በርሊን፤ የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል መግለጫ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 28.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

በርሊን፤ የመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል መግለጫ

የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሰሞኑን በደረሰዉ ጥቃት ምክንያት መንግሥታቸዉ እስካሁን ሥደተኞችን ለመርዳትና ለመቀበል የሚከተለዉን መርሕ እንደማይቀይር አስታወቁ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:53

አንጌላ ሜርክል

የጀርመን መንግሥት በሐገሪቱ ዉስጥ የሚጣሉ የሽብር ጥቃቶችን ለመከላከል አዳዲስ እርምጃዎችን እንደሚወስድ የሐገሪቱ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል አስታወቁ። በዛሬዉ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሀገሪቱ ዉስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር ጥቃቶች ከተሰነዘሩ በኋላ ተገቢዉን ርምጃ መዉሰዳቸዉን አስታወቁ። ሜርክል አክለዉም በተቃራኒ ይቆማሉ ያሏቸዉ አሸባሪዎች ጀርመን የዉጭ ዜጎችን ለማስጠጋት ያላትን ዝግጁነት ለመጉዳት መነሳታቸዉንም አመልክተዋል። ጀርመን ዉስጥ በተከታታይ በተለያዩ ስፍራዎች የደረሱት ጥቃቶች አስደንጋጭ፣ ከባድ እና አሳዛኝ እንደሆኑ የገለፁት ሜርክል፤ ጥቃቶቹ ማናቸዉም ሰዉ ሊገኝበት በሚችልበት ቦታ መድረሳቸዉንም ተናግረዋል። ርምጃቸዉም የኅብረተሰቡ ተከባብሮ የመኖር ባህል ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ነዉ ሜርክል ያመለከቱት፤

«አሸባሪዎች እኛ ጠቃሚ በሆነ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዳናደርግ ነዉ ያለሙት። እነሱ የፈለጉት አንድነታችንን እና አብሮነታችንን ለማጥፋት ነዉ። የፈለጉት የአኗኗር ስልታችንን፤ ግልፅነታችንን እና የተቸገሩትን ሰዎች ለመርዳት ያለንን ዝግጁነት ማደናቀፍ ነዉ። በባህሎች መካከል እንዲሁም በሃይማኖቶች መካከል ጥላቻ እና ፍርሃትን ይዘራሉ።»

ከዚህም ሌላ ሜርክል ጀርመን ይህን ፈታኝ ወቅት መርሆዎቿን አፅንታ በመያዝ እንደምትወጣዉም በንግግራቸዉ አፅንኦት ሰጥተዋል። ባለፈዉ ሳምንት ዓርብ ሙኒክ ከተማ በገበያ ማዕከል ዉስጥ እና አካባቢዉ የተገደሉትን ለማሰብ የፊታችን እሑድ በተዘጋጀዉ ሥነስርዓት ላይም እንደሚገኙም አመልክተዋል።

 

ሜርክል፤ ሰሞኑን ደቡባዊ ጀርመን ዉስጥ አደጋዎች ከተጣሉ በኋላ ዛሬ በሠጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተመሳሳይ ጥቃቶችን ለመከላከል ይረዳል ያሉትን ባለ-ዘጠኝ ነጥብ ዕቅድ ይፋ አድርገዋል። ሜርክል ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ በፈጀዉ ጋዜጣዊ መግለጫቸዉ እንዳሉት ሰሞኑን በደረሰዉ ጥቃት ምክንያት መንግሥታቸዉ እስካሁን ሥደተኞችን ለመርዳትና ለመቀበል የሚከተለዉን መርሕ አይቀይርም። ሥለ መግለጫዉ የበርሊን ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤልን በስልክ አነጋግሬዉ ነበር።

ይልማ ኃይለ ሚካኤል

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic