1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሞያሌ ዙሪያ የመንግስትና ታጣቂዎች ተኩስ ልውውጥ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 27 2014

የኢትዮጵያ መንግስት «ሸኔ» ብሎ የሚጠራው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ኃይል ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ኬንያ ድንበር አቅራቢያ ሞያሌ ከተማ አካባቢ ውግያ ገጥመው እንደነበር የነገሌ ወረዳ አስተዳዳሪ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ታጣቂዎቹ መጠለያቸውን ካደረጉበት ሰሜን ኬንያ በመዝለቅ የሽምቅ ውግያ  ጥቃት መሞከራቸውም ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/49VCE
Wegweiser Autobahnschild Äthiopien
ምስል DW

ሚሊሻ ባረፈበት ነው አነጣጥረው ተኩስ የከፈቱት

የኢትዮጵያ መንግስት «ሸኔ» ብሎ የሚጠራው እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ኃይል ከመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ጋር ኬንያ ድንበር አቅራቢያ ሞያሌ ከተማ አካባቢ ውግያ ገጥመው እንደነበር የነገሌ ወረዳ አስተዳዳሪ ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ። ታጣቂዎቹ መጠለያቸውን ካደረጉበት ሰሜን ኬንያ በመዝለቅ የሽምቅ ውግያ  ጥቃት መሞከራቸውም ተገልጧል። «የኦሮሞ ነጻነት ጦር» ቃል አቃባይ ኦዳ ተርቢ በበኩላቸው በውግያው በመንግስት ኃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱን እና ከአካባቢው ማፈግፈጋቸውን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል። ከሞያሌ ከተማ ሦስት ኪሎ ሜትሮች ገደማ ርቆ በሚገኝ ስፍራ ላይ በሁለቱ ኃይሎች መካከል  የተኩስ ልውውጡ እስከ እሁድ ጠዋት የዘለቀ እንደነበረም ተገልጧል። 

የተኩስ ልውውጡ ኢትዮጵያ በስተ ደቡብ ከጎረቤት ሃገር ኬንያ ጋር በምትዋሰንበት የንግድ መዳረሻዋ ሞያሌ ከተማ ከ3 ኪ.ሜ. ገደማ ርቀት ላይ መከሰቱ ነው የተገለጸ። የወረዳዋ አስተዳዳሪ ለዶይቼ ቬለ (DW) እንደተናገሩት በሌሊት በተፈጸመው የተኩስ ልውውጡ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን እና አከባቢው በአሁኑ ወቅት ሰላማዊ የኑሮ እንቅስቃሴ የሚስተዋልበት ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ጥቃት በመፈጸም መንግስት በተደጋጋሚ የሚከሰው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ግን የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በደቡብ ኢትዮጵ ኮማንድ ከሚሰነዘረው ጥቃት ወደ ጉጂ ዞን ዋና ከተማ ነጌሌ እያፈገፈጉ ነው ይላል፡፡

ደቡብ ኦሮሚያ ቦረና ዞን ከሞያሌ ከተማ ወጣ ብሎ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ቦሌ በተባለ አከባቢ በባለፈው ቅዳሜ ለእሁድ አጥቢያ በአከባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የተከፈተው ተኩስ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ያረፉበት ካምፕ ኢላማው ማድረጉ ነው የሚገለጸው፡፡ የሞያሌ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ጂርማ ቢሊሶ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት የተኩስ ልውውጡ እስከ እሁድ ጠዋት የዘለቀ ነበር፡፡ 

“በአከባቢው የሚንቀሳቀሰው ያው የሸኔ ጦር ነው፡፡ ሰርገው ገብተው ነው በፀጥታ ኃይሎቻችን ላይ ተኩስ ከፍተው የነበሩት፡፡ የተከፈተውም ጥቃት ፊት ለፊት በቀን የፀጥታ ኃይሎቻችን የተገዳደሩ ሳይሆን በእኩለ ሌሊት ነው ሰርገው ገብተው በሽምቅ ውጊያ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩት፡፡ እንደውም ከዚያ ቀን አስቀድሞ ተኩሱን የጀመሩት የሚሊሻ ጥበቃ በሌለበት ከተማ ላይ አነጣጥረው ነበር፡፡ የቅዳሜ ሌሊት እሁድ አጥቢያው ግን ከከተማ 2-3 ኪ.ሜ. ወጣ ብሎ በሚገኘው ቦሌ አከባቢ ነው ሚሊሻ ባረፈበት አነጣጥረው ተኩስ የከፈቱት፡፡ ይህ ስፍራ ለጎረቤት አገር ኬንያ እጅግ በጣም ቅርብ ነው፡፡ መጠለያ ያደረጉትም በዚያ በሰሜን ኬንያ ነው፡፡ የፀጥታ ኃይሎቻችን ሲንቀሳቀሱ አሊያም ለስልጠና በቁጥር ሲቀንሱ ነው መጥተው ጥቃቱን የፈጸሙት፡፡”

እንደ ባለስልጣኑ ገለጻ ታጣቂዎቹን ተፋልመው የመለሱት የመንግስት የፀጥታ ኃይሎቹ በብዛት የአከባቢ ሚሊሻ ቢሆኑም የፌዴራልና የክልሉ ኃይሎችም እንደ የአከባቢው ባለስልጣን ማብራሪያ ግን ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ካደረጉት ታጣቂዎች ቢያንስ ሁለት ሰዎች እንደ ተጎዱ መረጃ ማግኘታቸውን ገልፀው የመንግስት የጸጥታ ኃይልም ሆነ ንብረት ላይ የደረሰ አንድም ጉዳት አልተከሰተም።

“በእኛ በኩል የደረሰ አንድም ጉዳት የለም፡፡ ጊዜው ለሌት ስለነበር ከሌላ ቦታም ወዲያውኑ ኃይል ተጨምረው ለመቆጣጠር ተችሏል፡፡ በእኛ በኩል ሁሉም ሰላም ነው፡፡ የወደመ ንብረትም ሆነ የጠፋ ህይወት የለም፡፡ በነሱ በኩል ግን ሁለት ቦታ በፈሰሰ ደም ቢያንስ ሁለት ሰዎች እንደተጎዱባቸው አረጋግጠናል፡፡ ይሙቱ ይኑሩ ግን አናውቅም፡፡” የሞያሌ ወረዳው አስተዳዳሪ ጂርማ ቢሊሶ አክለው እንዳብራሩት በቦረና ታጣቂዎች የሚቆጣጠሩት ቦታ የለም፡፡ እንደ እሳቸው አስተያየት ከሆነ ከጎረቤት ኬኒያ ጋር የሚያገናኘው የሞያሌ መንግገድ ላይ ተጽእኖ ይደርሳል የሚል ስጋት ቢያንስ እስካሁን አልተስተዋለም፡፡ 

“እነሱ የሚንቀሳቀሱበትና የተቆጣጠሩት አንድም ቀበሌ በዚህ የለም፡፡ የሞያሌ ወረዳን የሚያዋስነው ሚዮ፣ ዲሬ እና አሬሮ ወረዳ በሙሉ ከታጣቂው ኃይል ነጻ ናቸው፡፡ ያው ከኬንያም በሰፊው ስለሆነ የምንዋሰነው ይሄን ሁሉ መቆጣጠር አይቻላቸውም፡፡ እዚህ መጥተው የሚተኩሱትም ፊት ለፊት አይደለም፡፡ ይሄ ደግሞ ተለምዷል፡፡ የዛሬ አስር ዓመትም የዛሬ ሶስት ዓመትም የነበረ ነው፡፡ ህብረተሰቡን ለማስደንገጥ ብዙ ጊዜ ይሞክራሉ፡፡ እንደውም አብዛኛውን ጊዜ ያን ያህል የገዘፈ ኃይልም ተጠቅመን ሳይሆን በሚሊሻም ነው የምንከላከለው፡፡”

አከባቢው አሁን ላይ ሰለማዊ እና የእለት ተእለት ህይወት የቀጠለበትም ነው ተብሏል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ ላይ ከቀናት በፊት ባወጣው መረጃ ሸኔ ባለው ታጣቂ ቡድን ላይ ኦፐሬሽን እየተወሰደ መሆኑን የደቡብ ዕዝ የኋላ ደጀን አስተባባሪ ኮሎኔል ግርማ አየለን ዋቢ አድርገው ጽፈዋል።

ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ