1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሰሜን ኢትዮጵያ የማገርሸት ምልክት እያሳየ ያለው ጦርነት

ሰኞ፣ ግንቦት 8 2014

ለሰሜን ኢትዮጵያው የዓመት ከመንፈቅ ጦርነት የሰላም አማራጮች የቀረቡ ቢመስሉም አሁንም ጦርነቱ ሊያገረሽ እንደሚችል ምልክቶች መታየታቸው እየተገለፀ ነው። ጉዳዩን የሚከታተሉት ባለሙያ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት፤ ጦርነቱን አሁንም በሰላማዊ አማራጭ የመቋጨት መንገድ ሙሉ በሙሉ ባይዘጋም ነገሮች የሚያሳዩት ስለ አይቀሬው ሌላኛው ምዕራፍ ጦርነት ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4BMtb
Karte Äthiopien Region Tigray DE

በሰሜን ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ባይቋረጥም ለወራት ጋብ ብሎ የተስተዋለው ጦርነት ሰሞኑን የማገርሸት አዝማሚያን እያሳየ ነው፡፡ በተለያዩ መንገዶች የሰላም አማራጮች ለወራት ሲፈለግለት ነበር የተባለው ጦርነቱ አሁን አሁን በጦርነቱ ውስጥ በነበሩ ሁሉም ወገኖች የእርቁን መንገድ ተስፋ የሚያደበዝዝ እና የአውዳሚው ጦርነት መቀጠል ምልክት የሚያሳዩ መልእክቶች መደመጥ ጀምረዋል፡፡ ከወራት በፊት ለሰብኣዊ እርዳታ መቀላጠፍ ሲባል ተደርጓል የተባለው የሁሉም ወገን የተኩስ አቁም ጥሪ እና አዋጅም ያሳየው ተስፋ ዘለቄታዊነቱ አጠራጥሯል፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያውን የፖለቲካ ሁናቴ በቅርበት የሚከታተሉትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ የማይቀር የሚመስለውን ጦርነት ሰሞኑን በማቀንቀን ረገድ ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ ያለው ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) ቀዳሚውን ድርሻ ይወስዳል ባይ ናቸው፡፡

ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ አንዴም ሁለት ሶስቴ በመመላለስ ሶስት የሰራዊታቸውን ማዕከላት (በሰቆጣ፣ ወልዲያ እና ወልቃይት ጠገዴ) በመጎብኘት አስፈላጊ ላሉት ጥቃት ሁሉ እንዲዘጋጁ መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡ ትግራይ ክልልን እያስተዳደረው የሚገኘው ህወሓትን የሚመሩት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው በቅርቡ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጻፉት በተባለው ደብዳቤ ሰራዊታቸው የትግራይ ህዝብ ላይ ፈጸማል ያሉትን ከበባ ለመስበር እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ካስጠነቀቁም የሳምንታት ዕድሜ ተቆጥሯል፡፡ 

Äthiopien | Binnenvertriebene aus Tigray
ተፈናቃዮችምስል Alemnew Mekonnen/DW

ከወራት በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ በተካሄደው አውዳሚ እና ደም አፋሳሽ ጦርነት የፌዴራል መንግስት የወታደራዊ የበላይነትን በትግራይ ኃይሎች ላይ ማሳየቱን ካሳወቀ በኋላ ሰራዊቱ ወደ ትግራይ ክልል የሚያደርገውን ግስጋሴ እንዲገታ በማዘዝ ጦርነቱን በሰፊው ማቀዝቀዙ፤ በቅርቡም ለሰብዓዊ ድጋፍ መጓጓዣ ሲባል ጦርነቱ እንዲቆም በማወጁ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ መንግስትን የሚዋጋው ህወሃት አዎንታዊ ምላሽ መስጠቱ ለሰላማዊ የጦርነት መቋጫ መንገዶች በሮች የተከፈቱ መስለው ነበር፡፡ ይሁንና ይህም ሂደት በአንዳንዶች እምነት ተፈላጊውን ሰላም በተፈለገ ፍጥነት ያመጣ አይመስልም፡፡ እንደ ዶ/ር ሲሳይ መንግስቴ ማብራሪያ ግን ለሰላም አማራጩ አሁንም አልመሸም፡፡ 
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ባለፈው ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ ህወሓት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ጦርነቱን ለመቀስቀስ እየሰራ ነው በሚል ከሰውት፤ መንግስት ጥቃቱን ለመመከት አስፈላጊ ያሉት ዝግጅት ማድረጉን አመልክተው ነበር፡፡ መንግስት ወደ ትግራይ እና ሌሎችም አከባቢዎች የሚደረጉ ሰብዓዊ ድጋፎች እንዲቀላጠፉ ህወሓት ከያዛቸው አጎራባች ክልሎች እንዲወጣ ቢጠይቅም እስካሁንም አፋር ክልልን ጨምሮ የተለያዩ አከባቢዎችን ለቆ ሳይወጣ መንግስትን እርዳታ በማስተጓጎል ከሳል በማለት ወርፈውታልም፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በፊናው ትናንት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ኃይሎች እና በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት መካከል ውጥረት እየጨመረ መምጣቱ እንዳሳሰበው በመግለጽ፤ ለጋራ መግባባት እና ሰላም ሁሉም እንዲተባበር ጥሪ አቅርቧል።

ሥዩም ጌቱ

ልደት አበበ
ኂሩት መለሠ