በሠዓት ዝቅተኛ የክፍያ መጠን በጀርመን | ኤኮኖሚ | DW | 02.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

በሠዓት ዝቅተኛ የክፍያ መጠን በጀርመን

የመራሂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ክርስቲያን ዲሞክራቶች ኅብረት ፓርቲ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ፓርቲው በቅርቡ በተካሄደው የጀርመን የምክር ቤት እንደራሴዎች ምርጫ አብላጫውን ድምፅ ቢያገኝም፤ ሀገሪቱን በጥምረት አብሮ ሲመራ የቆየው FDP ለምክር ቤት በቂ ድምፅ ባለማግኘቱ ከሌሎች የተቃውሞ ፓርቲዎች ጋር ለመጣመር ድርድር በማድረግ ላይ ይገኛል።

በጀርመን ሀገር በሠዓት ዝቅተኛው የክፍያ መጠን ምን ያህል ይሁን የሚለው አጨቃጫቂ ጉዳይ ፓርቲዎች በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ካነሷቸው አበይት ነጥቦች ቀዳሚው በመሆኑ የሚደረገውን ድርድር እጅግ አስቸጋሪ ያደርገዋል። በዛሬው ከኢኮኖሚው ዓለም በስፋት የምንቃኘው ይሆናል።

የነፃ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ ከጀርመን ምክር ቤት መሰናበት ምናልባትም በጀርመን በሠዓት ዝቅተኛውን የክፍያ መጠን የመወሰኑ ጥያቄ መልስ የሚገኝለት ይመስላል። ይሁንና የጀርመን የምጣኔ ሀብት ጥናትና ምርምር ተቋም 8,50 ዩሮ በሠዓት ዝቅተኛው ክፍያ ይበዛል ባይ ነው።

ለመሆኑ በጀርመን አንድ ሠራተኛ ማግኘት የሚገባው ዝቅተኛ የክፍያ መጠን በሠዓት ምን ያህል ነው መሆን ያለበት? ምስራቅ አውሮጳ ውስጥ በሚገኙት ሐንጋሪ፣ ስሎቫኪያ፣ ሊትዋንያ እና ላቲቪያ በሠዓት ዝቅተኛ የክፍያ መጠን ሁለት ዩሮ እንኳን አይደስርስም። ወደ ምዕራብ ጀርመን ስናቀና ደግሞ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም እና ኔዘርላንድ ውስጥ ዝቅተኛ እርከኑ ከዘጠኝ ዩሮ ከፍ ያለ ነው። በሉክዘምበርግ እንደውም አንድ ሰው ለአንድ ሠዓት ለሰራበት መከፈል ያለበት ዝቅተኛ ክፍያ እርከን 11 ዩሮ ገደማ ይሆናል። በጀርመን ግን ለተወሰኑ የስራ አይነቶች ከተቀመጠው ዝቅተኛ የክፍያ መጠን በስተቀር ይህ ነው የተባለ አንድ ወጥ የክፍያ መጠን የለም። ሁኔታው መራሂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልን ሳያበሳጭ አልቀረም።

ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል ከSPD ፒር ሽታይንብሩክ ጋር

ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል ከSPD ፒር ሽታይንብሩክ ጋር«በአገልግሎት ሰጪው ዘርፍ ለአብነት ያህል በእኔ የምርጫ ቃጣና ሩገን በተሰኘው ደሴት ውስጥ በማዕድ ቤት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች አሁንም ድረስ በሣምንት ለ40 ሠዓታት እየለፉ ቀሪ ወጪያቸውን ለመሸፈን ሲሉ ወደ ስራ አፈላላጊ መስሪያ ቤት የሚሄዱ አሉ። ያ ትክክለኛ ነገር አይደለም።»

የጀርመን መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርክል ይህን የተናገሩት ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ ነበር። እንዲያም ሆኖ CDU የተሰኘው ፓርቲ የበላይ ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል በሠዓት ዝቅተኛ የክፍያ መጠን ጀርመን ውስጥ በሕግ እንዲደነገግ ለማድረግ ጥረት ሲያደርጉ አይታይም። ይልቁንስ ይህን ጥያቄ በምርጫው ሰሞን ጭምር በጥልቀት የገፉበት የሶሻል ዲሞክራቶቹ ዋነኛው የተቃውሞ ፓርቲ SPD እና የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ናቸው። ግራዎቹም ጉዳዩን አንስተው በጥብቅ ሲሞግቱበት ከርመዋል። SPD እና አረንጓዴዎቹ ዝቅተኛ የክፍያ እርከን 8,50ዩሮ እንዲሆን ሲጠይቁ፤ ግራዎቹ እንደውም ከ10 ዩሮ ማነስ የለበትም በማለት ይከራከራሉ።

CDU እና እህት ፓርቲው ክርስቲያን ሶሻል ኅብረት CSU በሠዓት የዝቅተኛ ክፍያ ጉዳይን ወደ ጎን ሲገፉ ይስተዋላል። ሠራተኛው በሠዓት ምን ያህል ይከፈለው የሚለው መወሰን ያለበት በሠራተኛ እና አሰሪው ስምምነት መሆን አለበት የሚል አቋም አላቸው። ከCDU እና CSU ጋር በጥምር ሲያስተዳድር የነበረው የነፃ ዲሞክራቶቹ ፓርቲ FDP በሠዓት ዝቅተኛ ክፍያ የሚለውን ሀሳብ ጭራሽ አይቀበለውም። የአሰሪና ሠራተኛ ጉዳዮች ባለሙያው ካርል ብሬንከ ዝቅተኛ ክፍያን አስመልክተው ሲያስጠነቅቁ የሌሎች ሃገራትን ልምድ በማጣቀስ ነው።


«በብሪታንያ ለምሳሌ እድሜን እና ብቃትን መሰረት ያደረገ ልዩነት አለ። በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ከግዛት ግዛት ይለያያል። አንዳንድ ግዛቶች ካስቀመጡት አጠቃላይ መፍትኄ ባሻገር የተለየ በሰዓት ዝቅተኛ የክፍያ እርከን ደንብም አላቸው።»

ስደተኛ የእንጆሪ ለቀማ ላይ ተሰማርቶ

ስደተኛ የእንጆሪ ለቀማ ላይ ተሰማርቶ

ካርል ብሬንከ እና በዓለም አቀፍ የምርምር ተቋሙ ውስጥ በጋራ ጥናታዊ ፅሁፍ በማቀናበር ባልደረባቸው የሆኑት ካይ ኡቬ ሙለር በሠዓት ዝቅተኛ የክፍያ መጠን በተለይ በጀርመን ምን ይዘት እንዳለው ጥናት አካሂደዋል። ባካሄዱት ጥናት መሰረትም በአሁኑ ወቅት ጀርመን ውስጥ 5,6 ሚሊዮን የሚጠጉ ሠራተኞች በዝቅተኛ ክፍያ መጠን መሰረት በሠዓት 8,50 ዩሮ ማግኘት ይገባቸዋል። ካይ ኡቬ፥«በሠዓት ዝቅተኛ ክፍያ ማበጀት የአከፋፈል ሁናቴው ላይ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የክፍያ ኢፍትሐዊነትን ለመቀነስ ይረዳል። እዚህ ላይ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው የሚገቡ ሁለት ተግዳሮቶች ግን አሉ። የመጀመሪያው በቅጥር ላይ ምንም ተፅዕኖ አያሳርፍ እንደው ማየቱ ነው። የቅጥር ቅነሳ የሚደረግ ከሆነ ግን ያ በእውነቱ በገቢ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፤ እናም ይሄ መወገድ አለበት።»

እንደ ጥናት አቅራቢዎቹ ብሬንከ እና ሙለር በሠዓት ዝቅተኛ የክፍያ መጠንን መወሰን በጀርመን ሀገር ድህነት እና ያልተመጣጠነ የአከፋፈል አሰራር ጉልህ በሆነ መልኩ እንዲቀነስ ያደርጋል። ገቢያቸው ደከም ያሉ ሰዎችም በዝቅተኛ ወርሃዊ በጀት ከመንገታገት ድነው በአነስተኛ ስራዎች ለመሰማራት መጠነኛ የትርፍ ሠዓት ስራም ለማከናወን ይችላሉ።

በጀርመን አንድ ግለሰብ በወር ከ450 ዩሮ የማይበልጥ ገቢ የሚያገኝ ከሆነ ስራው አነስተኛ ስራዎች በሚባሉት ውስጥ ነው የሚመደበው። አነስተኛ ስራዎች ደግሞ የደመወዝ ግብር አይቆረጥባቸውም። ብሬንከ እና ሙለር ጥናታቸውን ሲያከናውኑ ትኩረታቸውን በሠራተኞች ላይ ብቻ ሳይሆን ያደረጉት አሰሪዎችንም የሚመለከቱ ጉዳዮችን ለመዳሰስ ሞክረዋል። በሠዓት ዝቅተኛው የክፍያ መጠን ደንብ የሚወጣ ከሆነ በተለይ የሚያተኩረው እስከ አራት ሠራተኞችን የሚያስተዳድሩ አነስተኛ ድርጅቶች ላይ ይሆናል። እንደ ዳቦ ቤቶች፣ የውበት ሳሎኖች፣ ምግብ ቤቶች ብሎም የግብርና ስራዎች፣ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው የግድ ተጨማሪ ገንዘብ መክፈል ይጠበቅባቸዋል። እንደ ጥናት አቅራቢዎቹ ከሆነ በሠዓት ዝቅተኛው ክፍያ 8,50 ዩሮ የሚደረግ ከሆነ ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው የሚከፍሉት የደሞዝ መጠን በ20 ከመቶ ከፍ እንዲል ያደርጋል። ያ በመሆኑም ድርጅቶች ለምሳሌ ከ7 ዩሮ በመነሳት ቀስ እያሉ ጭማሪ በማድረግ እንዲያለማምዱ የሚያደርጉበት ስልት እንዲበረታታ ይመክራሉ። ድርጊቱ በእዛ መልኩ ስኬታማ ከሆነ በሂደት ዝቅተኛውን ገደብ ከፍ ማድረግ ይቻላል።

የሕንፃ መስተዋት ፅዳት

የሕንፃ መስተዋት ፅዳት«በሠዓት ዝቅተኛ የክፍያ መጠን ያለወጪ የሚተገበር ነገር አይደለም። በቅጥር ስምምነት ይሁን፣ የዕለት ፍጆታ ዕቃዎች ላይ ዋጋ በመጨመር ወይንም ድርጅቶች ትርፋቸውን ዝቅ በማድረግ፤ ብቻ በሆነው መንገድ ወጪው መሸፈን አለበት። እንደው ብቻ በይፋ በተደረጉ ክርክሮች በጥቂቱ ተፅዕኖ የሚያሳድረው ጥቅሙ ለሁሉም ነው የሚለው አባባል በጥቅሉ ሲታይ ትንሽ ግራ የሚያጋባ መሆኑ አልቀረም።»

በእዚህም አለ በእዚያ ግን አዲሱን ጥምር መንግሥት ለመመስረት አርብ ንግግር የሚጀምሩት ሁለቱ ፓርቲዎች ማለትም፤ ክርስቲያን ዲሞክራቶቹ ኅብረት CDUና ሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ SPD ከስምምነት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል። ድርድሩ በእርግጥ እስከ ቀጣዩ የጥር ወር ድረስ ሊዘልቅ ይችል እንደሆነም SPD ከወዲሁ አስታውቆዋል። SPD በምርጫ ዘመቻው ወቅት በሠዓት ዝቅተኛ ክፍያ ደንብ ሊወጣ ይገባል ሲል አጥብቆ ይሟገት ነበር። CDU ተቃራኒ አቋም ነው ያለው። ምናልባትም ሁለቱ ታላላቅ ፓርቲዎች ከአረንጓዴዎቹ ጋር በመጣመር መንግሥት ለመመስረት ይሳካላቸውና በሠዓት ዝቅተኛ የክፍያ መጠን ጉዳይ ዕልባት ያገኝ ይሆናል።

በፓርቲዎቹ መካከል ድርድሩ በሚጠበቅበት በአሁኑ ወቅት የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ዮኣሂም ጋውክ ከመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ጋር ሚስጥራዊ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል። ፕሬዚዳንቱ ምክር ቤት መግባት ከቻሉት አራቱ ፓርቲዎች መሪዎች ጋርም ለመነጋገር ቀጠሮ መያዛቸው ተጠቅሷል። እንዲያም ሆኖ ግን አሁን ፓርቲዎቹ ጥምር መንግሥት ለመመስረት በሚያደርጉት ድርድር የመጨረሻ ስምምነት ላይ ካልደረሱ በጀርመን ዳግም የምክር ቤት እንደራሴዎች ምክር ቤት ምርጫ መካሄዱ፣ በሠዓት ዝቅተኛ የክፍያ መጠን ጉዳይም መራዘሙ አይቀሬ ይሆናል። ሁሉንም በሂደት የምናየው ይሆናል።


ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic