በምሥራቅ አፍሪካ የዘመናዊ ሆስፒታል ግንባታ | አፍሪቃ | DW | 14.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በምሥራቅ አፍሪካ የዘመናዊ ሆስፒታል ግንባታ

በዓለም ዙሪያ ከ 300 አባላት በላይ ያሉት የኢትዮጵያ አሜሪካ የዶክተሮች ቡድን ከ 100 ሚልዮን ዶላር በሚበልጥ ወጭ አዲስ አበባ ውስጥ በምሥራቅ አፍሪቃ ግዙፍ እና ዘመናዊ የተባለ የህክምና ማዕከል ግንባታ በተሳካ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ተገለፀ::

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:48

በምሥራቅ አፍሪካ የዘመናዊ ሆስፒታል ግንባታ

የኢትዮጵያውያኑ የዶክተሮች ቡድን አባል ዶክተር አለማየሁ ሩጋ ለዶቼቨለ እንደገለጹት በአባላቱ መዋጮ እና በባንኮች ብድር በ 45 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ የሚገነባው ከውጭ ለሚመጡ ታካሚዎች ማረፊያ ሆቴል እና የሰራተኞች መኖሪያ ህንጻን ያካተተው ዘመናዊው ሆስፒታል በህክምና እጦት የሚሰቃዩ ምንም የገቢ ምንጭ የሌላቸውንም የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርግበት ስልት ነድፏል :: በጀርመን የግል ክሊኒኮች ባለቤት የሆኑት ዶክተር አለማየሁ ከአሁን ቀደም ሃገር ውስጥ ተመሳሳይ የህክምና ማዕከል በግላቸው ከፍተው ህብረተሰቡን ለማገልገል ያቀረቡት ጥያቄ በብቃት ማረጋገጫ የቢሮክራሲ ውጣውረድ አለመሳካቱ እንዳሳዘናቸውም ገልጸዋል :: በኢትዮጵያ የመንግስት መስሪያቤቶች የሚታየው እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ አስቆራጭ አሰራር ከፍተኛ እውቀት እና ልምድ ያካበቱ አያሌ በውጭ ሀገራት የሚገኙ ምሁራን ሕዝብ እና ሃገራቸውን እንዲያገለግሉ አያደፋፍርም ሲሉ ሃላፊው ይተቻሉ ::

 

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ከሶስት መቶ በላይ ስፔሻሊስት ዶክተሮችን እና ሌሎችንም የህክምና ባለሙያዎች በስሩ ያቀፈው የኢትዮ-አሜሪካ የዶክተሮች ቡድን በተለይም ዳግም በአዲስ መልክ ከተዋቀረ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሳይማር ያስተማረውን ማህበረሰብ ለማገልገል እና የእውቀት ሽግግርን በሃገራችን ለማስረጽ በጤና አገልግሎቱ ዘርፍ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱ ይነገርለታል :: በውጭው አለም በታወቁ የምርምር ማዕከሎች የህክምና ተቋማት እና ሥመጥር ሆስፒታሎች የሚያገለግሉት እነዚሁ የሙያ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በአንድ ጥላ ስር የሚያስተባብራቸውን የሙያ ማህበር ከመሰረቱ በኋላ ለዘመናት ያካበቱትን እውቀት እና መዋዕለ ንዋያቸውን ለሃገር እድገትና ለህዝባቸው ጥቅም ሊያውሉ የተግባር እንቅስቃሴ በቁርጠኝነት ጀምረዋል:: የኢትዮ-አሜሪካ ዶክተሮች ቡድን አባል ዶክተር አለማየሁ ሩጋ ስለ ማህበሩ ውጥን እና ግብ እንዲህ ይገልጻሉ ::

ዛሬ እንደ ኬናያ ባሉ የአፍሪቃ ሃገራት ለዲያስፖራ መያተኞች የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ሃገራቸው ገብተው የሙያ ክህሎታቸውን እና ገንዘባቸውን ለሃገር እና ህዝብ ጥቅም እንዲያውሉ ከማድረግ አልፎ የሃገራቱንም የምጣኔ ሃብት እድገት በከፍተኛ ፍጥነት ማሳደጉ ነው የሚነገረው:: በውጭው ዓለም የሚኖሩ ከ 300 በላይ የህክምና ባለሙያዎችን በአባልነት ያቀፈው የኢትዮ-አሜሪካ የዶክተሮች ቡድንም ከፍተኛ እውቀት እና ልምድ ያካበቱ ሙያተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ እየተጓዙ በሆስፒታሎች ጤና ተቋማት እና ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር የንድፈ ሃሳብ እና የተግባር ነጻ የእውቀት ሽግግር በማድረግ ላይ ይገኛሉ ይላሉ ዶክተር አለማየሁ ::

የኢትዮ-አሜሪካ ዶክተሮች ቡድን ሌላም ሃገርን እና ወገንን የሚያኮራ ተግባር በማከናወን ላይ ይገኛሉ :: አዲስ አበባ ውስጥ በሃያት አካባቢ ከመንግስት በተረከቡት 45 ሺህ ኳድራት ሜትር "ኤክሰለንስ ሜዲካል" ሴንተር የሚል ስያሜ የተሰጠውን በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ እና ዘመናዊ የህክምና መስጫ ማዕከል ከ 100 ሚልዮን ዶላር በሆነ ወጭ በመገንባት ላይ መሆኑን የቦርዱ የአውሮፓ ሃላፊ ዶክተር አለማየሁ ገልጸውልናል :: ካንሰርን ጨምሮ ሁሉንም ህመሞች በብቃት እና በጥራት ለማከም እቅድ የተያዘለት ይኸው ዘመናዊ ሆስፒታል ስራውን ሲጀምር በውጭ ምንዛሪ እጦት ምክንያት ውጭ ሄደው ለመታከም የሚንከራተቱት አያሌ ህሙማንን እና ከፍለው ለመታከም አቅሙ የሌላቸውን ወገኖቻች ጭምር በመርዳት ረገድ የጎላ ሚና እንደሚኖረው ሃላፊው ያስረዳሉ ::

በጀርመን ትልቁ ከተማ ፍራንክፈርት ሙያዊ ክህሎታቸውን በከፍተኛ የትምህርት ተቋም አዳብረው የግል የህክምና መስጫ ክሊኒኮች እዛው ፍራንክፈርት ውስጥ ከፍተው እንዲሁም ባለሙያዎችን ቀጥረው ኢትዮጵያውያንን የሚያኮራ ተግባር የሚከውኑት የኢትዮጵያውያን ዶክተሮች ቡድን አባል ዶክተር አለማየሁ ለዘመናት በውጭው አለም ያካበቱትን ሙያና እውቀት ሃገራቸው ውስጥ ለህብረተሰባቸው ለማበርከት የነበራቸው ውጥን አያሌ ፈተና እና እክል እንደገጠመው ነው የሚናገሩት :: በጀርመን የሙያ ብቃታቸው ተረጋግጦ የግል ክሊኒክ እንዲከፍቱ ፈቃድ ያገኙት ባለሙያው በተወለዱባት የኢትዮጵያ ምድር ገብተው መሰል ተቋም ለመክፈት ያቀረቡት የብቃት ማረጋገጫ ጥያቄ በቢሮክራሲ ውጣውረድ አለመሳካቱን አስታውሰው ይህ ዓይነቱ ችግር በጊዜ እስካልተቀረፈ ሌሎችም በዲያስፖራ የሚገኙ ሥመጥር ሙያተኞች ገንዘብ እና እውቀታቸውን ለሃገር እና ህዝብ ጥቅም ለማዋል የሚኖራቸውን ጉጉት እንደሚያጨልመው አሳስበዋል ::

በኢትዮጵያ በጤና አገልግሎቱ ዘርፍ የሚታየውን ችግር ያቃልላል ተብሎ ከፍተኛ እምነት የተጣለበት እና በውጭው ዓለም ከፍተኛ ዕውቀት እና ልምድ ባካበቱ ኢትዮጵያውያን የህክምና ባለሙያዎች አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው ግዙፍ እና ዘመናዊው የሆስፒታል ግንባታ ከ 4 ዓመታት በኋላ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ አሜሪካ ዶክተሮች ቡድን ገልጿል ::

እንዳልካቸዉ ፈቃደ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic