በረሐ የቀረው የአፍሪቃውያን ተስፋ | አፍሪቃ | DW | 17.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

በሐራ በርሐ እና ሜድትራኒያን ባሕር የከሸፈው የአፍሪቃውያን ሕልም

በረሐ የቀረው የአፍሪቃውያን ተስፋ

በየአመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አውሮጳ ለመሻገር ሲሞክሩ ሕይወታቸውን ያጣሉ። በጀርመን የሚኖሩ አፍሪቃውያን «ማንም በበርሐ አሊያም በባሕር ሊሞት አይገባም» የሚል ዘመቻ ጀምረዋል። ዘመቻው የሜድትራኒያንን ባሕር ለማቋረጥ ወደ አውሮጳ ለመሻገር ሲሞክሩ ሕይወታቸውን ስደተኞችን ሞት ለመግታት ያለመ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:43

በሰሐራ በርሐና ሜድትራኒያን ባሕር የከሸፈው የአፍሪቃውያን ሕልም

በካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ ንሎንካክ በተሰኘ የመኖሪያ መንደር የነ ሚሊንጉይ ቢያ የሙዚቃ ቡድን የከተማዋን ወጣቶች ቀልብ ለመሳብ እየታተረ ነው። ሚሊንጉይ ቢያ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ወደ አውሮጳ ለመሻገር ከሚጥሩ ወጣቶች መካከል አንዱ ነው። ቢያ ናይጄሪያ፣ቤኒን እና ኒጀርን በማቋረጥ ወደ አውሮጳ ለመሻገር ቢሞክርም ለተሻለ ኑሮ የነበረው ተስፋ አልጄሪያ ሲደርስ ከንቱ ሆኗል። ገንዘቡን በአጭበርባሪዎች የተዘረፈው ቢያ ወደ ካሜሩን ለመመለስ የማይፈልገውን ሥራ መስራት ነበረበት።
«ማለዳ በርሐውን ለማቋረጥ በጭነት ተሽከርካሪ ተጫንን። እንስቶች በተመለከቱ ቁጥር ወሲባዊ ግንኙነት ማድረግ ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር ነበርን። እንስቶቹ ሲቃወሙ ሁላችንንም ከተሽከርካሪው አስወረዱን። መንገድ ላይ የሞቱ ሰዎች ነበሩ። ስንጓዝ ልብሶቻችንን የያዙ ሻንጣዎች እና የውሐ ኮዳዎች ተሸክመን ነበር።  ጉዞው አድካሚ ሲሆን ሁሉንም ለመጣል ተገደድን። አንዳንድ ሰዎች በበረሐ ሲሞቱ አስከሬኖቻቸውን ጥለን መሔድ ስለማንችል በአሸዋ ሸፍነን ጉዟችንን መቀጠል ነበረብን።»

የቢያ ታሪክ በጀርመን የሚኖሩ አፍሪቃውያን ወደ ካሜሩን ተጉዘው ይኸን ገዳይ ጉዞ የሚያደርጉ ወጣቶችን ለማገዝ ካነሳሱ መካከል አንዱ ነው። «ማንም በበርሐ አሊያም በባሕር ላይ መሞት የለበትም» የተሰኘውን ዘመቻ የጀመረችው ሲልቪ ናንትቻ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ አውሮጳ ለመሻገር የሚሞክሩ በርካታ አፍሪቃውያንን ልብ ሰባሪ ታሪኮች መሰነዳቸውን ትናገራለች። 

«ጉዞውን ሲጀምሩ ሁለት ሳምንት ብቻ ይወስድብናል ብለው ቢያስቡም ከአውሮጳ ለመድረስ አንድ አመት፣ሁለት አመት፣ሶስት አመት እንደፈጀባቸው አጫውተውኛል። በጉዞው መጀመሪያ ብዙ ገንዘብ አናወጣም የሚል እምነትም ነበራቸው። ነገር ግን ከ10,000 ዩሮ በላይ አጥፍተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሌላ የተሳሳተ መረጃም ነበራቸው። ጣልያን አሊያም ስፔን ስትደርሱ ስራ ትቀጠራላችሁ ተብለው ነበር። ጣልያን፤ ስፔን ወይም ጀርመን ሲደርሱ ስራ አላገኙም። ሕገ-ወጥ በመሆናቸው ሥራ የመሥራትም ሆነ የመማር እድል የላቸውም። ይኸ ደግሞ ትልቅ ችግር ነው።» 

ሲልቪ ናንትቻ  ወጣቶቹን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ብዙ ጊዜዋን ብታጠፋም የ23 አመቷን ኔማቾ ጃኒን ማስቆም አልቻለችም። ጃኒን በካሜሩን ያለውን ሥራ አጥነት መቋቋም እንደተሳናት ትናገራለች። 

«ሁላችንም የየራሳችን እጣ-ፈንታ አለን። እድሜ ልካችንን በካሜሩን ለመኖር አልተፈጠርንም። ሁሉም ካሜሩንያውያን እዚህ ለመኖር ብቻ አልተፈጠሩም።»

ወደ አውሮጳ ለመሻገር መሞከር ያለው አደጋ ላይ የሚጠነጥነው በመገናኛ ብዙሃን ተደጋጋሚ ሽፋን አግኝቷል። ሜሊንጉይ ቢያ ፓውል ግን ድጋሚ አስቸጋሪውን ጉዞ ለመሞከር ፍላጎት አለው።

«ካሜሩን የወጣቶችን ተሰጥዖ ትቀብራለች። ከትምህርት በኋላ ሥራ ስትፈልግ ቅድመ-ሁኔታዎች ይሰጡሃል። ካሜሩን ጥሩ ሀገር መሆኗ እሙን ነው። ነገር ግን ተሰጥዖን ትቀብራለች። በካሜሩን መቆየት፤በካሜሩን መሰቃየት ሕልሜ አይደለም።» የ25 አመቱ ፒተር ንቺንዳ ሕገ-ወጡን ስደት ለማስቀረት አውሮጳ የተገን ፖሊሲዋን ልታላላ ይገባል የሚል እምነት አለው። 

«አውሮጳ በአፍሪቃውያን ላይ ያላትን ገደብ ልታላላ ይገባል። አውሮጳ የጣለችውን ገደብ ልታነሳ ይገባል። ካሜሩን የቦኮ ሐራምን ጥቃት ሸሽተው ከናይጄሪያ የሚመጡትን፤ የሰርጎ-ገብ ጥቃትን ሸሽተው ከመካከለኛው አፍሪቃ ሪፐብሊክ የሚመጡትን ሁሉ ትቀበላለች። አውሮጳ በኤኮኖሚያዊ ምክንያት የሚሰደዱ አፍሪቃውያንን ልትቀበል ይገባል። ስለዚህ አውሮጳ እንደ አፍሪቃ ሁሉ ድንበሮቿን ልትከፍት ይገባል።»
ስልቪ ናንትቻ በካሜሩን የጀመሩት ዘመቻ ወደ አውሮጳ ስለሚደረገው ሕገ-ወጥ ጉዞ የወጣቶችን አይን ከፍቷል ብላ ታምናለች። 

«አውሮጳ ገነት አይደለችም። ወደ አውሮጳ ለመምጣት ይሔን አደገኛ ጉዞ ማድረግ አይጠበቅባቸውም። ወጣቶች ወደ አውሮጳ የሚጓዙት ምርጫ በማጣታቸው መሆኑን ነግረውኛል። እነርሱን ማሳመን ከባድ ነው። ነገር ግን ከእነርሱ ጋር በመነጋገር እንዴት  አማራጮች ልናቀርብላቸው እንደምንችል ማየት፤አሊያም ወደ አውሮጳ ለመምጣት ቪዛ እንደሚያስፈልጋቸው ትክክለኛውን መረጃ መስጠት ይኖርብናል።»
ከጀርመን ከተጓዘው ቡድን ጋር ለስብሰባ ከተቀመጡት መካከል የሚሊንጉይ ቢያ ፖልስ እናት ሚሊንጉይ ጌትሩድ ይገኙበታል። የሚሊንጉይ እናት ልጃቸው ጉዞ ላይ በነበረባቸው አራት አመታት ልባቸው አለማረፉን ያስታውሳሉ። ወ/ሮ ሚሊንጉይ ጌትሩድ  ሌሎች ሰዎች ተጠንቀቁ የሚል ምክር አላቸው። 

«ወንድሞቼ እና ልጆቼ ሆይ ምክሬን ስሙኝ። በሀገራችሁ በርትታችሁ ስሩ። የምትበሉት እና የምትጠጡት አታጡም። ብትታመሙ የሚጠይቋችሁ ሰዎች በዚህ አሉ። በውጭ አገር ከሆናችሁ ግን ጎረቤቶቻችሁ እንኳ ስለ ጤንነታችሁ ግድ የሚሰጣቸው አይመስለኝም።»


ሞኪ ኪንድዜካ /እሸቴ በቀለ
ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች