በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር የመከላከያ ሠራዊት ተሰማራ | ኢትዮጵያ | DW | 18.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር የመከላከያ ሠራዊት ተሰማራ

በአማራ ክልል ምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ለወራት የዘለቀዉን ግጭት ለማስቆምና የአካባቢዉን ሰላም ለማስከበር የሀገር መከላከያ ሠራዊት በቦታዉ መሰማራቱን የክልሉ መንግሥት ገለፀ። የመከላከያ ሠራዊቱ በቦታዉ እንዲሰፍር የተደረገው የክልሉ መንግሥት ባቀረበዉ ጥያቄ መሠረት መሆኑም የክልሉ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት አስታውቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:21

«በግጭቱ 50 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል»

በምዕራብ እና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በርካታ የሰዉ ሕይወትና ንብረት የጠፋበት ግጭት ከተቀሰቀሰ ወራት ተቆጥረዋል። ይህንን ግጭት ለማስቆም በክልሉ መንግሥት እና በፀጥታ ኃይሎች ጥረት ቢደረግም ችግሩ እየተባባሰ መጥቶ ብዙዎችን ለሞት ወደ 50 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸዉ ለመፈናቀል እንዳበቃቸዉ ነው የክልሉ የመንግሥት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰማኸኝ አስረስ ለDW የገለፁት።

በመሆኑም ችግሩ ውስብስብ እንዲሁም ከግጭት ይልቅ የጦርነት ባህሪ እየያዘ በመምጣቱና ከክልሉ መንግሥት አቅምም በላይ በመሆኑ በአካባቢዉ አስተማማኝ ሰላም እስኪገኝ ድረስ የመከላከያ ሠራዊት እገዛ እንዲያደርግ ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ መቅረቡን ኃላፊዉ አስረድተዋል።

በጥያቄው መሠረትም ከትናንት ጀምሮ ግጭቱ በተከሰተባቸዉ አካባቢዎች የ33ኛዉ ክፍለ ጦር  የሠራዊት አባላት  መሰማራታቸዉንም አመልክተዋል።

እንደ ሃላፊዉ ከዚህ ቀደም 24ኛዉ ክፍለ ጦር በቦታዉ ተሰማርቶ የነበረ ቢሆንም በታኅሣስ ወር 2011 ዓ/ም መተማ አካባቢ በመከላከያ ሠራዊት እና በነዋሪዎች መካከል የሰው ሕይወት የጠፋበት ግጭት ከተከሰተ ወዲህ  ሠራዊቱ ከቦታዉ መነሳቱን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት  የተሰማራዉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከመደበኛዉ ሕግ የማስከበር እና ሰላምን የማረጋገጥ ሥራ በተጨማሪ  ከክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር የተወሰኑ ክልከላዎችን ያካተተ ሥራ እንደሚሠራም ገልፀዋል።

በዚህም መሠረት በፀጥታ ኃይሉ አስተማማኝ ሰላም እስኪገኝ ድረስ ከጎንደር-መተማ መስመር ከመንገድ 5 ኪ.ሜ ርቀት በቡድንም ይሁን በግል የጦር መሳሪያ  ይዞ መንቀሳቀስ አይቻልም። በሁመራ መስመርም በተመሳሳይ ክልከላ የተደረገ ሲሆን፤ በጎንደር ከተማ ደግሞ ከፀጥታ አካላት ውጭ ሕጋዊ ፈቃድ ያለዉም ቢሆንም ማንኛውም ሰው መሣሪያ ታጥቆ እንዳይንቀሳቀስ እገዳ ተጥሏል ሲሉ አቶ አሰማኽኝ አስረድተዋል። ያም ሆኖ ግን በአካባቢዉ የአስቸኳይ ጊዜ ታውጇል ወይም የኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል ማለት እንዳልሆነ አረጋግጠዋል።

ከእነዚህ ክልከላዎች ዉጭ ሕግን የተከተለ ፣ ሰላምና መረጋጋቱን የሚያግዝና ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ቅድሚያ የሰጠ ሥራ ይሰራልም ብለዋል። እነዚህን  ክልከላዎች ተላልፎ የተገኘና በፀጥታ መደፍረስ ተሳትፎ ያደረገ ግለሰብም ይሁን ቡድን  እንደ ኃላፊዉ ጠንከር ያለ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድበታል።

እንደ አማራ ክልል ኮምኒኬሽን ፅሕፈት ቤት፤ በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በተከሰተዉ ግጭት የተፈናቀሉ 50 ሺህ ሰዎችን ጨምሮ በክልሉ ከ90 ሺህ በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል። ከሰላምና ማረጋጋት ሥራዉ በተጨማሪ እነዚህን ተፈናቃዮች በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ወደ ቤት ንብረታቸዉ ለመመለስና ለማቋቋም መታቀዱም ተገልጿል። ነገር ግን ሥራዉ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚፈልግ  በመሆኑ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ርብርብ እንዲያደርግ የክልሉ መንግሥት ጥሪ አቅርቧል።

 

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

 

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ

 

Audios and videos on the topic