በርካታ ቋንቋ ለሕጻናት ጠቀሜታው | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 06.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በርካታ ቋንቋ ለሕጻናት ጠቀሜታው

ሕጻናት በለጋ ዕድሜያቸው በርካታ ቋንቋዎችን በቀላሉ መማር ስለመቻላቸው ተመራማሪዎች በአንድነት ይስማማሉ። ሕጻናቱ በርካታ ቋንቋዎችን መማራቸው ለወደፊት የማኅበራዊ ሕይታቸው ጠቃሚ ከመሆኑም ባሻገር አዕምሯቸው በፈጣን ኹናቴ እንዲበለጽግ ያግዛል ሲሉም ተመራማሪዎች ይናገራሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:31

በርካታ ቋንቋ ለህፃናት

ሕጻናት ዕድሜያቸው ሦስት ዓመት እስኪሞላው ድረስ በርካታ ቋንቋዎችን በአዕምሯቸው ጓዳ በቀላሉ ማኖር ስለመቻላቸው ሣይንቲስቶች በጋራ ይስማማሉ። የሕጻናቱ ለጋ አዕምሮ በተለይ ሦስት ዓመት እስኪሞላ ድረስ የተሰጡትን ቋንቋዎች አከማችቶ የማቆየት አቅም እንዳለው ተመራማሪዎች ይገልጣሉ።

ሕጻናት በርካታ ቋንቋዎችን ልክ እንደ አንድ ቋንቋ መማር እንደሚችሉ የተመራማሪዎች ጥናት ያትታል። ህጻናቱ በርካታ ቋንቋዎችን መማራቸው ለማኅበራዊ ጉድኝታቸው ወደፊት አስተዋጽዖ ይኖረዋል። ከዚያም ባሻገር በርካታ ቋንቋ ለሕጻናት ለዕምሮ ጥሩ እንደሆነ ጠበብቱ ይገልጣሉ። የዶይቸ ቬለዋ ብርጊተ ኦስተራት ልጆቻቸውን በርካታ ቋንቋ እያስተማሩ የሚያሳድጉ ወላጆችን ቦን እና ኮሎኝ ከተሞች ውስጥ ጎብኝታለች።

አኒታ ገና ሁለት ዓመትም አልሞላት። ሆኖም ገና ካሁኑ በርካታ ቋንቋዎችን እየማረች ነው። ወጣቷ እናቷ ቤቲና ከብራዚል ነው የመጣችው፤ ፖርቹጋልኛ ቋንቋ ትናገራለች። ሕንዳዊው አባቷ ፑግራች አፍ የፈታው በሒንዱ ቋንቋው ነው። እሱም ወጣት ነው። ባል እና ሚስቱ ቦን፤ ጀርመን መኖር የጀመሩት አኒታ ከመወለዷ ቀደም ብሎ ነው። አኒታ የተለያዩ ቋንቋዎችን እየሰማች ነው የምታድገው። በምትኖርበት አካባቢ የሚነገረው ቋንቋ ጀርመንኛ ነው። ፑግራች አፍ የፈታበት ሒንዲ በሕንድ የሥራ ቋንቋ ነው።

ሕንዳዊው የአኒታ አባት ፑግራች ቾዳሪ

ሕንዳዊው የአኒታ አባት ፑግራች ቾዳሪ«ከቤተሰቦቼ አብዛኞቹ መናገር የሚችሉት ሒንዲ ብቻ ነው። ስለዚህ አብዛኞቹ የቤተሰቦቼ አባላት ሕንድ ውስጥ ነዋሪ በመሆናቸው ልጄ ሒንዲ መማሯ ለእኔ አስፈላጊ ነው። እንግሊዝኛ ያው ትምህርት ቤት ስትሄድ መማር ትችላለች።»

ጀርመንኛ፣ ፖርቹጋልኛ እንዲሁም ከአያቶቿ ጋር ለመግባባት ሒንዲ ቋንቋ ማወቋ አኒታ ብዙ ቋንቋ በመማሯ የምታገኘው አንደኛው ጥቅም ነው። ህፃናት በርካታ ቋንቋ እየተማሩ ማደጋቸው አዕምሯቸው የተፍታታ እንዲሆን እንደሚረዳ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ገና በለጋነታቸው ራሳቸውን በሌላ ሰው ቦታ አድርገው መመልከት ይችላሉ። የተለያዩ ነገሮችን በቀላሉ እየቀያየሩ መሥራትንም ይካኑበታል።

ከዚህ ቀደም የተከናወነ አንድ ጥናት ላይ ሕጻናት ሰማያዊ ቀለም ያላቸው አራት ማዕዘናትን እና ቀይ ክበባትን እንዲለዩ ተደረገ። መጀመሪያ ቀለሙን ከዚያም ቅርጹን እንዲለዩ ነበር የተፈለገው። እናስ ውጤቱ ምን ይመስል ነበር? ክላውዲያ ማሪያ ሪል፤ ሙይንሽን ከተማ ውስጥ በሚገኘው የሉድቪች ማክስሚሊያንስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ናቸው። አጥኚዎቹ የደረሱበትን ውጤት እንዲህ ይገልጣሉ።

«በርካታ ቋንቋ እየተናገሩ የሚያድጉት ልጆች አንድ ቋንቋ ብቻ ከሚማሩት እጅግ በተሻለ የተሰጣቸውን ትእዛዝ በሚገባ ፈጽመው ሌላኛው ላይ ማተኮር ችለዋል። መለየት ችለዋል። ይኽ የሆነበት ምክንያትም ብዙ ቋንቋ እየተናገሩ የሚያድጉ ልጆች አንድ ቋንቋን ሲናገሩ ሌላኛውን መጫን መቻላቸው ነው።»

በርካታ ቋንቋዎችን መማር አእዕምሮ በተሻለ መልኩ እንዲቀየር እገዛ ያደርጋል። በዚያ መልኩ የሚያድጉ ልጆች አንዳች ነገርን በትኩረት መቆጣጠር የሚችለው ግራጫማው የዕምሮ ክፍላቸው በላቲን አጠራሩ (Substantia grisea) በተሻለ መልኩ ይበለጽጋል። ይኽ ክፍል የነርቭ መዋቅር ማዕከል ዋነኛው አካል ነው። በነገራችን ላይ ግራጫማው የዕምሮ ክፍል የመበልጸጉ ጉዳይ በርካታ ቋንቋዎችን በሚናገሩ አዋቂዎችም ዘንድተመሳሳይ ነው።«በርካታ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሰዎች በተለይ ቋንቋዎቹን በቀን ተቀን ሥራቸው ላይ የሚተገብሩ ሰዎች አዕምሮዋቸውን የበለጠ የማሠራቱ ዕድል አላቸው። ምክንያቱም አዕምሯቸው የትኛውን ቋንቋ ከማን ጋር መቼ ልናገረው በሚል በመጠኑ ሥራ ይበዛበታልና። ይኼኛውን ቋንቋ ስናገር ይኼኛውን ማስቀረት አለብኝ እያለም አዕምሮ በመጠኑ ያጠይቃል።»

በርካታ ወላጆች ልጆቻቸው የተለያየ ቋንቋ በአንድ ጊዜ መማራቸው ግራ ያጋባቸዋል የሚል ስጋት አላቸው። ሆኖም ይኽ በተመራማሪዎች ዘንድ ትክክል አይደለም። ልጆች ፈጽሞ ግራ አይጋቡም፤ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ አንደኛውን ቋንቋ ሌላኛው ላይ ለመጠቀም ይሞክራሉ እንጂ። ይኽ በሁለት ዓመቷ አኒታ ላይም የሚስተዋል እንደኾነ እናቷ ቤቲና ትናገራለች።

«ብዙ ጊዜ ስለ ጸጉሯ ሳዋራት ያ ይከሰታል። እናም በፖርቹጋልኛ ካቤሎ እላታለሁ። ካቤሎ ጸጉር ማለት ነው። እሷ ግን የምትመልሰው ባል ብላ ነው። መጀመሪያ ላይ ይኽን ቃል ስሰማ ደግሞ ባል ማለቷ ምን ለማለት ነው ብዬ ራሴን ጠይቄ ነበር። ጥሩ ጀርመንኛ ቋንቋ ታውቃለች ማለት ነው፤ ባል ጀርመንኛ ኳስ ማለቷ ነው አልኩ። ግን አባቷ ሲያብራራልኝ፦ ለካ ባል በሒንዲ ቋንቋ ጸጉር ማለት ነው። እናም ከዛን ጊዜ አንስቶ ጸጉሯን ማበጠር ስፈልግ ባል፣ ባል፣ ባል፣ ትላለች፤ እኔም አዎ፤ አዎ ተግባብተናል እላታለሁ።»

ያም በመሆኑ ቤቲና እና ፑግራች ልጃቸው የተለያዩ ቃላትን ከተለያዩ ቋንቋዎች መጠቀሟ ምንም አያስጨንቃቸውም። ሕጻናት በአንድ ዐረፍተ-ነገር ውስጥ የተለያዩ ቃላትን ከተለያዩ ቋንቋዎች ወስደው ቢጠቀሙ አንዳችም ችግር የሌለው መኾኑን ተመራማሪዎች ያብራራሉ።

ቤቲና፣ ፑግራች እና የሁለት ዓመት ልጃቸው አኒታ

ቤቲና፣ ፑግራች እና የሁለት ዓመት ልጃቸው አኒታወላጆች ልጆቻቸውን የተለያዩ ቋንቋዎች እየተናገሩ እንዲያድጉ ማድረጉ ከተሳካላቸው ውጤቱን መመልከት እና ማዳመጥ እጅግ አስደማሚ ነው፤ ልክ እንደ ካታሪና። ካታሪና ገና የዓሥራ አንድ ዓመት ልጅ ናት ግን ሦስት ቋንቋዎችን አቀላጥፋ ትናገራለች። ስጳኝ፣ እንግሊዝኛ እንዲሁም ጀርመንኛ ተናጋሪዋ ካታሪና ከወላጆቿ ጋር ኮሎኝ ከተማ ውስጥ ትኖራለች።

የካታሪና እናት ማሪዛ የተወለዱት ኮሎምቢያ ውስጥ ነው። አባቷ ቮልፍጋንግ ጀርመናዊ ናቸው። መጀመሪያ ላይ ወላጆቿ ካታሪና ሁለት ቋንቋ እንድትማር ነበር ፍላጎታቸው። ማሪዛ በስጳኝ ቮልፍጋንግ ደግሞ በጀርመንኛ እያዋሯት ሊያሳድጓት ነበር ዕቅዳቸው። ማሪዛ እና ቮልፍጋንግ ግን ለመግባባት የሚነጋገሩት በእንግሊዝኛ ነው። እናም ይኽ በአንድ ወቅት ካታሪና ላይ የራሱን ተጽዕኖ አሳርፏል።

«የሦስት ዓመት ልጅ ሳለች አንድ የመባልእት መደብር ውስጥ ነበርን። እናም በጀርመንኛ እማ ይኸውልሽ የአፕል ፍሬ ማለት ጀመረችና ወዲያው በእንግሊዝኛ እዚህ ጋር ደግሞ ሙዝ አለ አለች። እናም ያኔ፦ ለካ እንግሊዝኛም መናገር ትችላለች፤ የምንናገረውን ለመረዳትም እንግሊዝኛ መናገር ትፈልጋለች አልኩ።»

በዚህ መልኩም ካታሪና ሦስተኛ አፍ መፍቻ ቋንቋ ከወላጆቿ ወረሰች ማለት ነው። የ11 ዓመቷ ልጅ በአሁኑ ወቅት ከሦስቱ ቋንቋዎች ከአንዱ ወደ አንዱ ስትቀያይር ያለ አንዳች ችግር ነው። ካታሪና የቋንቋ ተሰጥዖ ብቻ አይደለም ያላት ይላሉ እናቷ። ካታሪና አለመግባባት በሚከሰትበት ወቅትም መፍትኄ የመፈለግ ችሎታ አዳብራለች። እንደ ካታሪና ያሉ ልጆች አዕምሮዋቸው በርካታ ነገሮችን እንደየ ዘርፉ ለመተንተን የተፍታታ ነው። ካታሪና ከወላጆቿ በሦስት ቋንቋዎች መነጋገሯ ምን አይነት ስሜት ይሰጣታል?

«ይኼ ለእኔ የዓለም የመጨረሻው ትክክለኛው ነገር ነው። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በጀርመንኛ ብቻ ሲያወሩ ግራ ይኾንብኛል። ብቻ ለምን ያ እንደሚኾን እኔንጃ።»

እንደ ካታሪና በርካታ ቋንቋዎችን እየተማሩ የሚያድጉ ሰዎች ሌሎችን ሊያስቀኑ ይችላሉ። አዋቂ ከኾኑ በኋላ አንድን ቋንቋ ያለአንዳች ቅላጼ አለያም ዘዬ ለመማር ይከብዳል። እንዲያም ኾኖ ግን አንድ ነገር በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ተጨማሪ ቋንቋ መማር እና መናገር አዕምሮን ብቁ ያደርጋል፤ የትኛውም ዕድሜ ላይ ቢኾኑ ማለት ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic