1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በራያ አላማጣ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለዉ አፈና መዋከብ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 20 2016

የወሎ አማራ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ በበኩላቸው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ “ከአንዳንድ የራያ አላማጣ ከአካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች እንዲወጡ ይደረጋል” በሚል ሰሞኑን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ያስተላለፉትን መልዕክት አይቀበሉትም

https://p.dw.com/p/4gO43
የልአላማጣ ከተማ በከፊል
የልአላማጣ ከተማ በከፊልምስል Fikru Eshsiebel

በራያ አላማጣ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለዉ አፈና መዋከብ

የማንነት ጥያቄ ባለባቸው የራያ አላማጣ አካባቢዎች መዋከብና መታፈን እየጨመረ መምጣቱን የወሎ አማራ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴና ነሪዎች አመለከቱ፣ በቅርቡ በተከሰተው ግጭት ምክንት የጤና ተቋማት ሥራ በማቆማቸው የእናቶችና ህፃናት ህይወት ማለፉንም አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፣ ሰሞኑን “የትግራይ ኃይሎችን ከአለማጣ አካባቢ እናስወጣለን” የተባለውም  ሀሰት መሆኑን ነው ነዋሪዎቹና የአላማጣ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር የገለፁት፡፡

 ከሚያዝያ 2016 ዓ ም አጋማሽ ጀምሮ የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያቀርቡባቸው የራያ አላማጣ አካባቢዎች ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ የግጭቱ መነሻ ደግሞ የተግራይ የፀጥታ አካላት ሁለቱ ወገኖች የይገባኛል ጥያቄ ወደሚያነሱባቸው አካባቢዎች በኃይል መግባታቸውን ተከትሎ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይገልፃሉ፡፡

ሰሞኑን የትግይ ጊዜያዊ አስተዳደር መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ ኃይሎቻቸውን አላማጣ አካባቢ ካሉ ቦታዎች እናስወጣለን ያሉትን ተከትሎ አንድ የጋርጃሌ ከተማ ነዋሪ በሰጡት አስተያየት የተባለው ነገር ሀሰት እንደሆነና በተቃራኒው ኃይል እየተሰባሰበ ነው ብለዋል፣ አንዳንድ ሰዎችም ታፍነው ተወስደዋል ነው ያሉት፡፡
ሌላ አስተያየት ሰጪም የትግራይ ኃሎች እንዲያውም ሰሞኑን ሌሎች አዳዲስ ቦታዎችን በኃይል ተቆጣጥረዋል ሰዎችንም ወስደዋል ብለዋል፡፡ በተለይ አላማጣ አካባቢ አየር ሜዳ ወደ ተባለ አካባቢ ሰሞኑን አዳዲስ ቦታዎችን በኃይል ይዘዋል ብለዋል፡፡

የአላማጣ ከተማ በከፊል
የአላማጣ ከተማ በከፊልምስል DW

የወሎ አማራ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢና የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኃይሉ አበራ በበኩላቸው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ “ከአንዳንድ የራያ አላማጣ ከአካባቢዎች የትግራይ ኃይሎች እንዲወጡ ይደረጋል” በሚል ሰሞኑን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ያስተላለፉትን መልዕክት አይቀበሉትም፣ “ዓለምአቀፉን ማህበረሰብ ለማደናገር የተደረገ ጥረት ነው” ብለውታል፡፡

የትግራይ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ዘረፋና ወከባ ተጠናክሮ ቀጥሏል ሲሉ አቶ ኃይሉ ይከስሳሉ፣ የጤና ተቋማት በሙሉ አቅማቸው መስራት ባለመቻላቻው፣ የእናቶችና የህፃናት እለፈ ነው ብለዋል፤ 60 ሺህ ያክል ተማሪዎች ደግሞ ከትምህርት ውጪ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ከሚያዝያ አጋማሽ ወዲህ ብቻ በህክምና እትረት ብቻ 4 እናቶችና 8 ህፃናት ህይወታቸው ማለፉን ተናግረዋል፡፡

በኦፍላ ወረዳ 6 ሰዎች ታፍነው ወደ ትግራይ መወሰዳቸውን አቶ ኃይሉ አስረድተዋል፣ የመከላከያ ሰራዊትና ፌደራል ፖሊስ አካባቢው እንዲረጋጋና ችግሮች እንዳይፈጠሩ ጥረት ቢያደርጉም በገጠሩ የአስተዳደሩ አካባቢዎች ብዙ ጉዳቶች እየደረሱ እንደሆነ ነው ያብራሩት፡፡

በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው ስምምነት የትግራይና የአማራ ክልሎች የሚወዛገቡባቸው አካባቢዎች ህገመንግስቱን መሰረት በማድረግ በህዘበ ውሳኔ መፍትሄ የሚያገኝ እንዲሆን የሚያሳስብ ነው፡፡

የተግራይ  የፀጥታ አካላት አደረሱት ስለተባለው ጉዳይ  ተጨማሪ አስተያየት ለማግኘት ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ኃለፎም በእጅ ስልካቸው ብደውልም ሆነ አጭር የፁሁፍ መልዕክት ብልክ ምላሽ አላገኘሁም በተመሳሳይ ለአማራ
ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ያደረግሁት የስልክ ጥሪ መልስ አላገኘም፡፡

ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ 
እሸቴ በቀለ