በሰው መነገድ | ኤኮኖሚ | DW | 07.10.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

በሰው መነገድ

በዛሬው ዘመን የተደራጁ ወንጀለኞች ሰውን እንደ እቃ የሚነግዱበት አድራጎት ልክ እንደ ጦርመሣሪያ ወይም እንደ አብሾ እጽ ወፍራም ትርፍ ነው የሚያመነጨው። በመላው ዓለም ውስጥ የሚንቀሳቀሱት የኮንትሮባንድ ወንጀለኛ ቡድኖች ብዙ ገንዘብ በማስከፈል ሰውን በድብቅ መንገድ እየጫኑ ከአንዱ የዓለም አካባቢ ወደሌላው የሚያዘዋውሩበት አድራጎታቸው በያመቱ ከ ፳ እስከ ፴ ሚሊያርድ ዶላር እንደሚያስገኝላቸው ነው የሚገመተው።

በኢጣሊያ ደሴት ላምፔዱዛ የተኮለኮሉ ሕገወጥ ፈላስያን

በኢጣሊያ ደሴት ላምፔዱዛ የተኮለኮሉ ሕገወጥ ፈላስያን

ግን ይኸው በሰው የሚደረገው የኮንትሮባንዱ ንግድ በአንድ በኩል ለወንጀለኞቹ ግዙፉን ትርፍ ሲያጎርፍ፣ በሌላው በኩል በመላው ዓለም ውስጥ መንግሥታትን የሚያስጨንቅ ትልቅ ችግር ነው የሚፈጥረው። ከጥቂት ቀናት በፊት ሄልሲንኪ/ፊንላንድ ውስጥ ጉባኤ ያካሄደው የአውሮጳ ፀጥታ አጠባበቅና ትብብር ድርጅት ስደተኞች የሚገኙበትን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ግልጽ ለማድረግ ሞክሮአል።

በሰው የሚደረገው ንግድ ዛሬ በሕገወጡ መንገድ ትልቁን ዓለምአቀፍ ገበያ የፈጠረ ሆኖ ነው የሚታየው። ሁኔታውን በሚከታተሉት ጠበብት ግምት መሠረት፥ በመላው ዓለም ውስጥ የሚገኙና በመቶ የሚቆጠሩ ሕግወጥ ድርጅቶች በሰው በመነገድ ብቻ ጥሩ የተድላ ኑሮ ነው የሚመሩት። በሰው በመነገድ ብቻ ለሚቶጅሩት ወንጀለኛ ቡድኖቾ ለዚሁ ሕገወጥ ተግባር ሁኔታውን የሚያመቻችላቸው፥ በሕጋዊው መንገድ ወደ ሐብታሞቹ ሀገሮች መፍለስ በየጊዜው አስቸጋሪ የሚሆንበት ድርጊት ነው። ሕጋዊው መንገድ የሚዘጋባቸው የሦሥተኛው ዓለም ፈላስያን ወይም ስደተኞች ብዙ ገንዘብ እያስከፈሉ በሕገወጡ መንገድ የሚያሸጋግሩትን ወንጀለኞች አገልግሎት ለመሻት ይነሳሳሉ። እነዚሁ በሰው የሚነግዱት ወንበዴዎች እየተደራጁ በኅቡእ ነው የሚንቀሳቀሱት። አንዱን ፈላሲ ወይም ስደተኛ በሕገወጡ መንገድ ወደ አንዲት ሐብታም ሀገር ለማሸጋገር የተለያየ ዋጋ ነው የሚጠየቀው። እንደ ጉዞው ዓይነት መጠን--በባሕር ወይ,ም በአየር--ዋጋው ከግዳጅ ወሲብ አንስቶ እስከ ፲፭ሺ ዶላር ሊደርስ ይችላል። ብዙ ገንዘብ ከፍለው በየአሮጌ መርከቦችና ጀልባዎች እየታጨቁ ወደ ባሕርማዶ ለመሸጋገር የሞከሩ ብዙ የሦሥተኛው ዓለም ፈላስያን ባሕር ውስጥ ሕይወታቸውን ማጣታቸው በየጊዜው ነው የሚመለከተው። ሰሞኑንም በሰሜን አፍሪቃዊቱ ሀገር ቱኒዚያ ጠረፍ ፊትለፊት ፸፭ ሕገወጥ ፈላስያንን ያጨቀች አንዲት አሮጌ መርከብ አደጋ ደርሶባት ቢያንስ ፲፯ ስደተኞች ሲሰጥሙ፣ ፵፯ቱ እንደጠፉ መቅረታቸው፣ መርከቢቱም መስጠሟ ነበር የተዘገበው። በዘገባው መሠረት፣ በመርከቢቱ እየተሳፈሩ ወደ ኢጣሊያ ሊሸጋገሩ የነበሩት ጠቅላላው ሕገወጥ ፈላስያን ፪፻፹ ነበሩ። ያይን ምሥክሮች እንደገለፁት፣ ስደተኞቹን ያጨቀችው አሮጌ መርከብ ባሕሩ ላይ መንቀሳቀስ ከጀመረች በኋላ አንድ ሰዓት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ ነበር ተሰባብራ የሰጠመችው። በያመቱ ከአፍሪቃ እየተነሱ በሕገወጡ መንገድ ወደ አውሮጳ ለመሸጋገር አእላፍ ፈላስያን ናቸው ሙከራ የሚያደርጉት፣ ግና ከእነዚሁ መካከል ብዙዎቹ የፖለቲካ ተገን ተሥፋቸውን ሳይደርሱበት ለመከራና ለአደጋ ነው የሚዳረጉት።

“ያለ ረዳት ሽሽት የለም” ይላል ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽነል የሚያጎላው ማስገንዘቢያ። ይኸውም፥ ስደተኞች ትውልድ-ሀራቸውን ለቅቀው ለመውጣት የሚችሉት፥ በአፍአዊው ርዳታ አማካይነት ብቻ መሆኑ ነው። ስደተኞቹ ይህንኑ አፍአዊ ርዳታ ተመርኩዘው ለሽሽት በሚነሳሱበት ጊዜ ይሉኝታን በማያውቁ በዝባዦች እጅ የሚወድቁበት አደጋ በጣም የጎላ ነው። ዓለምአቀፉ መድኅን ኮሚቴ በሚያቀርበው ግምት መሠረት፥ ለወንጀለኞቹ አሸጋጋሪ ድርጅቶች ብዙ ገንዘብ እየከፈሉ በሕገወጡ መንገድ ወደ ባሕር ማዶ ለመፍለስ የሚነሳሱት ሰዎች አሃዝ ከ፯፻ሺህ እስከ አራት ሚሊዮን የሚደርስ ነው፤ ትክክለኛው አሃዝ ተጣርቶ አይታወቅም።

ስደተኞቹ አውሮጳንና ዩኤስ-አሜሪካን ብቻ አይደለም ለፖለቲካ ተገን ዓላማቸው መድረሻ ለማድረግ የሚነሳሱት። በሰው የሚነግዱት ወንጀለኞቹ ቡድኖች ዛሬ በመላው ዓለም ውስጥ ነው የተደራጁት። ለስደተኞቹም ሆነ ወይም ለአሸጋጋሪዎቹ ስብስቦች ለምሳሌ በባሕረሰላጤው ዙሪያ የሚገኙት ነዳጅዘይት ላኪዎቹ ሀገሮችም ናቸው መስሕብ የሚሆኑት። በምድርዘይት ሐብት የከበሩት የባሕረሰላጤው አካባቢ ሀገሮች በተለይም ደኽየት ካሉት ዓረባውያት ሀገሮችና ከእስያ የሚነሱትን ስደተኞች ነው የሚስቡት። በሰባኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ ፮፻፶ሺ የነበረው የእነዚሁ ስደተኞች አሃዝ አሁን ከአሥር ሚሊዮን በልጧል። በሩቅ ምሥራቅ ደግሞ፣ ብዙ ስደተኞች ወደ ጃፓን ወይም ወደ እንዱስትሪያዊው የዕድገት ደረጃ ወደተቃረቡት ገስጋሾቹ የደቡብምሥራቅ እስያ ሀገሮች ለመሸጋገር ነው የሚጣጣሩት። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አውስትራሊያም ናት ለሕገወጥ ፈላስያን ትልቅ መስሕብ እየሆነች የተገኘችው።

ስደተኞች ወይም ፈላስያን፥ በበዝባዦች እጅ እንደሚወድቁ ወይም ሕይወትን ለሚያሳጣው ለከባዱ አደጋ እንደሚዳረጉ እያወቁት ነው በሕገወጡ መንገድ ለመሸሽ የሚነሳሱት። ከትውልድ ሀገር ለመሸሽ የሚያነሳሳው ዓቢዩ ምክንያት፥ በብዙ የሚደረጁ ሀገሮች ውስጥ የሚፈራረቀው ጦርነት ነው። ለዚህ አንድ ምሳሌ የሚሆኑት፥ የቀድሞዎቹ ቅኚግዛቶች ነፃነታቸውን ካገኙበት ድርጊት ጋር እየተያያዙ የመጡት ውዝግቦች ናቸው። አሁንም ቢሆን፣ በ፳፩ኛውም ምእተ-ዓመት መጀመሪያ ላይ፣ ጦርነት ነው ዋነኛው የሽሽት ምክንያት። ከዚሁ ጎንለጎን፥ በብዙ የሦሥተኛው ዓለም ሀገሮች ውስጥ ያለው ከባዱ የኤኮኖሚ ውድቀትና ድህነትም ነው ለስደተኞች ጎርፍ ተጠያቂ የሚሆነው።

እነዚሁ ድሆቹ ሀገሮች ናቸው ብዙውን ጊዜ ፈጣኑን የሕዝብ ጭማሪ የሚያስመዘግቡት፥ ግና ይኸው አለቅጥ ፈጣኑ የሕዝብ ጭማሪ ነው የጉስቁልናውን ሁኔታ የሚያባብሰው። አሁን በሚቀርበው ስሌት መሠረት፣ እጎአ በ፪ሺ፶ ዓ.ም. 9.4 ሚሊያርድ ከሚደርሰው የዓለም ሕዝብ ስምንት ሚሊያርዱ በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ የሚኖር ይሆናል። ይኸው ሁኔታ በበኩሉ በእነዚያኑ ሀገሮች የተፈጥሮ ጓዳ ላይ ከባዱን ጎጂ ግፊት መፍጠሩ የማይቀር ነው። ይኸውም፥ “የሕዝበት ፍንዳታ” የሚሰኘው አለቅጥ ፈጣኑ የሕዝብ ጭማሪ የአፈርን ይዘት የሚያዳክምና የሚያራቁት፣ ደንን የሚያስመነጥር፣ የምድር ውስጡን ውሃ የሚያስሟጥጥ እና የአየሩን ንብረት የሚያቃውስ ነው የሚሆነው--ጠበብቱ እንደሚያስጠነቅቁት። ይኸው ተቃዋሽ ሁኔታ የኋላኋላ የፈላስያንን እና የስደተኞችን ጎርፍ ያባብሳል ማለት ነው። እንዲያውም፣ ያሁኑ የስደተኞች ጎርፍ ገና መቅድሙ ሆኖ የሚያዩት የምርምር ጠበብት፥ ዓለምአቀፉ የሕዝቦች ፍልሰት ወደፊትም ፍጥነቱን እየጨመረ ገና ወደ ብዙ ትውልዶች ሽግግሩን መቀጠሉ አይቀርም ነው የሚሉት።

አስቀድሞ እንደተጠቀሰው፣ ሕገወጥ ፈላስያንን በሕገወጥ መንገድ ወደ ባሕር ማዶ የሚያሸጋግሩት፣ በዓለምአቀፍ ደረጃ ራሳቸውን የሚያደራጁት የውንብድና ቡድኖች በዚሁ ሰውን መነገጃ በሚያደርጉበት የወንጀል አድራጎታቸው በዓመት ከ፳ እስከ ፴ ሚሊያርድ ዶላር ትርፍ እንደሚያጋብሱ ነው የሚገመተው። በዚህ አኳኋን፣ በሰው የሚደረገው ንግድ ልክ እንደ ዓለምአቀፉ የአብሾ ወይም የጦርመሣሪያ ኮንትሮባንድ ንግድ ወፍራሙን ገቢ የሚያጎርፍ መሆኑ ነው።