በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ያገረሸው ውጊያ | አፍሪቃ | DW | 28.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ያገረሸው ውጊያ

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የርስበርሱ ጦርነት ካበቃ ሁለት ዓመት ሆነው። ይሁንና፣ አሁን ውጊያው እንዳዲስ አገርሽቷል። ይህን አሳሳቢ ሁኔታ ለማብቃትም የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ   ፕሬዚደንት  ፎስታ አርሾንዥ ቱዋዴራ እርቀ ሰላማ ለማውረድ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:27

ውጊያ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ

በዚሁ መሰረትም፣ ፕሬዚደንት ቱዋዴራ ከፖለቲካ ቡድኖች እና ከዓማፅያኑ ንቅናቄዎች ተወካዮች ጋር ተወያይተዋል። በሲቭሉ መንግሥት ውስጥ ተወካዮች ላሏቸው የዓማፅያኑ ቡድን ተዋጊዎች የሰላም እጃቸውን ዘርግተዋል። ተዋጊዎቹን የጦር መሳሪያ ትጥቅ ባፋጣኝ ለማስፈታት እና ወደ መደበኛው ኑሮ ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ከአንድ ሳምንት በፊት አስታውቀዋል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች፣ በተለይ በመዲናይቱ ባንጊ ሙስሊሞች በብዛት በሚኖሩበት ፒኬ5 በተባለው ሰፈር ደም አፋሳሽ ውዝግቦች ተበራክተው ተካሂደዋል። የዓማፅያኑ  ቡድን መንግሥት ለሙስሊሙ ህብረተሰብ የሚገባውን ትኩረት አልሰጠም በማለት የጦር መሳሪያውን አንስቷል።  
በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ የተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ በምህፃሩ የሚኑስካ  አባላት በባንጊ የአንድ ወንጀለኛ ቡድን አባላትን ትጥቅ ለማስፈታት  እና በቁጥጥር ለማዋል በሞከሩበት ጊዜ አንድ ሰላም አስከባሪ ተገድሏል፣ ሌሎች ስምንት ደግሞ ቆስለዋል። በዚህ በተያዘው የሚያዝያ ወር መጀመሪያ ከሰላም አስከባሪው ጓድ ጋር በተካሄደ ውጊያም  ቢያንስ 21 ሰዎች መገደላቸውን ያካባቢ ምንጮች ገልጸዋል። የውጊያው ሰለባዎች ሲቭሎች ይሁኑ ወይም የታጣቂው ቡድን አባላት እስከዛሬ በግልጽ ሊታወቅ አለመቻሉን ምንጮች አመልክተዋል። በዚሁ ሰፈር ወንጀለኞች ስር መስደዳቸውን የሚኑስካ ኃላፊ ኦናንጋ አንያንጋ አስታውቀዋል።

«  በፒ ኬ 5 ሰፈር የኃይሉ ተግባር ከብዙ ጊዜ ወዲህ እንደቀጠለ ነው። ወንጀለኞች በዚሁ ሰፈር ስር የሰደዱ ሲሆን፣ ይህ ተግባራቸው በሀገሪቱ ሕዝብ ዘንድ በፍፁም ተቀባይነት አላገኘም። በጣም ብዙ የጦር መሳሪያም አላቸው። ሕዝቡ ይህን ሁኔታ በትዕግሥት ሊያልፈው አልቻለም። በመሆኑም፣ የሚኑስካን ርዳታ ጠይቋል። እናም ለርዳታው ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተናል። »
ይሁን እንጂ፣ ብዙዎቹ የሀገሪቱ ዜጎች ከሰላም አስከባሪው ጓድ ብዙ ነው የሚጠብቁት። የሚኑስካ አባላት በቀጥታ በዓማፅያኑ አንፃር ርምጃ እንዲወስዱ ይፈልጋሉ። ሚኑስካ ግን ይህን ማድረግ የሚያስችለው ጠንካራ ተልዕኮ አልተሰጠውም፣ ጥቃት ሊሰነዝር የሚችለው በቀጥታ ስጋት ከተደቀነበት ብቻ ነው። ሕዝቡ የሚፈልገውን ጥበቃ ማከናወን ያለበት የሀገሪቱ ጦር ኃይል በሚኑስካ አንፃር፣ በቂ በጀት የለውም፣ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ላይ በተጣለው ፣ የዓማፅያን ቡድኖች በማያከብሩት   ዓለም አቀፍ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የተነሳ ደግሞ ጦሩ በሚገባ የታጠቀ አይደለም። 

ፕሬዚደንት ቱዋዴራ ስልጣን ከያዙ፣ ውዝግቡም በይፋ ካበቃ እና የሽግግር መንግሥቱ በተመረጠ መንግሥት ከተተካ ሁለት ዓመት  ሆኖዋል። የግዛት እና የወረዳ አስተዳዳሪዎች ሁሉ ስራቸውን በማከናወን ላይ መሆናቸውን እና የመንግሥቱ ስልጣን በመላ ሀገሪቱ መረጋገጡን የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ጠቅላይ ሚንስትር ሳምፕሊስ ሳራንዢ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። ይሁንና፣ በሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚደንት ካትሪን ሳምባ ፓንዛ ዘመን የእርቀ ሰላማ አፈላላጊ ሚንትስትር  እና የፕሬዚደንትዋ አማካሪ የነበሩት አንቷኔት ሞንቴኝ  አሁንም በቀጠለው ቀውስ ሰበብ፣ በጠቅላይ ሚንስትሩ አባባል እንደማይስማሙ እና ቀውሱ አካባቢውም ላይ ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል አስታውቀዋል። 
« በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ በሀገር ውስጥ መፈናቀላቸው እና በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞችም ወደ ጎረቤት ሀገራት መሸሻቸው በአካባቢው ቀውስ እንዳያስከትል አስግቷል።  ይህን ቀውስ እንደ ቀላል ነገር ልንመለከተው አንችልም። ብሔራዊው ኤኮኖሚ ወድቋል። ይሁንና፣ ታጣቂ ቡድኖች ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ በመበራከታቸው ጎን፣ መንግሥት  እጅ መግባት ያለበትን ግብር በመሰብሰብ ላይ ናቸው። በአንፃራቸው፣ የሀገሪቱ መንግሥት ካዝናው ባዶ በመሆኑ  የሚጠበቅበትን ስራ ማከናወን አልቻለም።  
 »
በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ቀውሱ በሕዝቡ ዕለታዊ ኑሮም አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፉን ዤስቲዮን ዴ ኮንፍሊ ዓለም አቀፍ ተቋም የተሰኘ የውዝግቦች መፍትሔ አፈላላጊ መንግሥታዊ ድርጅት ኃላፊ የሆኑት የቶጎ ተወላጅ ካግ ሶንሱሲ አመልክተዋል።
«  ሰዎች፣ በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ እንደሚታየው፣ ለብዙ ጊዜ በጦርነት ውስጥ በሚኖሩበት ጊዜ፣ ያሳለፉት አሰቃቂ ገጠመኛቸው ከኅሊናቸው አይጠፋም። እንዲያውም አንዳንዶች ሰላምን የሚፈሩ ነው የሚመስለው። ሰዎችንም ወደ ጦርነት ለመገፋፋት ሲሞክሩ ይታያሉ። ነገር ግን ጦርነት ለዚች ሀገር ያስገኘው አንዳችም ነገር የለም።   »
አንዳንዶች የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክን ውዝግብ በማብቃቱ ረገድ ሚኑስካ ሊረዳ ይችል ይሆናል ይላሉ፣ ነገር ግን፣ ዓለም አቀፉ ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ አንዱ ወታደሩ ለዓማፅያን የጦር መሳሪያ እና ጥይት አቅርቧል በሚል ወቀሳ ከተሰነዘረበት ወዲህ ተዓማኒነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል። የጓዱ ወታደር የሰራው ስራ እጅግ እንዳሳዘናቸው የሚኑስካ ኃላፊ ኦናንጋ አንያንግ ቢናገሩም፣ የጓዱ ገፅታ ነቁጣ አርፎበታል።
« ይህ ከአንድ ወታደር የማይጠበቅ አሳፋሪ ድርጊት ነው። እንደተሰማው፣ ወታደሩ በዚሁ ሙያ ላይ 25 ዓመት አገልግሏል። ጠንካራ ቅጣት እንደሚሰጠው በፍፁም አልጠራጠርም። »  
ከዚህ በተጨማሪ ምንም እንኳን እስካሁን ከ12 የሚሊሺያ ቡድኖች 240 ተዋጊዎች በብሔራዊው ጦር ውስጥ ቢቀላቀሉም የዓማፅያን ቡድን ተዋጊዎችን ትጥቅ የማስፈታቱ ተግባር አዝጋሚ መሆኑ ሁኔታዎችን አወሳስቧል። አንዳንድ የሀገሪቱ ዜጎች በተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ስምምነት ሩስያውያን የጦር አሰልጣኞች ወደ ሀገሪቱ እንዲመሄዱ እና ለስልጠና የሚያስፈልገውን የጦር መሳሪያ እንዲያቀርቡ ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ፣ ይህ ዓይነቱ ርዳታ በቂ እንደማይሆን ነው የዤስቲዮን ዴ ኮንፍሊ ዓለም አቀፍ ተቋም ኃላፊ ሶንሱሲ የገለጹት። እንደ ሶንሱሲ አስተያየት፣

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ላይ የተጣለው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ፣ በተለይ፣ በዚሁ የአፍሪቃ አካባቢ የሚታየው የጦር መሳሪያ ዝውውር ሲታሰብ ከረጅም ጊዜ በፊት መነሳት ነበረበት።
«  አንድ መንግሥት፣ የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን ሳያቋርጡ በስውሩ ገበያ ከሚያገኙ ቡድኖች ጋር ሊፎካካር  አይችልም። ድርድሩ እንዲሳካ ከፈለገ መንግሥት ራሱ ጠንካራ ወታደራዊ አቋም ሊኖረው ይገባል። »
ዓማፅያኑ ግን የጦር መሳሪያ ትጥቃቸውን በርዳታ እንደሚያገኙ ቢያመለክቱም፣ እንደ ሶንሱሲ፣ ይህን በማስረጃ መደገፍ ይጠበቅባቸዋል።
« አንድ የዓማፅያን ቡድን የፈረንሳይ ድጋፍ እንዳለው ከተናገረ፣ ይህን አባባሉን የሚያረጋግጥለት ማስረጃ፣ ማለትም፣ ከፈረንሳይ አምባሳደር ወይም ከፊናንስ ሚንስትሩ ወይም ከፕሬዚደንቱ የደረሰው ጽሁፍ መኖሩን፣ የማንንስ ጥቅም ለማስጠበቅ ስትል እንደምትደግፋቸው የሚሉትን  ጥያቄዎች የሚመልስ ማስረጃ ቅረብ ይኖርበታል። »
የሀገሪቱ መንግሥት ፀጥታን የማስጠበቁን ኃላፊነት እንዲወጣ ከተፈለገ አቅሙ ሊጠናከር ይገባል። አሁን በመዲናይቱ ባንጊ የተጀመረው ውጊያ ውዝግቡን ወደ ሀይማኖታዊ ግጭት እንዳይቀይረው አስግቷል። ሙስሊም የሚሊሺያ ቡድኖች ወደመዲናይቱ ለመገስገስ ካለፈው ሳምንት ወዲህ ያሰሙትን ዛቻ ክርስትያኖቹ ታጣቂ ቡድኖችም እንደሚከተሉ አስታውቀዋል። ይህ በሕዝቡ ዘንድ ስጋት በመፍጠሩ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሳምፕሊስ ሳራንዢ ሕዝቡ እንዲረጋጋ ተማፅነዋል።
« እኔም ፣ ልክ እንደ ፕሬዚደንቱ፣ ሕዝቡ እንዳይደናገጥ ጥሪ አስተላልፌአለሁ። መንግሥት ጦርነት እንዲጀመር የሚደረገውን ጥረት ማብቃት የሚያስችሉ ርምጃዎችን አነቃቅቷል። እርግጥ፣ ሰዎች በሀገሪቱ አለመረጋጋት እንደተስፋፋ ይናገራሉ። ግን፣ ይህ እውነት አይደለም፣ የሀገሪቱን መረጋጋት ለማረጋገጥ የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ዜጎች ነቅተው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። »
ለውዝግቡ በፖለቲካው መድረክ መፍትሔ ለማስገነት የሚደረገው ጥረት በቀጣዮቹ ጊዜ በሚታየው ሂደት ላይ ጥገኛ ይሆናል ተብሏል።


አርያም ተክሌ/ፊሊፕ ዛንድነር
እሸቴ በቀለ
 

Audios and videos on the topic