በሩር ፣ ከተሞችን ፣ በዘመናዊ ሥነ-ቴክኒክ ለማልማት የሚደረገው ውድድር፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 03.11.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በሩር ፣ ከተሞችን ፣ በዘመናዊ ሥነ-ቴክኒክ ለማልማት የሚደረገው ውድድር፣

ለብዙ ዘመናት ፣ በድንጋይ ከሰል የማዕድን ቁፋሮና አቅርቦት የታወቀው በሰሜን ምዕራብ ጀርመን የሚገኘው ሩር በመባል የታወቀው አውራጃ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በባህል፣ በሳይንስና ሥነ ቴክኒክ አዲስ ፈር የመቅደድ ዝንባሌም ሆነ እንቅሥቃሴ እየታየበት ነው።

default

የዘንድሮ የአውሮፓ የባህል መዲና በተሰኘችውና፤ በዘመናዊ ሥነ-ቴክኒክ፣ ከተሞችን ለማልማት ከተወዳደሩት 5 የሩር አውራጃ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው በ ኤሰን የሚገኝ፣ የቀድሞ ድንጋይ ከሰል ማውጫ ጣቢያ፣

«ኤሰን» በተባለችው በሩር አውራጃ ከተማና በታኅታይ ሳክሰኒ(ኒደርዛኽሰን) ፌደራል ክፍለ ሀገር ዋና ከተማ ሃኖፈር ትብብር፣ ትናንት ፣ «የጋራ የወደፊት ዕጣ-ፈንታችን» በሚል መፈክር ዓለም አቀፍ ጉባዔ፣ የተከፈተ ሲሆን ስብሰባው እስከ ፊታችን ቅዳሜ ይዘልቃል። ይህ ስብሰባ ፣ «ሩር 2010 » በሚል መሪ ቃል ፤ በሩር አውራጃ የሚገኙ ከተሞች ራሳቸውን የሳይንስና የባህል ማዕከላት ለማድረግ የተነሳሱበትን ዘመቻ መለስ ብሎ የሚቃኝም ነው። የጀርመን የትርዒት ማሳያ ማዕከል ፣ ከፎልክስቫገንና ሜርካቶር ከተሰኘው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጋር በመተባበር ፣ በመጀመሪያዎቹ 3 ቀናት በሃኖፈር የትርዒት ማሳያ አዳራሽ፣ ከዚያም ዓርብና ቅዳሜ በሩር አውራጃ በኤሰን ከተማ የተጠቀሰውን ዐቢይ ጉባዔ ያካሂዳል። ከሳይንስ ፣ ከፖለቲካ ና ከባህል ከተውጣጡ 500 ያህል ጠበብት ሌላ፤ ጥቂት የተመረጡ ታዳጊ ተመራማሪዎችም ይሳተፋሉ።

የጉባዔው ተሳታፊዎች ከሚያተኩሩባቸው ዋና-ዋና ጉዳዮች መካከል፣ የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ፤ የኃይል ምንጭ፣ የወደፊቱ ሥነ ቴክኒክ፣ ሳይንሳዊ የልማት ዕድገት፣ የአቅድ ለውጥ፣ ጤና አጠባበቅ፣ ሰብአዊ መብትና ዓለም አቀፍ እሴቶች፣ የሚሉት ይገኙበታል። እስከ ቅዳሜ በሚቆየው ዐቢይ ጉባዔ፣ የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት (ቡንደስታኽ) ፕሬዚዳንት፣ ኖርበርት ላሜርት፣ ቀድሞ፣ የተባበሩት መንግሥታት የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ መርኀ-ግብር ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ክላውስ ቶዖፈር የጀርመን ህገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አንድሪያስ ፎስኩለ፣ በጀርመን ሀገር የውጭ ተወላጆች ተዋህደው የሚኖሩበትን ሁኔታ የሚያጠኑት ክላውስ ጄ ባደ እንዲሁም ዩ ኤስ አሜሪካዊው የሃይማኖት ጉዳዮች ምሁር ፊሊፕ ጀንኪንስ በመገኘት ንግግር ያሰማሉ ተብሎም ይጠበቃል።

በዛ ካሉት የሩር አውራጃ ከተሞች መካከል ፤ 16 ተወዳድረው 5 ብቻ፤ ማለትም፣ ቦኹም፤ ቦትሮፕ፣ ኤሰን፤፤Gelsenkirchen/Herten እንዲሁም በሩር ወንዝ ዳር የምትገኘው ሙዑልሃይም ናቸው ለፍጻሜ ውድድር የቀረቡት ። ከእነዚህ መካከል አሸናፊው ከተማ የትኛው እንደሚሆን ፤ ነገ ይገለጣል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ለውድድር ብቁ ነው የተባለው ከ 50 ሺ ያናነሰ ኑዋሪ ያለው ከተማ ፤ ወይም ያን ያህል ኑዋሪዎች ያሉት የአንድ ከተማ ከፊል ነው። ተወዳዳሪዎቹ ፣ እጅግ ዘመናዊ በሆነው ሥነ ቴክኒክ ለመገልገል የተዘጋጁ፣ የተቃጠለ የአየር መጠንን (CO2) ግምሽ በግማሽ ለመቀነስ የተሟላ ዝግጅት ያደረጉ መሆን አለባቸው። እንዲህ ዓይነቱ ውድድር እንዲካሄድ ያበቃው፣ የሩር አዲስ አቅድ አስተዋዋቂ፣ የተሰኘው፣ ከ 60 መለስተኛና ታላላቅ ኢንዱስትሪ ኩባንያዎች የተውጣጣ ማኅበር ነው።

የታሰበውን ፣አዲስ ፣ ለተፈጥሮ አካባቢ ፍጹም ተስማሚ የሆነ ከተማ ለማደራጀት ፣ አዲስ ቴክኒክ ፤ ቁሳቁስ፤ የገንዘብ አቅምና የመሳሰለው የግድ ተፈላጊ ነው። ስለሆነም በአሸናፊነት የሚመረጠው ከተማ በሚመጡት 10 ዓመታት፣ 2,5 ቢሊዮን ዩውሮ ገንዘብ ሥራ ላይ በማዋል፤ አቅዱን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል። «ሻልከ 04 » በሚል ስያሜ የሚታወቀው የጀርመን የአንደኛ ምድብ የአግር ኳስ ክለብ የሚገኝባት ከተማ Gelsenkirchen ተጣማሪ ከሆነችው ከሄርተን፣ ወደ ቦትሮፕና ግላድቤክ፣ ሁለት መለስተኛ አውቶቡሶች ይመላለሳሉ። አውቶቡሶቹ የሚንቀሳቀሱት በመደበኛ ቤንዚን ወይም ዲዜል ሳይሆን በሃይድሮጅን ጋዝ ነው። የሃይድሮጅን ጋዙን የሚሞሉት ቀድሞ የደንጋይ ከሰል ማዕድን ማውጫ በነበረው Zeche Ewald በተሰኘው ጣቢያ ነው። በዚያ ጣቢያ ፣ የሃይድሮጅን ጋዝ የሚመረትበት ከፍተኛ የሥነ ቴክኒክ ማዕከል ተቋቁሟል። ሄርተን እንግዲህ በዚህ በመመካት ነው ከተጣማሪዋ ጌልዘንኪርኸን ጋር ለሩር አውራጃ የአዲስ ከተማ አያያዝ መሪም ሆነ አርአያ እሆናለሁ ብላ ለውድድር የተዘጋጀች። ከነፋስ ኃይል ከሚገኝ የኤልክትሪክ የኃይል ምንጭ ሌላ፤በሃይድሮጂን ጋዝ የሚንቀሳቀሱ የቤት መኪናዎችና አውቶቡሶች፣ ብስክሌቶች ጭምር፣ ሄርተንን በሚመጡት 10 ዓመታት ልዩ ገጽ እንደሚፈጥሩላት የተወዳዳሪዎቹ ባለስልጣናት ጽኑ ተስፋና እምነት ነው።

ቦትሮፕ፣ በዚያ በሚገኘው የፍራውን ሆፈር የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃና የአስተማማኝ ቴክኒክ ማዕከል እርዳታ፣ የከተማይቱን አያያዝ በዘመናዊና ጤናማ አቅድ ማደስ እንደሚቻላት የምትገልጸው። መኖሪያ ቤቶችንም ፤ በትኅተ ምድር 1000 ሜትር ጥልቀት በሚወጣ ሞቃት ድንጋይ ማሞቅ የሚቻልበት ቴክኒክ መኖሩን ማሳየቷ አልቀረም። ከተጠቀሰው የተፈጥሮ አካባቢና አስተማማኝ ቴክኒክ ተቋም ዮሰፍ ሮበርት የተባሉት እንዲህ ብለዋል።

«በየዕለቱ ፣ 15,000 ኩብሜትር ይሞላል ፤ይህም በጣም ብዛ ያሉ ቤቶችን ለማሞቅ በቂ ነው። ከጠጠርም ሆነ ድንጋይ የሚገኘውን ሙቀት ወደ ቤቶች ማስተላለፍ ይቻላል። እርግጥ ሙቀቱን ለማስተላለፍና ደረጃውን ከፍ ለማድረግ፤ የሙቀት «ፓምፕ» ያስፈልጋል። »

በድንጋይ ከሰል መጠቀም ከቆመ በኋላ፣ ቤትን እንዴት ማሞቅ እንደሚቻል የሳይንስ ጠበብቱ ማሰብ ማሰላሰላቸው አልቀረም። 64 ሄክታር ቦታ በሚሸፍነው ከከርሰ ምድር ተዝቆ በሚከማቸው የቀዘቀዘ ጠጠርም ሆነ የተፈጥሮ ጡብ በፀሐይ ኃይል ኤልክትሪክ ማመንጨት የሚቻልበት ጣቢያ መገንባት አያዳግትም። ከፀሐይም ሆነ ጥልቀት ካለው ከርሰ ምድር ከሚወጣ ድንጋይ የሚገኝ ሙቀትንም ሆነ የኃይል ምንጭን በነጻ ማግኘት ይቻል ይሆናል፤ ነገር ግን፤ ለእያንዳንዱ ቤት ለማከፋፈል የሚያስፈልገውን ወጪ መክፈል አይቀሬ ነው። ግን ማን ይሆናል የሚከፍለው? ይህ ነው በአሁኑ ጊዜ ብዙ ነገሮችን በዘመናዊ አቅድ ለመያዝ በሚወሰዱ እርምጃዎች፤ ገንዘቡ ከየት ይመጣል? የሚለውን ጥያቄ የሚያስከትለው። በሩር የሚገኙ ከተሞችን በዘመናዊ አቅድ ለማልማት ንድፍ የቀረበው በጋራ ፕሮጀክት አማካኝነት ነው። የሄርተን ከተማ ከንቲባ፣ ዑሊ ፔትስሰል--

«ፕሮጀክቱ እንዲጠነሰስ ያበቁት ፣ ለሩር አውራጃ ከተሞች ልማት ሃሳብ ያቀረቡት ትልልቆቹ የኢንዱስሪ ኩባንያዎች ድርሻቸውን ይከፍላሉ። የግል ባለንብረቶችም ይሳተፋሉ። ከመንግሥትም በኩል፣ ገንዘብ ሥራ ላይ የሚውልበት መረብ ሳይዘረጋ አይቀርም። እናም ፣ አዲስ ሞዴል ነው ሠርተን የምናሳየው። በኮንትራትም ሆነ በበጎ አድራጎት፣ ወይም በደቦ በመሳተፍ ከተማን ለማልማት በሚወሰደው እርምጃ፣ ባንኮችም ቢሆኑ፣ ከመቶ የተወሰነ እጅ ትርፍ የሚገኝበትን ፣ በዚህ ረገድ ገንዘብን ሥራ ላይ የሚቻልበትን ሁኔታ ችላ አላሉትም። እኛም ብንሆን፣ ቀንበሩ አቅመ ደካሞች በሆኑ ዜጎች ትከሻ ላይ እንዲያርፍ አንፈልግም። ገንዘብን በአግባቡ ሥራ ላይ በማዋል፣ በዘመናዊ ሥነ ቴክኒክ በመጠቀም፣ አለን እንተባበራለን፣ የሚሉትን ነው የምንፈልገው። የኃይል ምንጭይከፈልበታል። ይሁንና በቁጠባ በሚያዝ የኃይል ምንጭ ፤ ገንዘቡ ሥራ ላይ እንዲውል እናደርጋለን። ያለን ዋና ገንቢ ሐሳብ ይኸው ነው።»

አንድን ከተማ ሙሉ-በሙሉ ለማደስ የኑዋሪዎችን በጎ ፈቃድ ይጠይቃል። አንዳንዶች፤ ከታደሰ የቤት ኪራይ ይጨምርብናል ብለው ይሠጋሉ። ወይም አካባቢአቸው እደሳውን ማካሄድ እንደማይቻለው ይሰማቸዋል። ለዚህም ነው፤ በቦትሮፕ የመጀመሪያው ቅስቀሳ ነክ ዘመቻ የተካሄደው። ቦትሮፕ እርግጥ ነው የ20ሺ ሰዎችን ፊርማ ለማሰባሰብ በቅታለች። ኤሰን የጎዳና የምርጫ ዘመቻ የማካሄድ እቅድ ነው ያላት። በቦኹም ኑዋሪዎች በየአጥቢአቸው እየተሰባሰቡ እንዲመክሩ ተደርጎአል። በመሠረቱ፤ የተወሰኑ ህንጻዎችን ቀለም ለመቀባት ወይም አሮጌ የቤት ማሞቂያ መሣሪያዎችን መለወጥ አይደለም ዋናው ቁም ነገር!ከዚያ የላቀ የተስተካከለ ህይወት መምራት የሚቻልበትን ፤ ጤናማ አመጋገብ የሚኖርበትን ፣ አቋራጭ መንግዶች የሚሠሩበትን ፣ ከሩቅ የሚያገናኝ የሥራ መስኮች የሚዘረጉበትን፣ መኖሪያ ቤቶችም ሱቆችም አምረው የሚሠሩበትን ጽንሰ ሐሳብ ነው ተፎካካሪዎቹ አንግበው የተነሱት።

በሩር ወንዝ ዳር በምትገኘው ሙዑልሃይም፤ በጀርመን ሀገር በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የተቃጠለ አየር (CO2) ልቀት ፍጹም የሌለበት የገበያ አዳራሽ ተሠርቷል። የፀሐይን ጨረር ወደ ኤልክትሪክ ኃይል መለውጥ የሚችል ጣራ፤ የምድርን ሙቀት አጠራቅሞ መጠቀም የሚችል፤ በነፋስ ኃይል በሚሽከረከሩ ግዙፍ ፉሪቶች፣ የኤልክትሪክ ኃይል የሚያጠራቅም፤ የራሱ ልዩ የመብራት አምፑሎች ያሉት፣ ሞቃትና ቀዝቀዛ አየር እንደአስፈላጊነቱ የሚለዋውጥ ሥርዓት ያለው ነው የተሠራው የገበያ አዳራሽ!

ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ፣ በሩር አውራጃ ከሚገኙት በዛ ያሉ ከተሞች 16 ቢወዳደሩም ለፍጻሜ ውድድር የተመረጡት 5 ናቸው ፣ ከ 5 ቱ ደግሞ አንደኛ የሚወጣው ነገ ይለይለታል። ታዲያ የተቀሩት ከተሞች ሁሉ፣ በዘመናዊ ሥነ ቴክኒክ በመታገዝ መኖሪያቸውን ለማልማት የቀረበውን ሐሳብና ፕሮጀክቱን አቋርጠው ይተውታል? ወይስ ይገፉበታል? እርግጥ ነው የተጠቀሱትና ያልተጠቀሱት ከተሞች ሁሉም በቂ ገንዘብ ያላቸው ናቸው ማለት አይቻልም። ተወዳዳሪዎቹ የሆነው ሆኖ፣ በአንድ ቃል ይስማማሉ። እርሱም፣ ገንዘብ ኖረንም አልኖረንም፤ ከተሞቻችንን በዘመናዊ ሥነ ቴክኒክ እገዛ ለማልማት እንነሣ ! የሚል ነው። የቦትሮፕ ከተማ ዋና ቀያሽ መሃንዲስ ፣ ወ/ሮ ክሪስትና ክላይንሃይንስ እንዲህ ይላሉ።

«እኛ ሁላችን፣ እንዳሸነፍን ነው የሚሰማን። ብዙ ፕሮጀክቶችን ብዙ ሐሳቦችን ይዘን ከመቅረባችንም፣ በተለያዩ ኩባንያዎችና በከተማዎቹ መስተዳድር መካከል የመገናኛ የመወያያ መረብ ዘርግተናል። ይህም ያላንዳች ጥርጥር ይቀጥላል።»

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ