በሞዛምቢክ እና ዚምባብዌ የበረታው የኢዳ ማዕበል | አፍሪቃ | DW | 23.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በሞዛምቢክ እና ዚምባብዌ የበረታው የኢዳ ማዕበል

ኢዳ በተባለው ኃይለኛ ማዕበል በተመታችው ሞዛምቢክ የሞቱ ሰዎች 417 ደርሰዋል። በዚምባዌ ሌሎች 259 ሰዎች ሲገደሉ 300 ገደማ የገቡበት አይታወቅም። በሰዓት 200 ኪ.ሜ. የነጎደው የኢዳ አውሎ ንፋስ ተራራ እየናደ መኖሪያ ቤቶች ቀብሯል። ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት ወድመዋል። ከአደጋው የተረፉ ኮሌራን ለመሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ተጋልጠዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:33

በማላዊ፣ ዚምባብዌና ሞዛምቢክ ከ600 በላይ ሰዎች ሞተዋል

ቤራ የተባለችው የሞዛምቢክ የወደብ ከተማ ነዋሪዎች ግፊያ እና ጩኸት በበረከተበት ሰልፍ የአካባቢው አስተዳደር ከሚያከፋፍለው እርዳታ ለመቃመስ ይታገላሉ። ከሰልፉ መካከል በዕድሜ የገፉ አረጋውያን፤ ሕፃን የታቀፉ እናቶች አቅም እና ጉልበቱ የሌላቸው ልጆች ጭምር ይገኙበታል። የጦር መሳሪያ ያነገቱ ጸጥታ አስከባሪዎች እርዳታ ፈላጊዎችን ሥርዓት ለማስያዝ የሚያደርጉት ጥረት ግን ፍሬ አላፈራም። ኢዳይ የሚል መጠሪያ የተሰጠው ድንገተኛ አውሎ ንፋስ የፈጠረው ከባድ ጎርፍ  ቤት ንብረታቸውን ያወደመባቸው ነዋሪዎች የመንግሥታቸው እጅ ጠባቂ ሆነዋል። ከልፉ መካከል የሚገኙ እንደሚሉት ግን እርዳታው በቂ አይደለም።

አንድ ከሰልፉ መካከል እርዳታ የሚጠብቅ የቤራ ነዋሪ "በረሐብ እየተሰቃየን ነው። እርዳታ በሰልፍ እንጠብቃለን። የአካባቢው አስተዳደር ስማችንን መዝግቦ ይኸው በሰልፍ እርዳታ እንጠብቃለን። ነገር ግን እርዳታው በፍጹም በቂ አይደለም። የከፋ ችግር ውስጥ ብንገኝም ምንም ነገር አልሰጡንም" ሲል ይናገራል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች አንዱ የሆነው አራት ልጆቹ በዳቦ ብቻ መቆየታቸው አሳስቦታል። "ልጆች አሉኝ። አራት ልጆች አሉኝ። እና ዳቦ ብቻ ሊመገቡ ነው? አንድ ከረጢት እርዳታ ስጡኝ" እያለ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይለማመጣል።

እርዳታ ከሚታደልባቸው ክፍሎች ለመግባት በርካቶች ይጋፋሉ። በሮች እና መስኮቶችን በኃይል ለማስከፈት የሚታገሉም ይገኙበታል። ልጇን ታቅፋ ከውጪ ለቆመችው ማርታ አንቶኒዮ ግን ይኸ የሚሞከር አይደለም።  "በእርዳታ በኩል ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተሰጠን ። ለሁሉም አያድሉም። እርዳታ የሚሰጠው በክፍሎቹ ውስጥ ለሚገኙ ብቻ ነው። እርዳታ ከሚሰጥበት ክፍል ውጪ የሚገኙ ግን አያገኙም" የምትለው ማርታ የምትሻውን ለማግኘቷ እርግጠኛ አይደለችም።

ለቤራ ነዋሪዎች የሚቀመስ ምግብ እና የሚጠጣ ንጹህ ውሐ ማግኘት ብቻ አይደለም ፈታኝ የሆነው ጆሴ ማኩይሳ "በአውሎ ንፋሱ ሳቢያ የመኖሪያ ቤቶቻችን ወድመዋል። የምንጠለልበት የለንም። መልሶ ለመገንባት እንኳ በእጃችን ጥሪት የለም" ሲል የገቡበትን ቀውስ ይገልጻል።

አደጋው ከደረሰ በኋላ የተለያዩ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በሰሜናዊ ሞዛምቢክ ለምትገኘው የቤታ ነዋሪዎች እርዳታ ለማቅረብ በመረባረብ ላይ ይገኛሉ። ለጊዜው ዋንኛ ትኩረታቸው በከፍተኛ ጎርፍ ሳቢያ መፈናፈኛ ያዙ ሰዎችን ነፍስ ማዳን ነው።  ጊፍት ኦፍ ዘ ጊቨርስ የተባለ የደቡብ አፍሪካ የነፍስ አድን ድርጅት ኃላፊ አሕመድ ባህም "በጎርፍ በተጥለቀለቁት አካባቢዎች ያለው ኹኔታ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ውሐው የተኛው አንድ ሁለት፣ ሶስት አሊያም ኪሎ ሜትር መሬት ላይ አይደለም። መፈናፈኛ ያጡ ማኅበረሰቦች ጋ ለመድረስ 30 እና 40 ውሐ የተኛበት መሬት መሻገር ይጠይቃል። ጀልባ አልያም የጭነት መርከብ ይዞ በመሔድ ሰዎቹን ማውጣት የሚታሰብ አይደለም። ፈተና የሆነው የአየር ድጋፍ ማጣታችን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የአካባቢው የአየር ኹኔታ አሁንም እርግጠኛ የሚኮንበት አይደለም። በመጪዎቹ ቀናት ዝናብ ሊጥል እንደሚችል የአየር ትንበያ ባለሙያዎች አስታውቀዋል። በዚምባብዌ እና በሞዛምቢክ መካከል የሚገኝ ግድብ በመከፈቱ የውሐ መጠኑ እንደሚጨምር የሚጠብቁት አሕመድ ባህም

"ከአምስት እስከ አስር ሺሕ ሰዎች በአፋጣኝ ከአካባቢው መውጣት አለባቸው ብዬ እገምታለሁ። በቂ ሔሊኮፕተሮች የሉም። ከፍተኛ ጭነት የመሸከም አቅም ያላቸው ሔሊኮፕተሮች ያስፈልጋሉ" ይላሉ።

የኢዳይ አውሎ ንፋስ 500, 000 ነዋሪዎች ያሏትን የቤይራን ከተማ በጠንካራ ንፋስ እና ኃይለኛ ዝናብ እንዳልነበረች አድርጎ አውድሟታል። እስከ ስድስት ሜትር ከፍታ ያለው ጎርፍ የፈጠረው ይኸው አደጋ በሞዛምቢክ ብቻ ከ400 በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። የሞዛምቢክ መንግሥት፣ የነፍስ አድን ሰራተኞችም ሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ቁጥር ከዚህ በላይ ሊያሻቅብ እንደሚችል ሥጋት አላቸው። የምግብ፣ የንጹህ መጠጥ ውሐ እና መድሐኒት እጦት በአገሪቱ ዜጎች ላይ የከፋ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ የሚል ማስጠንቀቂያም ተሰምቷል።

የዚምባብዌ ሰቆቃ

ኢዳይ በሞዛምቢክ ብቻ አልተገደበም። ድንበር ተሻግሮ በዚምባብዌ እና ማላዊ የከፋ ጉዳት አድርሷል። በዚምባብዌ 259 ሰዎች ሕይወታቸውን ተነጥቀዋል። በቺማኒማኒ መንደር በሚገኝ አንድ የሕክምና ማዕከል የተኛው ታፒዋ ቻንያዎ ሕይወቱ ቢተርፍም ቤተሰቦቹ ግን ዕድል አልቀናቸውም። "እናቴ፣ አባቴ፣ ምግብ ታመጣልን የነበረችውን ጨምሮ ሁለት ታናናሽ እህቶቼ ሁሉ ሞተዋል። አንደኛዋ እሕቴ ትንሽ ልጅ ነበራት" የሚለው ታፒዋ ሐዘን ተጭኖታል።

በዚምባብዌ የኮፓ ሩሲቱ ሸለቆ የምትገኘው የቺማኒማኒ መንደር ከሞዛምቢክ ድንበር አቅራቢያ ትገኛለች። ከመንደሪቱ አጠገብ ከሚገኝ ተራራ የተናደ ዓለት እና የተንሸራተተ ጭቃ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመኖሪያ ቤቶችን ከነባለቤቶቻቸው ሲቀብር የቺማኒማኒ ነዋሪዎች ነፍሳቸውን የማዳን ዕድል አልነበራቸውም። የ42 አመቷ ጃኔ ቺትሱሮ እያላጋ ከወሰዳት ጎርፍ በተዓምር ስትተርፍ አጠገቧ የነበረች ልጇ የት እንደደረሰች አታውቅም። ጃኔ ቺትሱሮ  "ልጄ በፍርስራሹ እስካሁን የት እንደተቀበረች አላውቅም። ምንም ተስፋ የለንም። አልባሳት እንኳ የለንም። የቀረን ፍርስራሽ እና የድንጋይ ቁልል ብቻ ነው" ስትል የአደጋውን መጠን ትገልጻለች።

የ31 አመቷ ፕሬዝ ቺፖሬ ፊቷ በገጠማት አደጋ አብጧል። ግንባሯ እና ጭንቅላቷ ላይ ቁስል ይታያል። ከሕይወቷ በቀር የተረፋት የለም። "የመኖሪያ ቤቴ በጎርፉ ድምጥማጡ ጠፍቶ ከፍርስራሹ ስር ተቀብሬ ነበር። ከእኔ ጋር ተኝታ የነበረችው ልጄ በጎርፉ ተወስዳለች። እኔም ጎርፍ እያላጋ ወስዶኝ ነበር"

የጤና ባለሙያዋ ታንማሪ ዙንጋ እንደሚሉት ሙታምባራ፣ ቺፒንጌ እና ሙታሬ በተባሉ የዚምባብዌ መንደሮች ሕሙማን ወደ ሕክማና ማዕከላት መድረስ ተስኖቿዋል። መንደሮቹን በአቅራቢያቸው ከሚገኙ የጤና ማዕከላት የሚያገናኙ መንገዶች በጎርፉ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። 

ታንማሪ ዙንጋ "መድሐኒቶቻቸው በጎርፍ ተጠርጎ የተወሰደባቸው ሕሙማን መተኪያ ለማግኘት ተቸግረዋል። መድሐኒት እንዳመጣላቸው ማዘዣቸውን የሰጡኝ ነበሩ። መድሐኒቱን ባለፈው ሳምንት አመጣሁ። አርብ እለት ከባድ ዝናብ እየጣለ በመሆኑ ሳይወስዷቸው ቀሩ። መድሐኒቶቹን ለሕሙማኑ ሳላስረክብ በጎርፍ ተወሰዱ። በርካታ የኤች.አይ.ቪ. ሕሙማን አሁን መድሐኒት የላቸውም" ሲሉ ይናገራሉ።

በአደጋው የከፋ ጉዳት እንደደረሰባት ሞዛምቢክ ሁሉ በዚምባብዌም የምግብ ነገር አሳሳቢ ነው። የከፋ ጉዳት የደረሰበትን አካባቢ የጎበኙት የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ዩናይትድ አረብ ኤሚሬትን ጨምሮ ከጎረቤት አገራት እርዳታ ይገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ መንግሥታቸው አገሪቱ በተፈጥሮ ሳቢያ የገጠማትን ቀውስ ለመቋቋም የሚያስችል አቅም ይኖራት እንደሁ ያሉት ነገር የለም። የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ግን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ርብርብ እንዲያደርግ መወትወት ይዘዋል። በቺማኒማኒ መንደር የምግብ ቤት ባለቤት የሆኑት ዳይና ማንዴቫ ግን ፈተና የገጠማቸው ዜጎች ከወዲሁ ወገባቸውን ጠበቅ እንዲያደርጉ መክረዋል።

 

እንደ ሞዛምቢክ ሁሉ በዚምባብዌ የነፍስ አድን ፍለጋው መንገዶች እና የመገናኛ አውታሮች በመውደማቸው ምክንያት ተስተጓጉሏል። ድልድዮች በጎርፍ ተወስደው በአደጋው የተጎዱ አካባቢዎች ከተቀረው የአገሪቱ ክፍል ተቆራርጠዋል። በአስከፊው የአየር ጠባይ ሳቢያ ሔሊኮፕተሮች እንዳሻቸው መብረር አይችሉም። ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በአስጊ ኹኔታ ላይ የሚገኙ ተጎጂዎችን ሲያክሙ የከረሙ የሕክምና ባለሙያዎች ከተራራ በተናደ ዓለት የቆሰሉ ጭምር እንደገጠሟቸው ለDW አስረድተዋል። የጎን አጥንቶቻቸው እና እጆቻቸው የተሰባበሩም ጥቂት አይደሉም። 

የጎረቤት አገራት እርዳታ

በዚህ አደጋ 56 የማላዊ ዜጎች ጭምር ሕይወታቸው አጥተዋል። የጎረቤት አገራት ሞዛምቢክ ፣ ዚምባብዌ እና ማላዊን ለመርዳት እጃቸውን የዘረጉ ሲሆን የታንዛኒያ ጦር 238 ቶን መድሐኒት እና ምግብ በማቅረብ ቀዳሚ ሆኗል።

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማኅማት ተቋማቸው ጉዳት ለደረሰባቸው አገሮች 350,000 ዶላር (308,000 ዩሮ ) እንደሚሰጥ ቃል ገብተዋል። የአውሮጳ ኅብረት በበኩሉ 3.5 ሚሊዮን ዩሮ የሰጠ ሲሆን ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እርዳታ የጫነ አውሮፕላን ወደ አካባቢው ልኳል። በኢዳይ አውሎ ንፋስ ሳቢያ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር በሞዛምቢክ ብቻ ከ1,000 በላይ ይደርሳል 400,000 ከቤታቸው ይፈናቀላሉ የሚል ሥጋት አለ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊዎች እንዳሉት ይኸው አደጋ በሞዛምቢክ 1.7 ሚሊዮን በጎረቤት ማላዊ ደግሞ 920,000 ሰዎች ሕይወት ያምሳል። ባለሙያዎች አፍሪካን የሚጨምረው ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ በታሪኩ ከገጠሙት ሁሉ የከፋው የአየር ንብረት አደጋ ብለውታል። በሰዓት 160 ኪሎ ሜትር የሚጋልበው እና እስከ 20 ጫማ የሚረዝመው አውሎ ንፋስ በመጀመሪያ የመታው ባለፈው አርብ ሞዛምቢክን ነበር። ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን እና የዓለም የምግብ ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በሶስቱ አገራት የተኛው ውሐ እና አደጋ በጤና ተቋማት ያደረሰው ጉዳት በጤናው ዘርፍ ተጨማሪ ሥጋት ሊሆን እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

አደጋው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የአፍሪቃ አገሮች ያላቸውን መሰረተ-ልማት ጥያቄ ውስጥ ከትቶታል። ሞዛምቢክም ሆነች ዚምባብዌ በራሳቸው አቅም መፈናፈኛ ያጡ ዜጎቻቸውን መታደግ፤ ደብዛቸው የጠፉትን መፈለግ እና ሟቾችን መቅበር ተስኗቸዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

Audios and videos on the topic