1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን ፤ በምዕራብ አዉሮጳ ግዙፉ መስጂድ

ዓርብ፣ ጥቅምት 2 2011

በጀርመንኛ ምኅጻረ ቃል «ዲቲብ» የሚል ስያሚን የያዘዉ የቱርክ እስላማዊ ጉዳይ ኅብረት ማዕከላዊ መስጅድ ፤ በምዕራብ አዉሮጳ ከሚገኙ መስጂዶች ግዙፍ እና እጅግ ዘመናዊ  መሆኑ እየተነገረለት ነዉ።

https://p.dw.com/p/36Nm9
DITIB-Zentralmoschee, Köln
ምስል picture-alliance/dpa/H. Ossinegr

ባንድ ጊዜ 1200 ሠዎችን ይይዛል፤ እጅግ ዘመናዊ መስጂድ ነዉ

በጀርመን ሃገር  ወደ 2000 ሺህ የሚሆን መስጆዶች እንደሚገኙ ጥናቶች ያመለክታሉ። ከአራት ሚሊዮን በላይ የእስልምና እምነት ተከታዮች እንደሚኖሩም ይነገራል። በጎርጎረሳዉያኑ የቀን ቀመር ጥቅምት 3 ቀን ጀርመናዉያን የዉኅደት ቀንን የሚያከብሩበት ቀን ሲሆን፤ በዚሁ እለት ደግሞ በጀርመን ዉስጥ የሚገኙ መስጅዶች ሁሉ ለጎብኝዎቻቸዉ በሮቻቸዉን ክፍት አድርገዉ ይዉላሉ። ታድያ የመስጂዱ ተጠሪዎች  ኢማሞች እንዲሁም ምዕመናን እንግዶችን በመቀበል፤ ስለመስጂዱ ሥራ፤ ስለሙስሊም የፀሎት ሥነ-ስርዓት፤ መስጂዱ ስለሚያሰባስባቸዉ  ምዕመናን፤ መስጂዱ ለማኅበረሰቡ ስለሚያበረክተዉ አስተዋፅኦ፤ እንዲሁም ሥለ እስልምና አስተምሮ ለጎብኝዎቹ ማብራርያን ይሰጣሉ።  እንደወትሮዉ ሁሉ በዚህ ዓመትም በጀርመን የሚገኙ መስጂዶች ሁሉ ለጎብኝዎቻቸዉ በሮቻቸዉን ክፍት አድርገዉ ነዉ የዋሉት። እለቱ በጎርጎረሳዉያኑ ጥቅምት 3፤ ማለትም ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት መስከረም 23 እለት ነበር የዋለዉ። የዘንድሮዉ የጀርመን ዓመታዊዉ የመስጂድ ጉብኝት ከወትሮዉ ለየት ያለ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ራድዮ ጣብያችን ከሚገኝበት አቅራብያ በሚገኘዉ ኮለኝ ከተማ በምዕራብ አዉሮጳ  ዘመናዊ እና ዉብ የሆነ ግዙፍ መስጊድ በይፍ ከተመረቀ ከቀናቶች በኋላ መሆኑ ነበር።  

Gebetssaal der Kölner Moschee
ምስል Picture alliance/dpa/M. Becker

በቱርክ መንግሥት ድጋፍ እንደሚተዳደር የተነገረለት እና በጀርመንዋ ኮለኝ ከተማ የታነፀዉ ይህ ዉብና ግዙፍ መስጊድን መርቀዉ የከፈቱት የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረቺብ ታይብ ኤርዶጋን ነበሩ። ላለፉት ወራቶች ሃገራቸዉ ከጀርመን ጋር ፖለቲካዊ ዉዝግብ  ዉስጥ የነበረችዉ የቱርክ ፕሬዚዳንት ረቺብ ታይብ ኤርዶጋን፤ ጀርመንን በይፋ ለመጎብኘት በርሊን ደማቅ አቀባበል ከተደረገላቸዉ በኋላ በጉብኝታቸዉ መጨረሻ ወደ ኮለኝ ከተማ አቅንተዉ ኤርንፌልድ ቀበሌ ዉስጥ የታነፀዉን ዘመናዊ መስጂድ በይፋ በመረቁበት ወቅት «የአሁኑ ጀርመን ጉብኝቴ  እጅግ የሰመረ ነበር» ሲሉ ነበር የተናገሩት። አዲሱ መስጂድም «የጀርመን እና የቱርክን ወዳጅነት ያጠናክረል።»  ብለዋል። 

Deutschland Türkischer Präsident Erdogan in Köln
ምስል Reuters/Handout Presidential Press Office/K. Ozer

በጀርመንኛ ምኅጻረ ቃል «ዲቲብ» የሚል ስያሚን የያዘዉ የቱርክ እስላማዊ ጉዳይ ኅብረት ማዕከላዊ መስጅድ ፤ በምዕራብ አዉሮጳ ከሚገኙ መስጂዶች ግዙፍ እና እጅግ ዘመናዊ  መሆኑ እየተነገረለት ነዉ። በዚህም የሃይማኖቱን ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ያስደሰተዉ የሕንጻዉ አቀማመጥ፤ ዘመናዊነት የተመልካችን፤ የጎብኝዎችን ቀልብ መሳቡ ተመልክቶአል።  ግንባታዉ  ወደ 30 ሚሊዮን ይሮ ወጭን ጠይቆአል። በሁለት ጀርመን የሕንጻ ምሕንድስና ባለሞያዎች የታነፀዉ ዘመናዊዉ መስጂድ ባለፈዉ ሁለት ሳምንት በቱርኩ ፕሬዚደንት በይፋ ተመረቀ እንጂ ፤ ሥራን የጀመረዉ ባለፈዉ ዓመት በጎርጎረሳዉያኑ 2017 የረመዳን ወቅት ነበር። በጀርመን ኮለኝ አካባቢ ሲኖሩ ወደ 17 ዓመት እንደሆናቸዉ የሚናገሩት መሃመድ ሁሴን «ዲቲብ» የተሰኘዉን በኮለኝ የተገነባዉን መስጂድ ወደ ሦስት ጊዜ ሄደዉበታል።  ግንባቱ ከመጀመሩ በፊት በከተማዋ አስተዳደር የግንባታ ለማግኘት ብዙ ጭቅጭቅም እንደነበረበት ያስታዉሳሉ።

Pfaffenhofen Moschee
ምስል Getty Images/J. Simon

በአዉሮጳ የሞስኮ መስጂድ ከተባለዉ በሩስያ ርዕሰ ከተማ ዉስጥ ከሚገኘዉ መስጂድ ለጥቆ በግዙፍነቱ አሁን ኮለኝ በይፋ የተመረቀዉ «ዲቲብ» መስጂድ ሁለተኛ እንደሆነ ተመልክቶአል። የሞስኮዉ መስጂድ ለመጀመርያ ጊዜ የታነፀዉ በጎርጎረሳዉያኑ 1904 ነበር። ከዝያም ነዉ ከ 100 ዓመት በኃላ አሁን ግዙፍና ዘመናዊ ሆኖ የተገነባዉ ከጎርጎረሳዉያኑ 2007 እስከ 2015 ዓም ሆኖ በተጠናቀቀበት ዓመት በይፋ ተመርቆ ሥራዉን ጀምሮአል።

Moschee-Eröffnung in Köln
ምስል DW/G. Acer

55 ሜትር ርዝመት ያላቸዉ ሁለት ሚናራዎችን ያቀፈዉ ግዙፉ የኮለኙ « ዲትብ » መስጂድ በ 16ሺህ 500 ስኬር ወለል ላይ ያረፈ፤ ባለ አምስት ፎቅ ሕንጻን ያካተተ ነዉ። በሕንፃ ዉስጥ ሰፋፊ አዳራሾች ፤ ቤተ-መጻሕፍት የትምህርት እና የዉይይት ክፍሎች፤ ሱቆችና ፤ ሌሎች ከመስጂዱ ሥራ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ሱቆችንም ይዞአል።  « ዲቲብ» መስጂድ በምዕራብ አዉሮጳ ግዙፍ ይባል እንጂ በሞስኮ ሩስያ ላይ ያለዉን መስጂድ እንደማያክል ከለን አቅራብያ ነዋሪ የሆኑት አቶ መሃመድ ሁሴን ተናግረዋል።

ሙሉዉን ጥንቅር የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ