በማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ግጭት የመንግሥት ተቋማት ተዘግተዋል | ኢትዮጵያ | DW | 14.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በማዕከላዊ እና ምዕራብ ጎንደር ግጭት የመንግሥት ተቋማት ተዘግተዋል

በማዕከላዊ ጎንደር ጭልጋና አካባቢው በየወቅቱ በሚነሳው ግጭት ምክንያት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። ነዋሪዎች እንደሚሉት በምዕራባዊ ጎንደር ዞን መንገዶች ዝግ በመሆናቸው ወደ ጎንደርና ባሕር ዳር ከተሞች ለመንቀሳቀስ ተቸግረዋል፡የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተፈናቃዮች ቁጥር 80 ሺሕ ደርሷል ብሏል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:02

የክልሉ መንግሥት የተፈናቃዮች ቁጥር 80 ሺሕ መድረሱን አስታውቋል

ምዕራባዊና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች ከዓመቱ መጀመሪያ ጀምሮ  በአካባቢው ህዝቦች መካከል በተፈጠረው ግጭት ሰዎች ተገድለዋል፣ ንብረት ወድሟል በርካቶችም ቤት ንብረታቸውን ተተው ተፈናቅለዋል፡፡ በተለይ ካለፈው ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋና አካባቢው እንደገና ባገረሸው ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል ንብረትም ወድሟል፡፡አካባቢዉ እስካሁንም አለመረጋጋቱን ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ በአካባቢው ትምህርት ቤቶችንና የፍትህ ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶች መዘጋታቸውን ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት፡፡ እንደዚሁም በምዕራባዊ ጎንደር ዞኖች የሚኖሩ ነዋሪዎች ጭልጋና አካባቢው በተፈጠረው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት ወደ ጎንደርና ባሕር ዳር ከተሞች መንቀሳቀስ አልቻሉም፡፡

አንድ የገንዳ ውሀ ከተማ ነዋሪ ወደ ጎንደርና ባሕር ዳር  ከተሞች ለመጓዝ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው አልፎ አልፎ እንኳ በአጀብ መሄድ ቢቻልም የ65 ብር ታሪፍ መንገድን እስከ 300 ብር ከፍለው ለመጓዝ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ ሽንፋ ከተማ ከገንዳ ውሐ ከተማ 54 ኪሎሜትር ላይ ትገኛለች፡፡ የዚች ከተማ ነዋሪዎችም ቢሆን ጎንደር ከተማ ለመድረስ ከፍተኛ ወጪ ከማውጣታቸውም በላይ ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡ ጎንደር ከተማ ለመድረስ 7 ሰዓት ብቻ ይወስድባቸው እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ግን በጭልጋ ከተማና በአካበቢው በተፈጠረው ችግር  ምክንያት በባህር ዳር ዞረው ስለሚሄዱ አንድ ቀን ተኩል ወስዶባቸዋል፡፡ 

የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ በክልሉ ወቀታዊ ጉዳይ ዙሪያ ትናንት በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት በምዕራባዊና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች በተፈጠረው ግጭት ትምህርት ቤቶች የዕለት ተለት የመማር ማስተማር ሥራቸውን አቁመዋል፣ ጤና ተቋማትም በተሟላ መንገድ ሥራቸውን ባግባቡ እየተወጡ አይደልም፡፡ የመንግስት ሰራተኞችም መስራት የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ ስራ ማቆማቸውን አመልክተዋል። ወንድም እህት የሞቱባቸው ወገኖች ለስነ ልቦና ቀውስ መጋለጣቸውን የተናገሩት አቶ አሰማኸኝ ችግሮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ የክልሉ መንግስት እየሰራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ ባለፈው ህዳር በክልሉ የተፈናቃዮች ቁጥር ከ20 ሺህ እንደማይበልጥ ጠቁመው ዛሬ ላይ ግን ይህ ቁጥር በብዙ እጥፍ ጨምሯል ነው ያሉት፡፡የተፈጠረውን ቀውስ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመቀየርና ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ወደ 600 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው የህብረተሰቡ  ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንና ይህን የሚያስተባብር ግበረሀይል መቋቋሙንም ተናግረዋል፡፡በአካባቢው ያለው ውጥረት መሻሻል ቢታይበትም አሁንም ግን አካባቢው የስጋት ቀጠና መሆኑን አልሸሸጉም፡፡

ዐለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic