በርካታ አፍሪቃዉያን የጀልባ ስደተኞች ሰመጡ | አፍሪቃ | DW | 19.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በርካታ አፍሪቃዉያን የጀልባ ስደተኞች ሰመጡ

ከአሌክሳንድርያ ግብፅ በጀልባ ወደ አዉሮጳ ለመግባት የሞከሩ ከ 400 በላይ ስደተኞች መሞታቸዉ በሚወራበት በአሁኑ ወቅት 500 ስደተኞችን ያሳፈረች ሌላ ጀልባ የደረሰችበት አለመታወቁ እየተነገረ ነዉ። የጀልባ ላይ ስደተኞቹ ከኢትዮጵያ ከኤርትራ አልያም ከሶማልያ መምጣት አለመምጣታቸዉ ግን በዉል አልተረጋገጠም።

የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ያልተረጋገጡ ምንጮችን ጠቅሰዉ እንደዘገቡት በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከሰሜን አፍሪቃ ወደ ኢጣሊያ በጀልባ በመጓዝ ላይ እንዳሉ የሰመጡት ሰዎች የኢትዮጵያ የኤርትራና የሶማልያ ዜጎች ናቸዉ ይባላል።በጀልባ ላይ ከነበሩት ተሳፋሪዎች መካከል የ 29 ሰዎችን ሕይወት ብቻ ማትረፍ መቻሉ ነዉ የተነገረዉ ።

ከ 500 በላይ ከሶማልያ ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የመጡ ተሳፋሪዎችን ጭነዉ ሜዲተራንያን ባህርን በአራት ጀልባ አቋርጠዉ ወደ አዉሮጳ ለመግባት የሞከሩት ተገን ጠያቂዎች የተነሱት፤ ከግብጽዋ የባህር ዳር ከተማ ከአሌክሳንድርያ መሆኑ ነዉ የተነገረዉ። ከነዚህ ስደተኞች መካከል ከ 400 በላይ ስደተኞች መሞታቸዉም ታዉቋል። እስካሁን ግን የተረጋገጠ ዘገባ አልደረሰንም። በስዊድን ነዋሪ የሆኑትና ኤርትራዊትዋ የስደተኞች መብት ተሟጋች ሜሮን እስጢፋኖስ እንዳሉት በጀልባዉ ላይ የነበሩት በርግጥ ከየትና እንደማን እንደነበሩ ማወቅ አልቻልንም።

Lampedusa: völlig entkräfteter Flüchtling aus Somalia

«ስለደረሰዉ አደጋ ሰምቻለሁ፤ ማረጋገጥ አልችልም ግን ከየት እንደመጡና ማንነታቸዉን ለማረጋገጥ 2 እና 3 ቀናት ይፈጅብናል። ማንነታቸዉን ልናረጋግጥ የምንችለዉ ከቀናት በኋላ ቤተሰቦቻቸዉ እኔጋ ሲደዉሉ ነዉ። ይህን ሁሉ ለማረጋገጥ ጊዜዉ አሁን ገና ነዉ። መጀመርያ ላይ የሚወጡ ዘገባዎች ብዙዉን ጊዜ ስህተት ይኖርባቸዋል። ከቀናቶች በኋላ ግን ማወቅ ይቻላል።»

ባለፈዉ ዓመት ሜድትራኒያን ባሕር ዉስጥ ከ 700 በላይ ሰዎች የሰጠሙበትን ከፍተኛ አደጋ ያስታወሱት ሜሮን፤ በአሁኑ ወቅት ይላሉ የአየሩ ፀባይ አስተማማኝ በመሆኑ ስደተኞች በጀልባ ወደ አዉሮጳ ለመግባት ሙከራ ላይ ናቸዉ።

«የአየር ሁኔታዉን ተከትሎ የጀልባ ላይ ስደተኞች ወደ አዉሮጳ ለመግባት ጥረት የሚያደርጉበት ወቅት ነዉ። ባለፈዉ ዓመት በዚሁ ጊዜ ወደ አዉሮጳ ለመግባት ጥረት ያደረጉ 800 የሚሆኑ ሰዎች ነበር በአንድ ጊዜ ባህር የሰመጡት። ከነዚህ መካከል 300 ያህሉ ኤርትራዉያን ናቸዉ ብለን እናምናለን። እናም በተመሳሳይ በዚህ ዓመት ይኸዉ ሁኔታ ነዉ እያየን ያለዉ። ትናንት ይፋ በሆነዉና ሜዲተራንያን ላይ ሰመጡ ከተባለዉ ጀልባዎች ስንት ኢትዮጵያዉያን ኤርትራዉያን አልያም ሶማልያዉያን እንደነበሩ የሚታወቅ ነገር የለም።»

DW TV Sendung Africa on the Move Meron Estefanos

ኤርትራዊትዋ የስደተኞች መብት ተሟጋች ሜሮን እስጢፋኖስ

ባልካን መንገድ በመባል የሚታወቀዉ ስደተኞች ወደ መሃል አዉሮጳ የሚገቡበት መንገድ በመዘጋቱ ተገንጠያቂዎች ወደ አዉሮጳ የሚገቡበትን መንገድ መቀየራቸዉ ተሰምቶአል። በሊቢያ ብቻ ከ 300 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ አዉሮጳ ለመግባት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙም ተዘግቧል። ሜሮን እስጢፋኖስ ፤ «በሊቢያ በመጠባበቅ ላይ ከሚገኙት ሰዎች መካከል በርካታ አበሾችም ይገኛሉ» ሲሉ ተናግረዋል።

«ሰምቻለሁ ። በርካታ አበሾች በጀልባ ወደ አዉሮጳ ለመሻገር እየተጠባበቁ ይገኛሉ። በርካታ አበሾችም የሱዳን በረሃን አቋርጠዉ ወደ ሊቢያ እየገቡ መሆኑን ሰምቻለሁ። አሁን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረና እየጨመረ የመጣዉ ወደ አዉሮጳ ለመሻገር የሚፈልጉ አብዛኞቹ ስደተኞች በግብፅ በኩል ነዉ ሙከራቸዉን እያደረጉ የሚገኙት። ከአሌክሳንድርያ ግብፅ በጀልባ ተሳፍረዉ ወደ ጣልያን ለመግባት ሙከራ እያደረጉ ነዉ። ይህን መንገድ የመረጡት ደግሞ በ «IS» ምክንያት ነዉ። «IS » እያፈነ ሰዎችን ይወስዳል፤ የቻድ ዜጎችም ሰዎችን አፍነዉ ይወስዳሉ። በዝያ ምክንያት ወደ አዉሮጳ መግባት የፈልጉ ተገን ጠያቂዎች፤ በሊቢያ በኩል ወደ አዉሮጳ ለመግባት ሙከራ ከማድረግ ይልቅ ሙከራቸዉን በግብፅ አሌክሳንድርያ በኩል አድርገዋል። ይህም ከአፍሪቃ የጀልባ ስደተኞች ተነስተዉ የሚሞክሩበት ታዋቂ መንገድ ሆንዋል።»

ኤርትራና ኢትዮጵያዉያኑን አበሻ ሲሉ በጥቅል ስም የሚያስቀምጡዋቸዉ ኤርትራዊትዋ የስደተኞች መብት ተሟጋችዋ ሜሮን ስጢፋኖስ በግብፅ እስር ቤትም ጥቂት የማይባሉ አበሾች እንደሚገኙ ነዉ የገለፁት።

«አዎ በአሌክሳንድርያም በኩል አድርገዉ በጀልባ ሜዲተራንያንን ለማቋረጥ ሲሞክሩ የተያዙ በርካታ አበሾች አሉ። አብዛኞቹ ከግብፅ እስር ቤቶች ሆነዉ ይደዉሉልኛል። የግብፅ መንግሥት አብዛኞቹን ወደ የአገራቸዉ እንዲመለሱ ይደረጋል። ይህ መረጃ ባለፉት ሳምንታት የሆነ ነገር ነዉ። በግብፅ ብዙ ሙስና የሚታይ በመሆኑ ባለስልጣናቱ ራሳቸዉ ገንዘብ እየተቀበሉ ብዙ ሰዎችን የባህር ጉዞ እዲጀምሩም ያደርጋሉ። ስለዚህ ራሱ ስርዓቱም ነዉ። »

አደገኛ የባህር ጉዞ የሚሰደዱ ወጣቶችን የሚረዳውና መቀመጫውን ኢጣልያ ያደረገው ኤጀንስያ ሐበሻ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት መስራችና ሃላፊ አባ ሙሴ ዘርዓይ እንደሚሉት፤ ትናንት ከተሰማዉ አደጋ ሌላ ሌላ 500 ሰዎችን የጫነች መርከብ መጥፋትዋን ሰምተናል። የጣልያን የባህር ላይ ጠባቂዎች እንዲፈልጉ ተናግረናል። በሌላ በኩል በትናንትናዉ እለት ከሊቢያ የተነሱ 130 የጀልባ ላይ ስደተኞችን ሕይወት ማትረፍ መቻሉንና 27 ሰዎች መስመጣቸዉን የጣልያን የባህር ጠባቂዎች አስታዉቀዋል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic