በርሊን፥ በዐሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ጀርመን ገቡ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 06.09.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

በርሊን፥ በዐሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ጀርመን ገቡ

6000 ገደማ ስደተኞች በሐንጋሪ እና ኦስትሪያ በኩል እሁድ ጳጉሜ 1 ቀን 2007 ደቡብ ጀርመን መግባታቸው ተገለፀ። ፖሊስ በጠቅላላው 10,000 ግድም ስደተኞች ዛሬ ሙኒክ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል ብሏል። የኦስትሪያ የባቡር ድርጅት ቅዳሜ ዕለት ከሐንጋሪ የመጡ 11 000 ገደማ ስደተኞች ወደ ጀርመን የሚጓዙበትን መንገድ ማመቻቸቱን አስታውቆ ነበር።

ስደተኞች የመጡት ከሶሪያ፣ አፍጋኒስታን እና ኢራቅ እንደሆነ ተናግረዋል። የጀርመን የድንበር ፖሊስ ትናንት እና ዛሬ ብቻ በጠቅላላው 17 000 የሚደርሱ ስደተኞች ጀርመን ይገባሉ ብሎ እንደሚገምት አስታውቃል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል ስደተኞች ጀርመን ሊገቡ የቻሉት ሐንጋሪ ውስጥ ዓርብ ሌሊት ከስደተኞች ጋር በተነሳው ቀውስ ምክንያት ሐንጋሪ ስደተኞቹን ወደ ፈለጉት ሀገር እንዲሄዱ እንድትፈቅድላቸው ጀርመን እና አውስትሪያ በመስማማታቸው ነው

ከሐንጋሪ የተነሱ በሺህዎች የሚቆጠሩ አብላጫ ሶሪያውያን ስደተኞች ቅዳሜ እለተ ኦስትሪያ እና ጀርመን ድንበር መግባታቸው ተዘገቦ ነበር። ከሐንጋሪ ጋር በምትዋሰነው የኦስትሪያ የድንበር ከተማ ኒኬልስዶርፍ እስከ ቅዳሜ ነሐሴ 30 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. ከሠዓት ድረስ 6500 ስደተኞች መድረሳቸው ተገልጧል።

የኦስትሪያ ባለሥልጣናት እስከ10,000 የሚደርሱ ስደተኞች ወደ ድንበራቸው መዝለቃቸውን እንደሚጠብቁ ቅዳሜ አስታውቀዋል። ስደተኞቹ በሐንጋሪ ቡዳፔስት ዋናው ባቡር ጣቢያ እንዳይንቀሳቀሱ ለቀናት ከተከለከሉ በኋላ ዓርብ ማምሻውን ነበር ወደ ኦስትሪያ ድንበር በእግራቸው ማቅናት የጀመሩት።

የስደተኞቹ ቀውስ በአውሮጳውያን መካከል ክፍፍልን ፈጥሯል። ጀርመን ስደተኞቹን «በደለኛ» አድርጎ መውሰዱ ይቅር ስትል ብሪታንያ በሺህዎች የሚቆጠሩ የሶሪያ ስደተኞችን እቀበላለሁ ማለቷ ተሰምቷል። ጀርመን ይመጣሉ ብላ ከምትጠብቃቸው 10,000 ስደተኞቹ መካከል 1,000 ያኽሉ ወደ ግዛቷ መግባታቸው ዛሬ ተጠቅሷል።

የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር በአውሮጳ የተከሰተው የስደተኞች ቀውስ የአውሮጳ ኅብረት ልዩ ጉባኤ ሊጠራለት ይገባል አሉ። የአውሮጳ ኅብረት ሃገራት ርእሳነ-ብሔር እና ጠቅላይ ሚንስትሮች በአንድ ወር ውስጥ ተገናኝተው መወያየት አለባቸው ሲሉ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ ከሉግዘምቡርግ አሳስበዋል። ይኽ የውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ ሐሳብ ከአንድ ሣምንት ግድም በኋላ ሰኞ ዕለት በሚከናወነው የኅብረቱ ጉባኤ የሚወሰን መሆኑም ተገልጧል። የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ስደተኞችን በኅብረቱ አባል ሃገራት የማከፋፈሉን ዕቅድ አንዳንድ የኅብረቱ አባል ሃገራት እስከአሁን አልተቀበሉትም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ልደት አበበ