በሞሮኮ ቡርቃ ታገደ መባሉ የፈጠረዉ ዉዥንብር | አፍሪቃ | DW | 13.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በሞሮኮ ቡርቃ ታገደ መባሉ የፈጠረዉ ዉዥንብር

የሞሮኮ የሃገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሙስሊም ሴቶች ሰዉነታቸዉን ሙሉ በሙሉ የሚሸፋኑበትን ቡርቃ የተባለዉን ልብስ ማምረትም ሆነ ከውጭ ለንግድ ማስገባት አግዷል በሚል ሰሞኑን የተሰማው ዜና ብዙ እያነጋገረ ነዉ። ይህን እገዳ በተመለከተ የመገናኛ ብዙኃን ካሰራጩት ዜና በስተቀር መንግሥት ይፋ ዘገባ አላወጣም። ይህም ነው ዉዥንብር የፈጠረው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:35

የንጉሳዊዉ ቤተሰብ ይፋዊ መግለጫ እስኪሰጥ ይጠበቃል

የሞሮኮ የሃገር ዉስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሙስሊም ሴቶች ሰዉነታቸዉን ሙሉ በሙሉ የሚሸፋኑበትን ቡርካ የተባለዉን ልብስ ማምረትም ሆነ ከውጭ ለንግድ ማስገባት አግዷል በሚል ሰሞኑን የተሰማው ዜና ብዙ እያነጋገረ ነዉ። ይህን እገዳ በተመለከተ የመገናኛ ብዙኃን ካሰራጩት ዜና በስተቀር መንግሥት ይፋ ዘገባ አላወጣም። ይህም ነው ዉዥንብር የፈጠረው።
360ma በተሰኘዉ የኢንተርኔት የዜና ማሰራጫ መረብ ላይ በጋዜጠኞቹ የተለቀቀዉ መረጃ አንድ የሃገር አስተዳደር ሚንስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን ዋቢ ያደረገ ነዉ።  በዚህ መረጃ መሰረት ባለሥልጣኑ  «በንጉሣዊ ስርዓት በምትተዳደረዋ ሞሮኮ ፣ በሁሉም   ወረዳዎችና ቀበሌዎች እንዲሁም ከተሞች ሁሉ ይህን ልብስ ማለትም ቡርካ  ታግዷል»  ብለዋል።  ቡርቃ ሴቶች  መላ ሰውነታቸውን የሚሸፋፍኑበት፣ በዓይን አካባቢ  አጥር የመሰለ ትንሽ ቀዳዳ ያለው ልብስ ነዉ።  በመረጃው መሰረት ነጋዴዎች የቡርካን ንግድ እንዲያቆሙ የተሰጣቸው ጊዜ 48 ሰዓት ብቻ ነበር። እስካሁን ይህ ተግባራዊ ይሁን አይሁን ግን ግልጽ አይደለም። በመሆኑም፣ ብዙዎች እገዳውን በተመለከተ በይፋ አዋጅ መውጣት አለመውጣቱን አጠያይቀዋል። እስካሁን እንደታወቀው አዋጅ አልወጣም። ይህ እገዳ ተጥሎአል የመባሉ ዜና ለምን አሁን ወጣ ለሚለዉ የብዙዎች ጥያቄ ከሞሮኮ የብዙኃን መገናኛዎች የተገኘዉ መልስ   ለደሕንነት ሲባል ነዉ የሚል ነዉ። ምክንያቱም ወንጀለኞች ቡርቃን በመልበስ ወንጀል ለመፈጸም ሊጠቀሙበት ይችሉ ይሆናል። 
በሞሮኮ ማኅበረሰብ ዘንድ ቡርቃ የሚለዉ ስያሜ ይህን ያህል የታወቀ አይደለም። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሞሮኮ ንጉሳዊዉ ቤተሰብ ዘንድ ተለብሶ ስለማይታይ ነዉ። በሰሜናዊ ሞሮኮ የሚኖሩ አንዳንድ ሴቶች  ፊትን እና ሰዉነትን  በጠቅላላ የሚሸፍነዉን ኒቃብ ሲያደርጉ ይታያል።  እንዲህ አይነቱ ልብስ ደግሞ በአብዛኛዉ የሚዘወተረዉ በወግ አጥባቂ ሙስሊሞች ዘንድም ነዉ።  በንጉሳዉያኑ ቤተሰቦች ዘንድም ቢሆን ይታወቃል። አንዴት ሴት እንዲህ ይላሉ ።


 « በኒቃብ ስር የሚደበቁት ሌቦች ብቻ ናቸዉ» ሌላዋ ሴት ደግሞ 
«ሂጃብና ኒቂብ በቅዱስ ቁራን ዉስጥ ተጠቅሶአል »  አሉ  « በሂጃብ የፊት ገጽታና እጅን ይታያል» ።
 ቡርቃ በሞሮኮ ታገደ መባሉን ተከትሎ ኒቃብ የተባለዉ ይህ በሞሮኮ ወግ አጥባቂ ሙስሊሞች ዘንድ የሚዘወተረዉ ልብስ ይታገድ ይሆን? እስካሁን መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነዉ። በሌላ በኩል በሞሮኮ ቡርቃን የሚለብስ ሴት በጣት የሚቆጠ በመሆኑ ለምን እገዳዉ አስፈለገ ብለዉ የሚጠይቁ ጥቂቶች አይደሉም።  የእስልምና ጉዳይ ምሁሩ ካሪም ኢፍራክ እንዲህ ሲሉ ያስረዳሉ።
«ቡርካ የእስልምና ነዉ ። ነገር ግን እጅግ ጥቂቱ ነገሩ ብቻ ነዉ  እስልምና። በማግሪብ ሃገራት ቡርቃን በተመለከተ በባህላዊዉም ሆነ ሃይማኖታዊዉ ፋይዳዉ ይህን ያህል የተስፋፋ አይደለም። ስለዚህ እገዳዉ የሚመለከተዉ በሞሮኮ ሌላ አይነት ርዕዮትን ማስተዋወቅ ለሚፈልጉት  ነዉ። »    
ሌላ አይነት ርዕዮት ማለታቸዉ በሃገሪቱ ከሕገ-መንግሥት በላይ ቅዱስ ቁራንን  በማስቀመጥ እንደቀድሞ ጊዜ  አይነት የእስልምና አመራርን ለማካሄድ የሚፈልጉትን ሰላፊስቶች ማለታቸዉ ነዉ። ይህ ከሆነ እገዳዉ በሞሮኮ አንድ ፖለቲካዊ ርምጃ መሆኑን የሚያመላክት ነዉ። የሞሮኮዉ ንጉሥ ሞሃመድ አራተኛ ከንግሥናቸዉ ሌላ የኃይማኖቱም መሪ ናቸዉ። ንጉሱ እስከዛሬ በተደጋጋሚ  እንደተናገሩት በሃገራቸዉ የለዘብተኛ እስልምና ሃይማኖትና አስተምሮት ብቻ ነዉ  ሕያዉና ተግባራዊ የሚሆነዉ።  
ስለዚህ ቡርቃን ወደ ሞሮኮ ማስገባትም ሆነ በማምረት ለሸቀጥ ገበያ ማቅረብ ስለመታገዱ ስለተሰማዉ ዜና ነዋሪዉ ከተባለ ባሻገር  ሃገሪቱ ከንጉሳዊዉ አስተዳደር በይፋዊ ትንታኔ ሰጥቶ እስኪያረጋግጥ መጠበቅ ግድ ይላታል።  

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic