1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምስራቅ ሸዋ ዞን ግጭትና ግድያ 

ሐሙስ፣ መጋቢት 22 2014

ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ውስጥ በከባድ ጦር መሣሪያ ጭምር በታጀበ ግጭት በርካቶች መሞታቸው እና በብርቱ መቁሰላቸው ተገለጠ። በውጊያው የፌዴራል ፖሊሶችን ጨምሮ ቢያንስ 26 የመንግስት ታጣቂዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውም ተዘግቧል።  ግድያው የተፈጸመው ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ መሆኑ ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/49ITy
Karte Sodo Ethiopia ENG

የምስራቅ ሸዋና ሰሜን ሸዋ ባለስልጣናት መልሶች ይቃረናሉ

ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ውስጥ በከባድ ጦር መሣሪያ ጭምር በታጀበ ግጭት በርካቶች መሞታቸው እና በብርቱ መቁሰላቸው ተገለጠ። በውጊያው የፌዴራል ፖሊሶችን ጨምሮ ቢያንስ 26 የመንግስት ታጣቂዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውም ተዘግቧል።  ግድያው የተፈጸመው ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ከ8-9 ሰዓት ገደማ መሆኑን የአከባቢው ባለስልጣናት ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል። ስለ ግጭቱ መነሻ እና የግድያው አፈፃፀም ግን የምስራቅ ሸዋ እና ሰሜን ሸዋ ባለስልጣናት መልስ እጅግ የተቃረኑ ናቸው። ሥዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ተጨማሪውን ልኮልናል።

ከመታሃራ ከተማ ወደ ቦሰት ወረዳ ወለንጪቲ ከተማ በሚወስደው መንገድ 25 ኪ.ሜ. ገደማ ላይ እንደሚገኝ በተገለፀው ቆርኬ/አውራ ጎዳና በተባለ ስፍራ ላይ ከ100 በላይ የሚሆኑ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ከወለንጪቲ ወደ መታሃራ ኢላላ ካምፕ በመመለስ ላይ ሳሉ፤ «ዝግጅት ባደረገ» በተባለ ታጣቂ ቡድን የፀጥታ ኃይሉ ላይ ርምጃው መወሰዱን በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ ተናግረዋል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ቦሰት ግን በዚህ የሚስማሙ አይመስልም፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ አሞራ ቀበሌ አውራ ጎዳና ባሉት ስፍራ የተፈጸመው የክስተቱ መነሻው ነዋሪዎች ላይ የተኮሱ የፀጥታ አካላት ልብስ የለበሱ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪው አቶ አባቡ ግን ከዚህ በፊትም የአስተዳደር ውዝግብ ነበረበት ባሉት በዚህች ስፍራ ጥቃቱ የፌዴራል ፖሊስ አባላትም ጭምር ላይ ያነጣጠረ ነው ይላሉ።

አከባቢው በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር እንዲሆን ከተወሰነ ሰንብቷል መባሉን የሚጋሩት የምንጃር ሸንኮራ ወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ቦሰት፤ ሕዝቡ ሁሌም በሚፈጠር ግጭት ዋጋ እየከፈለ በመሆኑ እልባት ያሻዋልም ነው ያሉት። ባለስልጣናቱ አከባቢው ላይ አሁን የአገር መከላከያ ሰራዊት ገብቶ መረጋጋት መፈጠሩንና የጂቡቲ አውራ ጎዳናም መደበኛ አገልግሎት ወደ መስጠት መመለሱን ተናግረዋል።

ሥዩም ጌቱ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ