በመንግሥት እና በግል ት/ቤቶች የተማሩ ወጣቶች ተሞክሮ | ወጣቶች | DW | 08.12.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ወጣቶች

በመንግሥት እና በግል ት/ቤቶች የተማሩ ወጣቶች ተሞክሮ

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት ትምህርታቸውን በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤት የተከታተሉ ኢትዮጵያውያንን ተሞክሮ ያስቃኘናል። ነፃ እና የሚከፈልበት ትምህርት ምን ዓይነት ሚና አለው?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:03

ነፃ ወይስ የሚከፈልበት ትምህርት?

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ 67, 000 በላይ የመንግሥትና የግል ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ። ትምህርት ሚኒስቴር በኅዳር ወር 2010 ዓም ይፋ እንዳደረገውም እነዚህ ትምህርት ቤቶች ባለ 11 አሀዝ ( ዲጂት) የመለያ ኮድ አግኝተዋል። በገጠራማ አካባቢ አሁንም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ያመዝናሉ። ወደ ከተማው ቀረብ እያለ ሲመጣ ደግሞ የግል ትምህርት ቤቶች ከመንግሥት ትምህርት ቤቶች ጎን ለጎን በመማር ማስተማር ሂደቱ ተሳትፈው ይሰራሉ። አዳፍር 27 ዓመቱ ነው። እስከ ከፍተኛ ተቋም ድረስ የተማረዉ በመንግሥት ትምህርት ቤት ነው። « በመግሥት ትምህርት ቤት በመማሬ የጎደለብኝ ነገር የለም። ከግል ትምህርት ቤት ጋር ሲወዳደር ግን ትምህርት ቤቶቹ ከወላጅ ጋር ተጣምረው አይሰሩም»

ሰሜን ሸዋ ውስጥ ትምህርቱን እንደተከታተለ የሚናገረው አዳፍር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች በቂ የቤተ ሙከራ መገልገያዎች፣ የቤተ መጽሐፍት እና የሌሎች መገልገያዎች እጥረት ማስተዋሉን ይናገራል። በዚህ ረገድ የግል ትምህርት ቤቶች የተሻሉ ናቸው ብሎ ወጣቱ ቢያምንም የሚጠይቁት ክፍያ አያስደስተዉም። ምክንያቱም ምንም እንኳን በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ትምህርት በነፃ ቢሆንም በርካታ ትምህርታቸውን መከታተል የማይችሉ ኢትዮጵያውያን አሁንም ስላሉ ነው።  « በነፃ መማር ቢባልም፣ ልብስ እና የትምህርት መገልገያዎችን ማሟላት ያስፈልጋል። ይህንን መክፈል ሳይችሉ ከትምህርት የሚፈናቀሉ ብዙዎች አሉ» ይላል።

ሌላው ሀሳቡን ያካፈለን ወጣት ሀቢብ መሐመድ ነው። በሁለቱም ትምህርት ቤቶች የመማር ዕድል ነበረው። እስከ 6ኛ ክፍል ወለጋ ውስጥ በአንድ የመንግሥት ትምህርት ቤት ከተማረ በኋላ ከ 7ኛ - 10ኛ ክፍል ያለውን ደግም አዲስ አበባ ውስጥ በግል ትምህርት ቤት ተምሯል። ትምህርት ቤቶቹ በጣም ልዩነት አላቸው ይላል። እንደ ወጣቱ ከሆነ« ቤተሰብ ገንዘብ ከፍሎ በሚያስተምርበት ጊዜ ነው ቁጥጥሩ የሚጠነክረው።»

የ 30 ዓመቱ መብራቱ በፈለገው የሙያ ዘርፍ ባይሆንም ሁለት ጊዜ ከዮኒቨርሲቲ ተመርቋል። ጠቅላላ ትምህርቱን የተከታተለው በመንግሥት ትምህርት ቤት ነው። ቢሆንም ከመንግሥት ትምህርት ቤት ይልቅ የግል ትምህርት ቤቶችን ይመርጣል። ትምህርት በክፍያ ቢሆንም ብዙም አያስጨንቀውም።« እንደዛ ከሆነ ተማሪዎች በፈለጉበት የሙያ ዘርፍ መርጠው መማር ይችላሉ። ወደ ትምህርትም የሚገቡት በፍላጎት ነው» ደቡብ ወሎ በሚገኝ በአንደኛ እና መለስተኛ የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ መምህር የሆኑት ሰይድም ቢሆኑ ትምህርት በክፍያ ቢሆን ይመርጣሉ። ምክንያታቸውም « ተማሪዎች ሁልጊዜ ይቀራሉ። ለምነን ማለት ይቻላል የምናስተምረው። በክፍያ ቢሆን ወላጆች ገንዘባቸው ስለሚቆጫቸው ልጆቻቸውን ተቆጣጥረው ለትምህርት ትኩረት ይሰጣሉ።»

Bildgalerie Ursachen von Armut: Mangelnde Bildungsmöglichkeiten

መምህር ሰይድም ይሁኑ ወጣት መብራቱ እንደሚሉት በርግጥ ክፍያ መክፈል ተማሪውን ያበረታታ ይሆን? ትምህርቱን በሙሉ በመንግስት ትምህርት ቤት የጨረሰው መብራቱ ከፍሎ ተምሮ ቢሆን ኑሮ በርግጥ ሁለት ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ መመረቅ ይችል ነበር? « በርግጥ ይህንን እድል አላገኘውም ነበር። ከፍሎ መማሩን የመረጥኩበት ምክንያት ልማር የፈለኳቸው ምርጫዎቼ ስላልተከበሩልኝ ነው።» ይላል መብራቱ።

በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው ጃፈር በመንግሥትም በግልም ትምህርት ቤት ተምሯል። እሱም 9ኛ ክፍል ደርሶ ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ሲገባ ክፍሉ በተማሪ ከመጨናነቅ ባሻገር ከፍተኛ ለውጥ እንዳየ ይናገራል። አብዛኛውን ጊዜ በግል ትምህርት ቤት የተማሩ ልጆች የቋንቋ እና የእጅ ጽሑፍ ችሎታቸው ጥሩ እንደሆነም ይነገራል። ይህም እውነት ነው ይላል ጃፈር። « የግል ትምህርት ቤቶች የእንግሊዘኛ ቋንቋ ላይ በጣም ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ» እሱም  የግል ትምህርት ቤቶችን ከመንግሥት ጋር ሲያነፃፅር የግል ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በተሻለ መልኩ ለቁም ነገር እያበቁ ነውም ይላል። ለሱ ግን ወሳኙ ነገር የትኛው ትምህርት ቤት የሚለው ሳይሆን ጠቅላላ የትምህርት አሰጣጡ እና ትውልዱ ነፃ የትምህርት ዕድል ማግኘት መቻሉ ነው።

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች