በሞያሌ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 10 ደረሰ | ኢትዮጵያ | DW | 11.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በሞያሌ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 10 ደረሰ

በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 10 መድረሱን የአካባቢው ባለስልጣን እና የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ገለጹ፡፡ ዛሬ አንድ ሰው ሲገደል ሌላ አንድ ሰው መቁሰሉን ደግሞ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ የደኅንነት ሥጋት የገባቸው የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች ወደ ኬንያ ተሰደዋል ተብሏል፡፡ 

የሞያሌ ከተማ ከንቲባ አቶ አስቻለው ዮሃንስ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ትላንት ከተገደሉት ውስጥ የአራቱ ቀብር ዛሬ ተፈጽሟል፡፡ የቆሰሉት ሰዎች ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሐዋሳ መላካቸውንም ከንቲባው ገልጸዋል፡፡ የከተማይቱ ነዋሪዎች ትላንት እና ዛሬ ወደ ኬንያ መሰደዳቸውን አቶ አስቻለው አረጋግጠው ብዛታቸው ምን ያህል እንደሆነ ግን እንደማያውቁ አስረድተዋል፡፡  

“ትላንትና በትክክል የሞቱት ዘጠኝ ናቸው፡፡ ከቆሰሉት ውስጥ አንድ ተጨምሮ አሁን የሟች ቁጥር አስር ደርሷል፡፡ ከዚያ ውጭ የቆሰለው አስራ አንድ ሰው ነው፡፡ ዛሬ አራት እዚህ ተቀብሯል፡፡ ሌላ ሶስት ወደ ሀገር ቤት ሄዷል፡፡ አንዱ የጉራጌ ተወላጅ ነው፡፡ ሁለቱ የኦሮሞ አርሲ ተወላጆች ናቸው፡፡ እነዚያ ዛሬ ወደ ቤተሰቦቻቸው ተልከዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ሁለት ቤተሰቦቻቸው ያልታወቁ አሉ፡፡ እነርሱን እስከ ነገ ጠብቀን የሚደረገውን ነገር ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ተወያይተን ውሳኔ እንሰጣለን፡፡ ትላንት ያው በተፈጠረው ሁኔታ ህዝቡ ስጋት ስለገባው ምንም የደህንነት ማስተማመኛ የለም በሚል ወደዚያ መሸጋገሩ ያለ ነገር ነው፡፡ ህዝቡ አሁን ወደ ኬንያ ማዶ ሴሺ ሞያሌ ታውን የሚባል አካባቢዎች ላይ ነው ሰፍሮ ያለው፡፡” 

ስለዛሬው ሁኔታ የተጠየቁት የሞያሌ ከንቲባ አንድ ሰው በሞተር ሳይክል ሲሄድ በጥይት ተመቶ መቁሰሉን መስማታቸው እና ተጨማሪ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ አንድ የሞያሌ ሆስፒታል ሰራተኛ ግን ዛሬ በጥይት ከተመቱት ውስጥ አንደኛው ሞቶ ሌላኛው መቁሰሉን እማኝነታቸውን ለዶይቸ ቬለ ሰጥተዋል፡፡ 

“ዛሬ ራሱ ሰባት ተኩል ላይ ሰው ተመትቷል፡፡ ጫሜ የሚባል ቦታ፡፡ ከሆስፒታል በኩል  ነው ራቅ ይላል፡፡ ሁለት ሰው ተመትቷል፡፡ አንዱ ሆስፒታል ነው ያለው፡፡ አንዱ ሞቷል ይባላል፡፡ መከላከያ፣ አጋዚ ነው፡፡ ከአጋዚ ውጭ ማንም አይደለም፡፡ ትላንት እኔ በአይኔ ያየሁት የ10 ሰው ሞት ነው፡፡ ሬሳ ክፍል ውስጥ ነው፡፡ የሞተ፣ ህይወቱ የጠፋ፡፡ የቆሰለ አስራ ምናምን ሰው ነው፡፡ ከስልጤም፣ ከወላይታም፣ ከኦሮሞም ብሔር ብሔረሰብ ነው የተገደለው፡፡ ያለምንም ጥፋት ያለምንም ጥያቄ ነው የተገደሉት እነዚህ ሰዎች፡፡”

በሆስፒታል በመገኘት አስር የሞቱ ሰዎችን በአይናቸው መመልከታቸውን የተናገሩ አንድ የሸዋ በር ነዋሪ ደግሞ ወደ አስር ሰዓት ግድም እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ የቀበሌያቸው ነዋሪዎች ድንበር አቋርጠው ወደ ኬንያ መግባታቸውን አስረድተዋል። አሁን በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ የተናገሩት ተፈናቃዩ መሬት ላይ ተኝተው ማደራቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን ስለተጠሉለበት ቦታ ደግሞ ተከታዮን ብለዋል።  

“እኛ አካባቢ እዚህ የተጠልለነው ትንሽ ነን፡፡ አንድ ሁለት ሺህ አንበልጥም፡፡ እንደኬንያ አጠራር ሴሺ ነው የሚባለው፡፡ ሞያሌ አውራጃ ሆኖ በማርሳቤት አስተዳደር ውስጥ ነው፡፡ የትላንቱን ጭፈጨፋ ህዝቡ ፈርቶ ነው፡፡ ያንን ፍራቻ እንደገና ይደገማል ብሎ ሀዝቡ ከሶስት ቀበሌ ወጥቷል፡፡  ከጫሙቅ፣ ሸዋበር እና አርበሌ ቀበሌዎች ኬንያ ተሰድደው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ህጻናት እና ሴቶች አብዛኞቹ ሄደዋል፡፡ አንዳንድ ደግሞ ወንዶች እዚያ የቀሩ አሉ፡፡”  

ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች በሌላ ቦታ ተጠልለው መመልከታቸውን እኚሁ ተፈናቃይ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ ተፈናቃዩ እንዳሉት በኬንያ ግዛት የአካባቢው አስተዳደር እና የቀይ መስቀል ሰዎች ምግብ እና መጠጥ ለተፈናቃዮቹ ያደሉ ሲሆን ዛሬም ምዝገባ ሲያካሄዱ ውለዋል። ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ግን ማንም ሰው መጥቶ እንዳልጎበኛቸው አስረድተዋል፡፡

በሞያሌ ስለተፈጠረው ሁኔታ ለመንግስታዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ ማብራሪያ የሰጡት የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት ሴክሬተሪያት ተወካይ ሌተናል ጄነራል ሀሰን ኢብራሂም የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ አዛዦችን ያካተተ ቡድን ዛሬ በሄሌኮፕተር ወደ አካባቢው በፍጥነት መሄዱን ገልጸው ነበር፡፡ ሌተናል ጄነራል ሀሰን ትላንት በሞያሌ የተፈጠረውን ሁኔታ “የተሳሳተ መረጃ በመያዝ የተፈጠረ ግጭት” ሲሉ የጠሩት ሲሆን ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በግጭቱ ተሳትፏል የተባለ የአንድ ሻለቃ ጦር ትጥቅ እንዲፈታ ተደርጎ አምስት አባላቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡     

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ