በሥነ ጽሑፍ የኖቤል ተሸላሚው ጉዑንተር ግራስ ዐረፉ | ባህል | DW | 13.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

በሥነ ጽሑፍ የኖቤል ተሸላሚው ጉዑንተር ግራስ ዐረፉ

ከሥነ ጽሑፍ ሌላ፤ በማሕበራዊ የፖለቲካ ሕይወት ክርክር ይወዱ የነበሩት ጉንተር ግራስ፣ የቀድሞው የጀርመን መራኄ መንግሥት ፣ ቪሊ ብራንት፤ ከፖላንድ ጋር ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ የተከተሉትን የውጭ የፖለቲካ መርሕ ከመደገፋቸውም በላይ ፣ በምርጫ ዘመቻ ለሶሺያል ዴሞክራቱ ፓርቲ (SPD) መታገላቸው ይነገርላቸዋል።

ጀርመናዊው ታዋቂ የሥነ ጽሑፍ ሰው፣ ቀራጺና ሠዓሊ ጉንተር ግራስ በ 87 ዓመታቸው ፣ የቀድሞው ዝነኛ የሥነ ጽሑፍ ሰው ቶማስ ማን በተወለዱባት ከተማ በሉቤክ ዐረፉ። እ ጎ አ በ 1929 በዛሬዋ የፖላንድ የወደብ ከተማ ዳንትዚግ ውስጥ የተወለዱት ግራስ ፤ እ ጎ አ በ 1959 ዓ ም፤ ለጻፉት Die Blechtrommel (የቆርቆሮው ከበሮ) በተሰኘው ልብ ወለድ መጽሐፋቸው ዓለም አቀፍ ዝና ማትረፍ ብቻ ሳይሆን ፣ በዚህ ታዋቂ ሥራቸው ሳቢያ ፣ እ ጎ አ በ 1999 የኖቤል ሽልማት አግኝተዋል ። ከሥነ ጽሑፍ ሌላ፤ በማሕበራዊ የፖለቲካ ሕይወት ክርክር ይወዱ የነበሩት ጉንተር ግራስ፣ የቀድሞው የጀርመን መራኄ መንግሥት ፣ ቪሊ ብራንት፤ ከፖላንድ ጋር ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ የተከተሉትን የውጭ የፖለቲካ መርሕ ከመደገፋቸውም በላይ ፣ በምርጫ ዘመቻ ለሶሺያል ዴሞክራቱ ፓርቲ (SPD) መታገላቸው ይነገርላቸዋል። ክርክርና ሒስ ይወዱ የነበሩት ግራስ ፣ እ ጎ አ በ 2012 እሥራኤልን የሚተች ረጅም ግጥም በማቅረባቸው ራሳቸው የመከራከሪያ ርእስ ለመሆን በቅተው አንደነበረም ይታወሳል። ጉንተር ግራስ ፤ በመጨረሻው የአዛውንት ሕይወታቸው፤ በናዚ ጀርመን የአገዛዝ ዘመን በተለይም የ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በለጋ ወጣትነት ዕድሜ የውጊያ ረዳት ሆነው መሠለፋቸውን እንዲሁም SS (Sichreheitsstaffel) የተሰኘው የናዚ ፓርቲ ልዩ ፈጥኖ ደራሽ ጦር አባል ለመሆን ተገደው እንደነበረ መናዘዛቸው፣ ጉድ አስኝቶ ነበር። የታዋቂውን ደራሲ ሞት በዛሬው ዕለት የሰሙ ጸሐፍትና ደራስያን መደንገጣቸውንና ማዘናቸውን ገልጸዋል። ጉንተር ግራስ፣ አከራካሪ ሐሳቦችን የማይፈሩ የሐያሲነት መንፈስ ያልተለያቸው ታላቅ ደራሲ ነበሩ ሲሉም በአድናቆት አስታውሰዋቸዋል።

ኂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ