በምዕራብ ጉጂ ዞን ግጭት ሰዎች መሞታቸው ተነገረ | ኢትዮጵያ | DW | 18.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በምዕራብ ጉጂ ዞን ግጭት ሰዎች መሞታቸው ተነገረ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ነዋሪ በሆኑ የኦሮሞ እና የጌዲኦ ተወላጆች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰዎች መሞታቸውን፤ መቁሰላቸውንና በሺሕዎች የሚቆጠሩ መሰደዳቸውን የአይን እማኞች እና የአካባቢው ባለሥልጣንት ገለጹ። ተፈናቃዮች ግጭቱ እስካሁንም እንደቀጠለ ነው ቢሉም የምዕራብ ጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ግን "ግጭቱ በርዷል" ብለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:58

በግጭቱ ቢያንስ 20 ሺህ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በተቀሰቀሰው ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መሞታቸው እና መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በርካታ ሰዎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ተጠልለው እንደሚገኙም አስረድተዋል።

በጉጂ ዞን ቃርጫ ወረዳ ላለፉት 40 አመታት መኖራቸውን የሚናገሩት አቶ በየነ ዶሪ ግጭቱ በተቀሰቀሰ በማግሥቱ ቤተሰቦቻቸውን ይዘው የመኖሪያ አካባቢያቸውን መልቀቃቸውን ይናገራሉ። መጀመሪያ በጌዲኦ ዞን ጮጪቲ ወደተባለ ቦታ ማምራታቸውን የሚናገሩት አቶ በየነ አሁን በዲላ ከተማ በሚገኝ የሆስፒታል አዳራሽ ከሌሎች በርካታ ተፈናቃዮች ጋር ተጠልለው እንደሚገኙ ይገልፃሉ። የግጭቱን መንስዔም ያስረዳሉ።

በአካባቢው ግጭት መፈጠሩን፤ ሰዎች መሞታቸውን እና መቁሰላቸውን የጉጂ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ዋሪ ገዳ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። የግጭቱን መንስዔ እንደዚሁም የሟቾቹን ትክክለኛ ቁጥር እንደማያውቁ እና ጉዳዩን በማጣራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። 

ግጭቱን ለማብረድ የአካባቢው የአስተዳደር ባለሥልጣናት ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ዋሪ የጸጥታ ኃይሎችም ግጭቱ ወደ ተቀሰቀሰባቸው ቦታዎች መሰማራታቸውን ይናገራሉ። አካባቢያቸውን ለቅቀው በየቦታው የሰፈሩትን በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ ከነዋሪዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን አስረድተዋል። በግጭቱ ምክንያት አካባቢያቸውን ለቅቀው በዞኑ የተለያዩ ቦታዎች የሰፈሩ ሰዎች "20 ሺህ ገደማ ይሆናሉ" ይላሉ። 

በዲላ ተጠልለው ያሉት አቶ በየነ ግን ይህን የምክትል አስተዳዳሪውን ቁጥር አይቀበሉትም። አቶ በየነ በጉጂ ዞን ብቻ ወደ 35 ሺሕ የሚጠጉ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ያስረዳሉ። በደቡብ ክልል ጌዲኦ ዞን ከገደብ እስከ ዲላ ከተማ ባሉ ቦታዎች ሌሎች በርካቶች ሰፍረው እንደሚገኙም ገልጸዋል። በጉጂ ዞን የሚኖሩ የጌዲኦ ተወላጆች ለበርካታ አመታት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ያነሱ እንደነበር የሚያስታውሱት ተፈናቃዩ የአሁኑ ግጭትም የዚያ ውጤት ነው ባይ ናቸው።

የጌዲኦ ተወላጆች ጥያቄን፤ ዶክተር አብይ አህመድ የኦሕዴድ ፅሕፈት ቤት ኃላፊ በነበሩ ወቅት ጉዳዩ ቀርቦላቸው እንደተመለከቱትም አቶ በየነ ያስታዉሳሉ። የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር "የጌዲኦ ሕዝብ በብዛት በሚኖርበት አካባቢ ቋንቋ እና ባሕሉን ማሳደግ ይችላል። መብቱም ነው" ሲሉ ለምዕራብ ጉጂ ዞን ደብዳቤ መፃፋቸውንም ያብራራሉ። ሆኖም የዞኑ አስተዳዳሪዎች ለጥያቄው ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል ሲሉ አቶ በየነ ይከሳሉ። የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ ግን ይኸንን ስሞታ አይቀበሉትም። ባለሥልጣኑ "ከሕብረተሰብ የቀረበ ጥያቄ የለም" ባይ ናቸው። 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ 
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች