በረራና ሬደር | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 19.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

በረራና ሬደር

የካቲት 29 ቀን 2006 ዓ ም፤ (08 03 2014) ከደቡብ ምሥራቅ እስያዊቷ ሀገር ማሌሺያ 239 መንገደኞችን አሣፍሮ ወደ ቤይጂንግ ጉዞ የጀመረ አኤሮፕላን፣ አቅጣጫውን ድንገት ለውጦ ከተመለሰ በኋላ እስካሁን እምን እንደገባ በይፋ ያልታወቀበት ሁኔታ

መላውን ዓለም እንዳስደመመ ይገኛል። ከአየርም ከየብስም ፤ የአኤሮፕላኑን ጉዞ መቆጣጠር ባያቅትም ፤ ከሬዳር ጋር የሚያገናኘው መሥመር ሆን ተብሎ በመሠናከሉም ሆነ በመዘጋቱ በቀጣይ የበረራ ሰዓቶች አኤሮፕላኑ የደረሰበትን ለማወቅ ሳይቻል ቀርቷል። በሬዳር ከየብስ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ጋር ግንኙነት ተቋረጠ ማለት፤ ከአየር ትራፊክ ጋር የመጋጨት አደጋ እንዳያጋጥም የተመደበ መሥመር ጠብቆ መብረር የሚቻልበት ሥርዓትም Traffic collision avoidance system (TCAS) (TEE-KAS) ወይም Traffic alert and collision avoidance system ተፋለሰ ማለት ነው። አየር ላይ አኤሮፕላኖች እርስ በርስ እንዳይጋጩ፣ መልእክት አስተላላፊና ተቀባዩ ልዩ ራዲዮ መሰል መሣሪያ «ትርንስፖንደር» ፤ ከአየር ትራፊክ ቁጥጥር ጣቢያ በተጨማሪ አደጋን ለመከላከል ያገለግላል። ማንኛውም ከ 5,700 ኪሎግራም በላይ ዕቃ የሚጭን ወይም ከ 19 nበላይ ሰዎች ማሣፈር የሚችል አኤሮፕላን ሁሉ፣ ትራንስፖንደር ሊኖረው እንደሚገባ ሥልጣን ያለው ዓለም አቀፉ የሲቭል በረራ ድርጅት ያስገድዳል። ታዲያ፣ በዘመናዊው የበረራ ደንብ ፣ APP(Approach Control) በመብረር የሚጠጋ ወይም የሚጠጉ አኤሮፕላኖችን መቆጣጠሪያ በሆነው ስልት ከአደጋ መከላከል የተለመደ ነው።

ታዲያ በአሁኑ ዘመን ካንድ ሀገር ወደ ሌላው ከአንድ ከተማ ወደሌላው የሚበር

አኤሮፕላን ፤ በአየር በረራ የያዘው መስመር፤ ከባህር ልክ በላይ ምን ያህል ኪሎሜትርም ሆነ ጫማ ከፍታ እንደሚገኝ ፣ ምን ያህል ፍጥነት እንዳለው፤ ከመነሻው እስከመድረሻው ምን ያህል ጊዜ እንደሚወስድበት፤ ይህንና ይህን የመሳሰለውን መረጃ በሚገባ ነው የሚያቀርበው። የአንድን የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላን ፣ የሩቁን አቅርቦ በሚያሳይ መነጽር (ባይኖኩላር፤ ካሜራን በመሳሰለው ይከታተሉ የነበረበት ዘመን ሩቅ አይደለም። በአሁኑ ዘመን ግን፤ በዲጂታል ካሜራ ላፕቶፕ በመሳሰለው ከተራራ በላይም ሆነ ደመናን ሰንጥቆ የሚበር አኤሮፕላንን፣ ዓይነቱንና የሚበርበትንም አቅጣጫ ማወቅ አስቸጋሪ አይደለም። በዘመናዊ የእጅ ስልኮች ፣ «ስማርትፎንስ ወይም «ታብሌትስ»ም አንድን አኤሮፕላን መነሻና መድረሻውን፣ ፍጥነቱን፤ ከምድር ያለውን ከፍታና የመሳሰለውን ለይቶ በማወቅ ሂደቱን መከታተል ይቻላል ---«ሬዳር ስፖቲንግ» በሚሰኘው ዘዴ ማለት ነው። አኤሮፕላኖችን ብቻ ሳይሆን ፤ በሰፊው ውቅያኖስ የሚቀዝፉትን ትልልቅና ትንንሽ መርከቦችንም ለይቶ መከታተል ይቻላል።

ከሰሞኑ በመገናኛ ብዙኀን የመወያያ አርእስት ሆነው ከሰነበቱት መካከል አንዱ በመግቢያችን ላይ እንደጠቆምነው ፤ ደብዛው ጠፍቶ እስካሁን ያልተገኘው የማሌሺያው የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላን ቦይንግ 777 ነው። ከጠፋ ዛሬ 11 ቀን የሆነውን አኤሮፓልን ፈልጎ ለማግኘት ታዲያ፤ (ማለት የት እንደወደቀ) ለማወቅ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ 3 ሚሊዮን ህዝብ በአንድ የሳቴላይት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት በኩል በፍለጋ መረባረብ ጀምሯል።

«ዲጂታል ግሎብ» የተባለው የሳቴላይት ኩባንያ እንዳስታወቀው፤ በ 24 ሺ ካሬ ኪሎሜትር ቦታ በተለይም በህንድ ውቅያኖስ አሰሳ ጀምሯል። ከዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ጋር በቀጥታ ግንኑነት ያለውና ያለማቋረጥ ተባብሮ የሚሠራው ዲጂታል ግሎብ፤ ከ 5 ጥራት ያለው ምስል ከሚያሳዩ ሳቴላይቶቹ የሚገኘውን መረጃ፤ በኮምፒዩተር እንዲቀርብ ያደረገ ሲሆን፤ ባለፈው ኅዳር በፊሊፒንስ ሐያን የተባለው ኃይለኛ አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ማዕበል በሰውና ንብረት ላይ ብርቱ ጥፋት ባደረሰበት ወቅት ለርዳታ ከተረባረበው የላቀ ህዝብ አሁን በሰፊው አኤሮፕላን ፍለጋ ላይ ተሠማርቷል ሲል ነው ያስታወቀው።

በበጎ ፈቃደኝነት በፍለጋ ላይ ከተሠማሩት መካከል አንዳንዶች እንደሚሉት ከሆነ ሳቴላይቶቹ ያልተቋረጠ የቪዲዮ ምስል እንደሚያቀርቡ የአሰሳ ካሜራዎች ሳይሆን አልፎ- አልፎ የተነሱ ፎቶግራፎችን ነው ኮምፒዩተር ላይ ለእይታ ያቀረቡት። በአንዲህ ዓይነት አሰሳ የጠፋውን አኤሮፕላን ማግኘት ከተቻለ ትልቅ ነገር ነው።

በዛሬው ዕለት ፤ ከታይላንድ የተገኘው አዲስ የሬዳር መረጃ ፤ አኤሮፕላኑ የተጓዘበትን መሥመር መልሶ መመልከት እንደሚቻል ፍንጭ ሰጥቷል። ከ 26 አገሮች የተውጣጡ በቡድን የተደራጁ አፈላላጊዎች በተለያዩ ኣኤሮላኖች ከፔርዝ፦ አውስትሬሊያ በስተደቡብ ምዕራብ ፤ ሕንድ ውቅያኖስ ውስጥ 305,000 ካሬ ኪሎሜትር ስፋት ባለው ባህር አሰሳቸውን ቀጥለዋል። የንግድ መርከቦችም ያዩትን እንዲጠቁሙ ተጠይቀዋል።

የታይላንድ ወታደራዊ ባለሥልጣናት እንዳሉት አንድ ምንና የማን መሆኑ ያልታወቀ አኤሮፕላን፤ በማላካ የባህር ሠርጥ አካባቢ ተመልክተው ነበር። ይህም የሆነው የማሌሺያው የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላን ትራንስፖንደር ምልክት መጥፋቱ በታወቀ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ነበረ። አሁን የማሌሺያ መርማሪዎች የሚያደርጉት፤ የሀገራቸው ጦር ኃይልና የታይላንድ መከላከያ ኃይል የመዘገቡትን የሬደር መረጃ ማመሣከርና፤ የአይሮፕላኑን የበረራ አቅጣጫ አገናዝቦ ፣ ፍለጋ የሚካሄድበትን አካባቢ ማጥበብ ነው። ቀደም ሲል የማጓጓዣ ጉዳይ ሚንስትሩ ሂሻሙዲን ሁሴን፤ እንዲህ ማለታቸው የሚታወስ ነው።

«ለፍለጋ የተሠማረንበትን ቦታ በአርግጥ አሥፍተነዋል። የአሰሳው ስልትም ተቀይሯል። እስካሁን በባህር ላይ ብቻ ነበረ ያተኮርነው።አሁን ግን 11 ሃገራትን የአሰሳው ክፍል ማድረግ ሊኖርብን ነው። MH 370 ፣ የ ቦይንግ 777 የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላ በረራ እነዚህን አገሮች አቋረጦ ሊሆን ይችላል። 25 አገሮች በፍለጋው በማገዝ ላይ ናቸው።ይህ ደግሞ ለአስተባባሪው ክፍል ተግዳሮት ነው።»

ከኩዋላሉምፑር ተነስቶ የሁለት ሰዓት በረራ ካደረገ በኋላ ከሬዳር በተሠወረው የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላን ውስጥ ሁለት በተሠረቀ ፓስፖርት የሚንቀሳቀሱ ሰዎችም እንደነበሩ በተደጋጋሚ ተነግሯል። ፓስፖርቶቹ ከ 2 ዓመት በፊት ታይላንድ ውስጥ የተሠረቁ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል። የተሠረቁት ፓስፖርቶች የአንድ ኦስትሪያዊና የአንድ ኢጣልያዊ መታወቂያ ሰነዶች ነበሩ ተብሏል። ልዊጂ ማራልዲ የተሰኘው ኢጣልያዊ፣ በመጨረሻ ለታይላንድ ባለሥልጣናት ይህን ብሎ ነበር።

«አንድ ወዳጄ በ SMS ጽፎ ደህና መሆኔን ፣ በሕይወት የምገኝ ስለመሆኔ ጠየቀኝ። በዚህ ጊዜም ነው ስለአውሮፕላኑ መጥፎ ዕጣ የሰማሁ። ስሜ ከተሳፋሪዎች ሥም ዝርዝር ውስጥ እንደነበረበት ተገነዘብሁ»።

የማሌሺያው የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላን የተለያዩ ምላ ምቶች እንደሚጠቁሙት ያጋጠመው አደጋ ሳይሆን ፤ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በአብራሪው ወይም በሌላ አኤሮፕላኑን በቁጥጥር ስር ባደረገ ሰው፣ የደባ ተግባር ነው የተፈጸመበት። እ ጎ አ በ 2009 ዓ ም፣ የ AIR FRANCE የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላን፤ ከሪዮ ወደ ፓሪስ 228 ሰዎችን አሳፍሮ ሲያመራ አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የወደቀው በአብራሪው ስህተት መሆኑ ነው በምርመራ የተደረሰበት።

አኤሮፕላኖች ሁለት ትራስፖንደሮች ነው ያሉአቸው።በአብራሪው ክፍል (ኮክፒት) በግራና ቀኝ የሚገኙት ትራንስፖንደሮች ተግባራቸውን በትጋት እንዲያከናውኑ፣አንደኛው ሥራውን ሲያከናውን ሌላውም አግልግሎት ለመስጠት እንዲችል፣ተከፍቶ መቆየት ይኖርበታል። ቦይንግ 777 የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላን፣ትራንስፖንደሩ ከተዘጋ በኋላ አኤሮፕላኑ ወደ ሰሜን ምሥራቅ ማለትም ከኩዋላሉምፑር ወደቤይጂንግ አቅጣጫ በመብረር፣ በምሥራቃዊው ማሌሺያ ፤ ኮታ፣ ባህሩጋ ሲደርስ ድንገት መሥመሩን ለውጦ ወደ ፔናንግ ደሴት ማለት ወደሰሜን ምዕራብ ነበረ ያቀናው።አቅጣጫ ለውጦና ከፔናንግ በስተሰሜን ምዕራብ፣ሦስት መቶ ኻያ ኪሎሜትር ገደማ ሲበር፣ የማሌሺያ ጦር ኃይል ሬዳር ተከታትሎት እንደነበረም ተወስቶአል። የ፲፬ አገሮችን ዜጎች አብዛኞቹ (153) ቱ ቻይናወያን ፣ 38 ቱ ደግሞ ማሌሺያውያን መሆናቸው ታውቋል።

ዓለም በበረራ ሳይንስ በተራቀቀበት በአሁኑ ዘመን ፤ ከማሌሺያ ተነስቶ አየር ላይ ድንገት የተሠወረው የህዝብ ማመላለሻ አኤሮፕላን ሁኔታ ደብዛው በጠፋ በ 11ኛው ቀን ፤ ዛሬም ቢሆን እንዳስገረመ ነው።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ


Audios and videos on the topic