭት በተቀሰቀሰበት በዚህ አካባቢ ምንም አይነት  የፀጥታ አስከባሪ ፖሊስ፤ ባለመኖሩ የመንደሩ ነዋሪዎች በተጠንቀቅ ፀጥታ የሚያስጠብቁላቸዉ የታጠቁ ቡድኖች እንዳሏቸዉና፤  አርብቶ አደሩ በግጦሽ ግዜ  ከብቱ እንዳይዘረፍ በግልጽ መሳሪያ ይዞ ሲንቀሳቀስ እንደሚታይ  ተጠቅሶአል። ኬንያዊዉ ጋዜጠኛ አብዱሰላም አትመን እንደሚለዉ ግጭቱ በሁለቱ ጎሳዎች በመሆኑ ለአጎራባች አገሮች የሚያሰጋዉ ነገር የለም።
«እንደኔ እምነት በሁለት ጎሳዎች መካከል ያለ ግጭት ነዉ፤ ሁለቱም ጎሳዎች አንዱ አንዱን እየወነጀለ ነዉ። ጎሳዎቹም በኬኒያ የማንዴራ አካባቢ ተወላጆች ናቸዉ።»


የኬንያ መንግሥት በማንዴራ አውራጃ ሰላምን ለማስፈን የፖሊስ ሃይሉን ሲያጠናክር ወታድሮችንም በቦታው እንደሚያሰፍር ማስታወቁ አይዘነጋም። በአካባቢው ባለፉት ወራት በርካታ የቦምብ ጥቃቶች ሲደርሱ በተለይም ፖሊሶች የታጣቂዎች የጥቃት ዒላማ ሆነው ቆይተዋል። ለጥቃቱ ሃላፊነት የወሰደ ወገን ባለመኖሩም የኬንያ መንግሥት ቀደም ሲል የሶማሊያን እስላም አክራሪ ቡድን አሸባብን ተጠያቂ ማድረጉ የሚታወቅ ነው።  ሶማልያ አዋሳኝ ላይ በሚገኘዉ የሰሜናዊ ኬንያ አካባቢ የተኩስና የጓዳ ሰራሽ ፈንጂ ጥቃት፣ ኬንያ ወታደሮቿን ወደሶማሊያ ከላከችበት ከጎርጎሮሳዊዉ 2011ዓ,ም ወዲህ በተደጋጋሚ ታይቶአል። 

አዜብ ታደሰ

ሸዋዪ ለገሰ 

Audios and videos on the topic