በማሊ የአማጽያኑ ግስጋሴ ተገታ | አፍሪቃ | DW | 12.01.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

በማሊ የአማጽያኑ ግስጋሴ ተገታ

የማሊ ጦር በፈረንሣይ አየር ሃይል በመረዳት ኮና የተሰኘችውን ሰሜናዊት ከተማ የአል-ቃኢዳ አበር ከሆነው እስላሚስት ቡድን ማስለቀቁን አስታወቀ። በዘመቻው አንድ የፈረንሣይ ጦር ሄሊኮፕተር አብራሪ ሞትዋል።

የማሊ መንግሥት ወታደሮች በፈረንሣይና በርከት ባሉ የአፍሪቃ ሃገራት በመታገዝ የአገሪቱን እስላሚስት ተዋጊዎች ዕርምጃ መግታታቸው ተነገረ። የማሊ ጦር በፈረንሣይ አየር ሃይል በመረዳት ኮና የተሰኘችውን ሰሜናዊት ከተማ የአል-ቃኢዳ አበር ከሆነው እስላሚስት ቡድን ማስለቀቁን አስታውቋል። በዘመቻው አንድ የፈረንሣይ ጦር ሄሊኮፕተር አብራሪ ሕይወቱን ማጣቱም እየተነገረ ነው። የማሊ ጊዜያዊ ፕሬዚደንት ዲዮንኩንዳ ትራኦሬ የሁኔታውን መካረር ምክንያት በማድረግ ለጊዜው ለአሥር ቀናት የሚጸና አገር-አቀር የአስቸኳይ ጊዜ ደምብ አውጀዋል። በሌላ በኩል ዩ ኤስ አሜሪካም ኒውዮርክ-ታይምስ ጋዜጣ እንደዘገበው የፈረንሣይን ጦር በትጥቅና በመረጃ አቅርቦት ለማገዝ ታስባለች። ሆኖም ተያይዞ እንደተጠቀሰው ዋሺንግተን ወደ አካባቢው ወታደሮች የመላክ ውጥን የላትም። ፈረንሣይ ትናንት ወታደራዊ ጣልቃ-ገብ ዕርምጃ የወሰደችው የማሊ መንግሥት ዕርዳታዋን ከጠየቀ በኋላ ነበር።

በሰሜናዊው ማሊ እስላማውያን አማጺ ኃይላት፤ የመንግሥትን ጦር ኃይል ገጥመው ብርቱ ውጊያ ካካሄዱ በኋላ ስልታዊ አቀመማጥ እንዳላት የተነገረላትን ኮና የተባለችውን ከተማ በቁጥጥራቸው ሥር ማዋላቸው ትናንት አርብ ተገልጾ ነበር። ዲፕሎማቶች ፤ አማጽያኑ ወደፊት መግፋታቸዉን አስታዉቀዉ ነበር። የጀርመን ዜና አገልግሎት ድርጅት DPA እንዳስታወቀው፤ 1,200 ታጣቂዎች፤ ወደ መዲናይቱ ፤ ባማኮ አቅጣጫ በመገሥገስ ላይ ነበሩ። አማጽያኑ ወደ ባማኮ ማምራታቸውን ከቀጠሉ፣ አገራቸው ጣልቃ በመግባት አማጽያኑን እንደምትወጋ፤ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ዖላንድ አስገንዝበዉ ነበር። አያይዘውም ዖላንድ፤ የማሊ ባለሥልጣናት ላቀረቡት የድረሱልን ጥሪ ፈረንሳይ ከተጓዳኞቿ ጋር ሆና ምላሽ ለመስጠት ተዘጋጅታለች ማለታቸዉ ይታወሳል። ፈረንሳዊው የማሊ ጉዳይ ልዑክ Jean Felix Oaganon ናይጀሪያን ከጎበኙ በኋላ እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጥተው ነበር። «የውሳኔ አንቀጽ 2085 ን ተግባራዊ ለማድረግ በመሥራት ላይ እንገኛለን። በመጀመሪያ ደረጃ፤ የውሳኔው ዋና ዓላማ፣ ሰፊ ጥረት በማድረግ፤ ከባማኮ ለሰሜኑና ደቡቡ የአገሪቱ ከፊል የሚበጅ የፖለቲካ መፍትኄ ማስገኘት ነው። እንዲሁም የማሊን ጦር ሠራዊት የሚያግዘው፣ የአፍሪቃ ሰላም አስከባሪ ኃይል በጊዜ የሚሠማራ መሆኑን ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል» ማሊን በተመለከተ፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ጥበቃው ም/ቤትም ኒው ዮርክ ውስጥ ባስቸኳይ በመሰብሰብ የማሊ ወቅታዊ ይዞታ እንዳሳሰበውና ባስቸኳይ ዓለም አቀፍ ጦር ኃይል እንዲዘምት መጠየቁ ይታወቃል። ባለፈው ዓመት በመጋቢት ወር፤ በማሊ የተካሄደው ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግሥት፤ የሥልጣን ክፈተት ባስከተለበት ወቅት፤ እስላማዊ አክራሪ ኃይሎችና የቱዓሬግ ብሔረሰብ ተዋጊዎች፤ ሰፊውን የማሊን ሰሜናዊ ግዛት በቁጥጥር ሥር ማዋላቸው የሚታወስ ነው።

አዜብ ታደሰ

መስፍን መኮንን

 • ቀን 12.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17Izr
 • ቀን 12.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17Izr