1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰሞኑ የሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉና በርካቶች መፈናቀላቸው ተሰማ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 27 2016

በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤ ዶንጎሮ እና ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች ካለፈው ሳምንት ሀሙስ ጀምሮ እንደ አዲስ ተቀሰቀሰ በተባለው ግጭት ሰላማዊ ዜጎች ጭምር የግጭቱ ሰለባ እየሆኑ ነው ተባለ፡፡ በተለይም በአቤዶንጎሮ ወረዳ ጎልቶ ተስተውሏል በተባለው በዚሁ አዲስ ግጭት የሰዎች ህይወት ስለማለፉና ነዋሪዎችም መፈናቀላቸው ተገልጿል፡፡

https://p.dw.com/p/4gdNL
ፎቶ ማህደር፤ተፈናቃዮች በባህርዳር
ፎቶ ማህደር፤ተፈናቃዮች በባህርዳርምስል Privat

በሰሞኑ የሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉና በርካቶች መፈናቀላቸው ተሰማ

የግጭቱ መንስኤ

በሆሮ ሀጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤዶንጎሮ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ መሆናቸውን ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ነዋሪ ባለፈው ሐሙስ በሰፊው ተቀሰቀሰ ባሉት አዲስ ግጭት እሳቸውን ጨምሮ በርካቶች ወደ ጫካ መሸሻቸውን አስረድተዋል፡፡ የግጭቱም መነሻ በአከባቢው ከመንግስት እውቅና ውጪ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የተባሉ ታጣቂዎች ላይ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ተኩስ መክፈታቸው ነው የሚሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፤ ግጭቱን ከባድ ሲሉ ገልጸውታልም፡፡ድጋፍ የሚሹት ከሆሮጉድሩ ወለጋ የተፈናቀሉት ወገኖች

“አረ እንደው ነገሩ ከብዷል፡፡ በየቤቱ በየአቅጣጫው ይገድላሉና ሰው ወደ ጫካ እየሸሸ ነው” የሚሉት አስተያየት ሰጪው ከዚህ በፊት እርቅ ወርዶ ተረጋጋቶ የነበረው አከባቢው ወደ ቀድሞው ቀውስ መመለሱን አስረድተዋል፡፡ “ፋኖ አምጡ” በሚል በመንግስት ጸጥታ ኃይሎች የተከፈተው ግጭቱ አከባቢውን መረጋጋት ነስቶታል በሚል ሀሳባቸውን ገልጸዋል አስተያየት ሰጪ ነዋሪው፡፡

የሰላማዊ ሰዎች ሰቆቃ

ሌላው ከዚሁ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡት ለደህንነታቸው ሲባል ግን ስማቸውን ያልገለጹት አስተያየት ሰጪም፤ ባለፈው ሀሙስ የጀመረው ችግር ተባብሶ በመቀጠል ወደ አጎራባች ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳም ትሰፋፍቷል ነው የሚሉት፡፡ “የው ነው አሁንም ችግሩ ተባብሶ እንደቀተለ ነው፡፡  ባለፈው ሀሙስ የተጀመረው አለመረጋጋት አሁን ላይ በአቤ ዶንጎሮ እና ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች ላይ ነው ከባድ ውድመትና ኪሳራ እያደረሰ ያለው፡፡ እራሳቸውን ለመከላከል በሚል የታጠቁ ሚሊሻዎችን ትጥቅ ለማስፈታት በሚል የተጀመረው ግጭት አሁን ላይ ምንም ለማያውቁት ህጻናትም ጭምር ነው ዳፋው የተረፈው” ሲሉም ግጭቱ በሰላማዊ ዜጎችም ላይ ጉዳት ማድረሱን አስረድተዋል፡፡የሆሮጉድሩ ተፈናቃዮች ሮሮ

ሌላም ሀሳባቸውን ያከሉ የአከባቢው ነዋሪ አሁንም ድረስ ቀጥሏል ባሉት ሰሞነኛው ግጭት ከየቦታው አስከሬን ማግኘታቸውንና ግጭቱን ሽሽት ወደ ጫካ የገባው ማህበረሰብ ለርሃብ እየተዳረገ መሆኑን በአስተያየታቸው ጠቁመዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ ስለዚሁ የሰሞኑ ግጭት ምንነትና እልባቱን በተመለከተ ከአከባቢው ባለስልጣናት በተለይም ከሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሚሬሳ ፊጤ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት በተደጋጋሚ የእጅ ስልካቸው ላይ በመደወል ጥረት ብናደርግም ለዛሬ አልሰመረልንም፡፡

የወለጋው ግጭት ዳራ

ባለፉት አራት ዓመታት በአራቱ የወለጋ ዞኖች ግጭት አለመረጋጋቱ ከተስፋፋ ወዲህ በተደጋጋሚ የሚከሰተው በተለይም ብሔረን መሰረት ያደረገው ግጭት በርካቶችን አፈናቅሎ ቁጥራቸው የማይናቅ ዜጎችንም ህይወት መቅጠፉ ይታወቃል፡፡ በዚህ አከባቢ በተለይም የኦሮሞ እና አማራ ብሔር ማህበረሰቦች ለዘመናት ተዋደው መኖራቸው ቢነገርም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ግጭቶች፤ በተለይም አልፎ አልፎ የታዩ የብሔር መልክ የያዙ የተባሉ ግጭቶች የአከባቢውን የጸጥታ ሁኔታ አወሳስበውት መዝለቁ ይታወሳል፡፡ስለ ሆሮጉዱሩው ጥቃት የፓርቲዎች መግለጫ

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህም በማህበረሰቡ መካከል የተፈጠሩትን ግጭቶች በእርቅና ውይይት የመፍታት ጥረቱ ስለመጀመሩ ተደጋግሞ ቢነገርም  ከአከባቢው ግጭትን ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ግን ቢያንስ እስካሁን ቀላል አለመሆኑ ነው የሚነገረው፡፡

ስዩም ጌቱ

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ