በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ያገረሸው ግጭት | አፍሪቃ | DW | 03.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ያገረሸው ግጭት

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ባለፈው ሳምንት በታየው ግጭት  85 ሰዎች ተገድለዋል። ከመዲናይቱ ባንጊ በስተሰሜን ምሥራቅ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የኦት ኮቶ ግዛት ዋና ከተማ፣ ብሪያ በታጣቂዎቹ ቡድኖች መካከል በተካሄደው ግጭት 11,000 ተፈናቅለዋል። የተመድ ዋና ጸሀፊ ፓን ኪ ሙን ግጭቱን በማውገዝ ባፋጣኝ እንያበቃ አሳስበዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:18
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:18 ደቂቃ

ግጭት በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ

በሰሞኑ የብሪያ ግጭት የሞቱት እና የተፈናቀሉት ውሁዳኑን የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ሙስሊም ማህበረሰብ እንወክላለን በሚሉት ለሁለት በተከፋፈሉ የቀድሞ የሴሌካ ቡድኖች ፣ ማለትም፣ የማአሬ ተሀድሶ ሕዝባዊ ግንባር እና ህብረት ለማአሬ ሰላም በተባሉት የሚሊሺያ ቡድኖች  መካከል የተፈጠረው ግጭት ሰለባዎች ናቸው። የማአሬ ተሀድሶ ሕዝባዊ ግንባር ካለፉት ጊዚያት ወዲህ በሀገሪቱ የፉላኒ ጎሳ አንፃር ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሎዋል፣ ምክንያቱም  የተቀናቃኙ ህብረት ለማአሬ ሰላም የተባለው ቡድን ብዙ አባላት የዚሁ የፉላኒ ጎሳ  ናቸው።  «ካዴይ ቮክስ» የተሰኘው በኢንተርኔት የሚነበበው የማአሬ እትም ዋና ስራ አስኪያጅ ሮካ ሮሊን ላንዱንግ በሀገሪቱ እጎአ ከ2013 ዓም ወዲህ የሚታየው ውዝግብ በዚህ አዲስ ጥቃት ወደ አሳሳቢ ደረጃ የተሸጋገረ አድርገው ተመልክተውታል። በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ባለፈው ሳምንት በታየው ግጭት  85 ሰዎች ተገድለዋል። ከመዲናይቱ ባንጊ በስተሰሜን ምሥራቅ 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የኦት ኮቶ ግዛት ዋና ከተማ ፣ብሪያ በታጣቂዎቹ ቡድኖች መካከል በተካሄደው ግጭት 11,000 ተፈናቅለዋል።
«ወደ ጎሳ ግጭት በማምራት ላይ ነን።  ሀይማኖታዊው ግጭት ወደ ጎሳ ውዝግብ ካመራን በሀገሪቱ አንድነት እና በማህበራዊው አብሮ የመኖር ሁኔታ ላይ  አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ያስከትላል። »


ይሁን እንጂ፣ አሁን እንደሚታየው በሀገሪቱ ማህበረሰብ ውስጥ የአብሮነት መንፈስ አለ ሊባል አይችልም። በማአሬ እጎአ ከ2013 ዓም ወዲህ በቀድሞ የሴሌካ ዓማፅያን እና በፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች በቀጠለው የኃይል ርምጃ  ቀውስ ውስጥ ነው የምትገኘው። የማአሬን ፀጥታ ሁኔታ ችላ ከተባለ እና ሁኔታውን ደህና ነው ብሎ ለማለፍ የሚሞከርበት ድርጊት ሀገሪቱ የምትገንበትን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ እንደማይቻል ለውሁዳን ብሔር/ብሔረሰቦች የሚሟገተው «ገዜልሻፍት ፊውር በድሮተ ፈልከር» የተባለው የጀርመናውያኑ ድርጅት ኃላፊ ኡልሪኽ ዴልዩስ በማመልከት የተለያዩት ሚሊሺያ ቡድኖች የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ቢደረግ እንደሚሻል አሳስበዋል።  በሀምበርግ ከተማ የሚገኘው የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት  ተቋም፣ በምሕፃሩ «ጊጋ» የተባለው ባልደረባ ቲም ግላቭየን ይህ ቀላል እንዳልሆነ ነው የገለጹት።
« የጦር መሳሪያ ትጥቅ ማስፈታቱ በጣም አዳጋች ነው። ምክንያቱም ሁሉም ቡድኖች አንዱን የህብረተሰቡን ክፍል ስለሚወክሉ ደህንነቱን ሊያረጋግጡ ይገባል በሚል ትጥቃቸውን መፍታት አይፈልጉም። አንዱን ቡድን የጦር መሳሪያ ትጥቅ ማስፈታት ማለት እንግዲህ ይህንኑ ቡድን  ብቻ ሳይሆን፣ የሚወክለውን ጎሳም ጭምር ትጥቅ ላልፈታው ሌላው ቡድን ጥቃት አጋልጦ መስጠት ሊሆን ይችላል ማለት ነው። »   
ታጣቂዎቹን ቡድኖች ትጥቅ ማስፈታቱ ቀላል እንደማይሆን የሚሟገተው «ገዜልሻፍት ፊውር በድሮተ ፈልከር» የተባለው የጀርመናውያኑ ድርጅት ኃላፊ ኡልሪኽ ዴልዩስ ተናግረዋል። 
« ይህን በሚገባ እናውቃለን። እኛ ለችግሩ መፍትሔ ለማስገኘት በጣም ወሳኝ ነው ብለን የምናስበው ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ብቻ ነው የምንፈልገው። »

Zentralafrikanische Republik Präsident Touadera (picture-alliance/dpa/L. Koula)

ፕሬዚደንት ቱዋዴራ

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ፎስተ አርሾንዥ ቱዋዴራም ቢሆኑ የተለያዩት የሚሊሺያ ቡድኖች የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን ለማስፈታት ፍላጎት አላቸው። ይሁን እንጂ፣ ፕሬዚደንቱ ሚሊሺያዎቹን ትጥቅ የማስፈታቱ ተግባር በግዳጅ ሳይሆን ግንዘብ በመስጠት ለማከናወን  እቅድ ይዘዋል። ቱዋዴራ ባለፉት ሶስት ዓመታት ቀውስ ለተዳቀቀችው ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መልሶ ግንባታ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሶስት ቢልዮን ዩሮ  ርዳታ ሲጠይቁ፣ ከዚሁ መካከል ዓለም አቀፉ ማህበረ ሰብ ሁለት ቢልዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብቶላቸዋል።
የጀርመናውያኑ የሚሟገተው «ገዜልሻፍት ፊውር በድሮተ ፈልከር» ድርጅት ኃላፊ ኡልሪኽ ዴልዩስ በገንዘብ ትጥቅ ማስፈታት የሚለውን የፕሬዚደንት ቱዋዴራ እቅድ መሳካትን በጥርጣሬ ነው የተመለከቱት።
«  ጦርነት ላዳቀቃቸው ሀገራት የሚሰጥ የገንዘብ ርዳታ የሀገራቱን ፀጥታ ከማረጋጋት ይልቅ፣ ሙስና እንዲስፋፋ ብቻ ማድረጉን ነው ከሌሎች የርስበርስ ጦርነት ያገኘነው ተሞክሮ ያስተማረን። »
የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ፕሬዚደንት ቱዋዴራ ባለፈው የካቲት ወር ለዚሁ ስልጣን በተመረጡበት ጊዜ ሀገሪቱን እንደሚያረጋጉ ቃል ገብተው ነበር። 
 ይሁን እንጂ፣ ይህንኑ የገቡትን ቃል በተግባር የመተርጎሙ ጉዳይ በርሳቸው እጅ ውስጥ እንዳልሆነ ቲም ግላቭየን ይናገራሉ። 
«  በቆዳ ስፋቷ ፈረንሳይን በምታህለው በዚችው ሀገር ውስጥ በግምት ወደ 2,000 የሚጠጉ የፀጥታ ጥበቃ ኃይላት ብቻ አሉ። እና መንግሥት የፈለገውን ነገር ለማድረግ ቢፈልግም ፣ በሀገሪቱ ወቅታዊ የፀጥታ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ ለማሳረፍ  የሚያስችለው አቅም የለውም። »


በማ አ ሬ የተሰማራው«ሚኑስካ» የተባለው  የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ 12,000 ወታደሮች ብቻ ነው ያሰለፈው።  ፈረንሳይም በዚችው ሀገር ጀምራው የነበረውን ተልዕኮ ከአንድ ወር በፊት ባለፈው ጥቅምት ወር ያበቃችበትም ድርጊት  የፀጥታውን ሁኔታ አሳሳቢ እንደሚያደርገው ዴልዩስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
« የፈረንሳይ ወታደሮች ከማአሬ መውጣት ጥሩ እንዳልሆነ ስናስጠነቅቅ ነበር።  ፈረንሳውያኑ ወታደሮች በፀጥታ ጥበቃው ረገድ ሲያከናውኑት የነበረውን ስራ  «ሚኑስካ» በሁነኛ ዘዴ ሊሸፍነው አይችልም። » 
እንደ ቲም ግላቪየን ትዝብት፣  በቂ አቅም ይጎድላቸዋል የሚሉዋቸው የሚኑስካ» ወታደሮች ሲቭሉን ሕዝብ ፈጥነው ያልተከላከሉበት ድርጊት ወደፊትም ለታጣቂ ቡድኖች መጠናከር ምክንያት ሆኖዋል።
« ሕዝቡ ለታጣቂ ቡድኖች የኃይል ርምጃ የተጋለጠ ያህል ተሰምቶታል። በዚህም የተነሳ   ሰዎች ይከላከሉናል ብለው የሚገምቱዋቸውን ታጣቂ ቡድኖች ይቀላቀላሉ። » 

ክሪስቲነ ሀሪየስ/አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች