በሜዴትራንያን ባህር የቀጠለው የስደተኞች ሞት  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 27.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

በሜዴትራንያን ባህር የቀጠለው የስደተኞች ሞት 

ስደተኞች የሜዴትራንያንን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮጳ እንዳይገቡ የህብረቱ የባህር ድንበር ጠባቂ ፍሮንቴክስ ጥበቃውን አጠናክሯል። በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይም ዘመቻ እየተካሄደ ነው። ኢጣልያ የምትረዳቸው የሊቢያ የፀጥታ ኃይላት ስደተኞችን አሳፍረው ወደ አውሮጳ ለመሄድ የሚሞክሩ ጀልባዎችን ወደ ሊቢያ እየመለሱ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:04

የስደተኞች ሞት

የሜዴትራንያን ባህር አቋርጠው አውሮጳ የሚሻገሩ ስደተኞች ቁጥር ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነጻጻር በጣም ቀንሷል። በጉዞ ላይ ህይወታቸው የሚያልፈው ስደተኞች ቁጥር ግን አሁንም ከፍተኛ ነው። በአብዛኛው ከሊቢያ ተነስተው በሜዴትራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮጳ የሚሻገሩ ፍለሰተኞች ቁጥር በያዝነው በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓም በእጅጉ ቀንሷል። ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ጉዳይ ድርጅት በምህጻሩ አይ ኦ ኤም በቅርቡ እንዳስታወቀው ባለፉት 3 ወራት በዚህ የጉዞ መስመር አውሮጳ መድረስ የቻሉት ፍልሰተኞች ቁጥር አምና በተመሳሳይ ወቅት አውሮጳ ከገቡት ጋር ሲነፃጸር በጣም ይራራቃል። ከጥር አንስቶ እስከ መጋቢት አጋማሽ በሜዴትራንያን ባህር አድርገው 6ሺህ ፍልሰተኞች ኢጣልያ 3900 ግሪክ 2800  ደግሞ ስጳኝ ገብተዋል። በኢጣልያ የዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም ቃል አቀባይ ፍላቭዮ ዲ ጂያኮሞ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት አምና በዚህ ወቅት ኢጣልያ የገቡት ስደተኞች ቁጥር 20 ሺህ ነበር።  ባለፈው ዓመት በአጠቃላይ ኢጣልያ መድረስ የቻሉት ቁጥር ደግሞ 120 ሺህ ነው። የፍልሰተኞች ቁጥር እጅግ መቀነስ ብዙ ትኩረት ስቧል። ሆኖም እንደ ቃል አቀባዩ ወደ አውሮጳ የሚገቡት  ቁጥር ሲቀንስ በጉዞ ላይ የሚሞቱት ቁጥር ግን አሁንም ከፍተኛ ነው።
«በዚህ ዓመት 358 ሰዎች በሜዴትራንያን ባህር ላይ ህይወታቸው አልፏል። ባለፈው ዓመት ደግሞ 580 ናቸው የሞቱት። የሚሞቱ ቁጥር ወደ አውሮጳ ከሚገቡት ጋር በመቶኛ ሲነፃጸር እየጨመረ ነው። ይህ ደግሞ አሳሳቢ ነው። እርግጥ ነው ይሄ ጉዳይ በጣም ያሳስበናል።»

የአውሮጳ ህብረት በሜዴትራንያን ባህር በኩል የሚደረገውን ህገ ወጥ የሚለውን ስደት ለማስቆም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። ስደተኞች የሜዴትራንያንን ባህር አቋርጠው ወደ አውሮጳ እንዳይገቡ የህብረቱ የባህር ድንበር ጠባቂ ፍሮንቴክስ ጥበቃውን አጠናክሯል። በህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ላይም ዘመቻ እየተካሄደ ነው። ኢጣልያ

የምትረዳቸው የሊቢያ የፀጥታ ኃይላት ስደተኞችን አሳፍረው ወደ አውሮጳ ለመሄድ የሚሞክሩ ጀልባዎችን ወደ ሊቢያ እየመለሱ ነው። በነዚህ እርምጃዎች ስደተኞች ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ ከመከላከሉ ጋር በሜዴትራንያን ባህር ላይ የሚደርስ የስደተኞችን ሞት መቀነስ ይቻላል የሚል ተስፋ ነበር። ይሁን እና አሁንም ስደተኞች በሜዴትራንያንን ባህር ላይ መሞታቸው አልቆመም። በሜዴትራንያን ባህር የስደተኞችን ሞት ማስቀረት ያልተቻለበት ምክንያት ምን ይሆን? በኢጣልያ የአይ ኦ ኤም ቃል አቀባይ ፍላቭዮ ዲ ጂያኮሞ 
«እኔ እንደሚመስለኝ በአሁኑ ጊዜ በሜዴትራንያን ባህር ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ የህይወት አድን መርከቦች ቁጥር ቀንሷል። ከዚሁ ጋርም በሜዴትራንያን ባህር ላይ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ቁጥር እየቀነሰ ነው። ድርጅቶቹ ባለፉት 8 ወራት ባጋጠሟቸው ችግሮች ምክንያት ሥራቸውን እያቋረጡ ነው። በጎርጎሮሳዊው 2014 ከፍተኛ የህይወት አድን ሥራ ያከናወነው የኢጣልያው ማሊኖስትሩም አሁን የለም። እናም አሁን በዓለም አቀፍ የውሐ ክልል ላይ ተጨማሪ መርከቦች ያስፈልጉናል።»
በሜዴትራንያን ባህር ላይ ሲጓዙ ለመስጠም አደጋ የሚጋለጡ ስደተኞችን ለመርዳት በዓለም አቀፍ የውሐ ክልል ላይ መርከቦቻቸውን አስማርተው ከነበሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብዙዎቹ አገልግሎታቸውን አቋርጠዋል። ድርጅቶቹ ሥራቸውን ያቆሙት ካለፉት 8 ወራት ወዲህ በነጻነት መሥራት ስላልቻሉ እና ጫናውም ስለበረታባቸው ነው።

ከሁሉም የሚጠነክረው ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ተቆጣጣሪዎች የሚሰነዘርባቸው ዛቻ እና ጥቃት መሆኑን ይናገራሉ። በዚህ ሰበብ መርከቦቻቸውን ከአካባቢው ካነሱት መካከል የፈረንሳዩ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ድርጅት MSF ፣የብሪታንያው የህጻናት አድን ድርጅት፣ እንዲሁም የጀርመናውያኑ ሲ ዋች የተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ይገኙበታል። ጫናውን ተጋፍጠው አሁንም በሜዴትራንያን ባህር ላይ የህይወት አድን ስራቸውን የቀጠሉም አሉ። ከመካከላቸው አንዱ Proactiva Open Arms የተባለው የስጳኙ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው። ድርጅቱ

ባለፈው ሳምንት ከሜዲቴራንያን ዓለም አቀፍ የውሐ ክልል 218 ስደተኞችን ከመስጠም ከታደገ በኋላ ፣ሰዎቹን ለሊቢያ የባህር ጠባቂዎች እንዲያስረክብ ተጠይቆ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሠራተኞቹ ከባድ የግድያ ዛቻ ደርሶባቸዋል። የድርጅቱ ሠራተኞች ከሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ችግር ሲገጥማቸው የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ይሁን እና የድርጅቱ ቃል አቀባይ አናቤል ሞንተስ እንዳሉት እንደ ዛሬ ሳምንቱ ዓይነት ዛቻ ግን ደርሶባቸው አያውቅም።
«ተመሳሳይ ሁኔታዎች ደርሰውብናል። እንደዚህ ዓይነት ከባድ ችግር ግን አጋጥሞን አያውቅም። በሌሎች አጋጣሚዎች ሊቢያውያን አስፈራርተውናል። ጥቃትም አድርሰውብናል። ወደ እኛ በጣም ተጠግተው ወደ ሰማይ ተኩሰዋል። ሆኖም እንደ አሁኑ ከልክ ያለፈ ሁኔታ ላይ ደርሰን አናውቅም። እንገድላችኋለን እያሉ ነበር የሚዝቱብን» 
ፕሮአክቲቭ ኦፕን አርምስ እንደሚለው የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ባለፈው ሳምንት በሰጡት ትዕዛዝ እና በሰነዘሩት ዛቻ  ድርጅታቸው የሚያካሂደውን የህይወት አድን ሥራ በእጅጉ ተፈታትነዋል። በነርሱ ትዕዛዝ ምክንያት በጣም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተከስተዋል ይላሉ የድርጅቱ መሥራች እና ሃላፊ ኦስካር ካምፕስ።

«ማስፈራራታቸው ብቻ አይደለም። የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች  የህክምና ባልደረቦቻችን እርዳታ ያደርጉላቸው የነበሩ ወደ መርከባችን ያስገባናቸውን ሴቶች እና ህጻናትን እንድንሰጣቸው አዘውን ነበር። ይህ ሲሆን ሁሉም ተረበሹ። ከመርከቡ ወደ ባህር ይወረወሩ ጀመር። ወንዶች ባሎች እና ወንድሞች እየዘለሉ ባህር ውስጥ ገቡ። መጮህ ጀመሩ ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ሆነ። ሰዎቹን ማዳኑን ማንም ያድርገው ማን ፣ቅድሚያ  የምንሰጠው ህይወት ማዳን እና ሰዎችን መርዳት ነው።»     
Proactiva Open Arms ከዓለም አቀፍ የባህር ክልል የታደጋቸውን 218 ሰደተኞች ለሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች አሳልፎ ሳይሰጥ ወደ ኢጣልያ ወስዷል። የመርከቡ ሠራተኞች  ፍቃድ ባለማግኘታቸው ስደተኞቹን ወደ ኢጣልያዋ ፖትሳሎ ወደብ ለመውሰድ ሦስት ቀናት መጠበቅ ነበረባቸው። መርከቧም ኢጣልያ ስትደርስ በቁጥጥር ስር ውላለች። ሠራተኞቹም በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠርጥረው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ኢጣልያ አስታውቃለች። አይኦም እንደሚለው ይህን የመሳሰሉት እርምጃዎች በሜዴትራንያን ባህር ላይ የሕይወት አድኑ ሥራ እንዲቀንስ በማድረጋቸው አሁንም ሰዎች መሞታቸው ቀጥሏል። እርምጃው ወደ አውሮጳ የሚገቡትን ስደተኞች ቁጥር ቢቀንስም ስደተኞች ካለፈቃዳቸው ወዳልተረጋጋችው ሊቢያ እየተመለሱ ለተጨማሪ  ስቃይ እና ግፍ መዳረጋቸው እንዲቀጥል አድርጓል ። የአይኦ ኤሙ ዲ ጂያኮሞ ይህን ፣ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ አውሮጳ ከሚመጡት ኤርትራውያን ስደተኞች ይዞታ

መረዳት ይቻላል ይላሉ። 
«በአሁኑ ጊዜ ወደ አውሮጳ የሚመጡት ስደተኞች በተለይም ኤርትራውያን ከከዚህ ቀደሞቹ በተለየ የተጎዱ መሆናቸውን እናያለን። እንደሚታወቀው ኤርትራውያን እና ሶማሌዎች ገንዘብ ሊከፍሉላቸው የሚችሉ ቤተሰቦች እሏቸው ተብሎ ስለሚገመት ህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች እና ሚሊሽያዎች በሚቆጣጠሯቸው ይፋ እውቅና ባልተሰጣቸው የማጎሪያ ማዕከላት ቁም ስቅል ይፈፀምባቸዋል።  ስደተኞቹን ለመልቀቅ በአውሮጳ የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲልኩ በመጠየቅ ያሰቃዩዋቸዋል። ለምሳሌ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ዓለም አቀፍ መርከብ ታድጓቸው ሲሲሊ ከገቡ ኤርትራውያን አንዱ ሊቢያ ውስጥ በደረሰበት ቁም ስቅል በመጎዳቱ ሲሲሊ ከደረሰ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ህይወቱ አልፏል። እናም ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነው»   
እናም በአሁኑ ጊዜ የአውሮጳ ህብረት እና ኢጣልያ ስደተኞችን ከዚህን መሰሉ አደጋ ለመጠበቅ በአጠቃላይ የስደተኞችን ሞት ለማስቀረት የእስካሁኑን አካሄድ ማስተካከል ይገባቸዋል ይላሉ ዲ

ጂያኮሞ ። ድርጅታቸው ለችግሩ መፍትሄ የሚላቸውንም ተናግረዋል።
«ከሁሉ አስቀድሞ ለስደተኞች ህጋዊውን መንገድ መክፈት አስፈላጊ ነው። ይህ መደረግ ያለበት ተገን ለሚፈልጉ ስደተኞች ብቻ ሳይሆን ሥራ ለሚፈልጉ ፍልሰተኞችም ነው። አሁን ፍልሰተኞች በህጋዊ መንገድ ወደ አውሮጳ መግባት አይችሉም። ስለዚህ በአደገኛ ጉዞ ወደ አውሮጳ ለመምጣት ወደ ወንጀለኛዎቹ ህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች ይሄዳሉ።  ከዚህ ሌላ የስደት ምንጭ በሆኑት ሀገራት ልማትን ማስፋፋት ሌላው መፍትሄ ነው። ምዕራብ አፍሪቃን ከመሳሰሉ ሀገራት የሚሰደዱት በቂ መረጃ ሳይዙ ነው። ሊቢያ ሲደርሱ ነው ከእውነታው ጋር የሚጋፈጡት። እናም ይህን ለማስቀረት መረጃ የማዳረስ ዘመቻ እናካሂዳለን። የስደት ምንጭ እና የስደተኞች መዳረሻ የሆኑ ሀገራትም ችግሩን ማስወገድ የሚያስችል የረዥም ጊዜ ፖሊሲዎችን መንደፍ ይኖርባቸዋል።»
እንደ አይኦም እነዚህ በቅርብ ጊዜ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ መፍትሄዎች አይደሉም። ችግሩም በሶስት ወይም  በስድስት ወራት ውስጥ ሊወገድ አይችልም። ሆኖም ካለፉት ዓመታት ልምድ በመውሰድ ቢያንስ በሜዴትራንያን ባህር የስደተኞችን ሞት ለማስቀረት ተጨማሪ የህይወት አድን መርከቦችን ማሰማራት እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።  

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች