1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመቐለ የአየር ድብደባ መፈጸሙን የግብረ-ሰናይ ሰራተኞች እና ዲፕሎማቶች ተናገሩ

ሰኞ፣ ጥቅምት 8 2014

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ዛሬ ሰኞ የአየር ድብደባ መፈጸሙን የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ሰራተኞች እና ዲፕሎማቶች ተናገሩ። የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ለገሰ ቱሉ "መንግሥት ለምን የራሱን ከተማ ያጠቃል? መቐለ የኢትዮጵያ ከተማ ነች" ሲሉ ለሬውተርስ የተባለውን ድብደባ አስተባብለዋል።

https://p.dw.com/p/41oYM
Äthiopien Tigray | Hauptstadt Mekele
ምስል MICHAEL TEWELDE/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ ዛሬ ሰኞ የአየር ድብደባ መፈጸሙን የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ሰራተኞች እና ዲፕሎማቶች ተናገሩ።  የትግራይ ቴሌቭዥን ጣቢያ በፌስቡክ ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ በአየር ድብደባው ሶስት ሰዎች መገደላቸውን እና በ10 የሚቆጠሩ መቁሰላቸውን ገልጿል።የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ተፈጸመ የተባለውን የአየር ድብደባ አስተባብሏል።

በከተማው የሚገኙ ሁለት የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች ሰራተኞች የአየር ድብደባው መፈጸሙን በአጭር የጽሁፍ መልዕት ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ገልጸዋል።ሌሎች ሁለት ዲፕሎማቶችም ጥቃቱ መፈጸሙን እንደተናገሩ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

በዘገባዉ መሠረት የመጀመሪያው ድብደባ ዛሬ ሰኞ ጠዋት በመቐለ ዳርቻ ስሚንቶ ፋብሪካ ከሚገኝበት አካባቢ ተፈጽሟል።

ሁለተኛዉ ድብደባ ዛሬ ዕኩለ-ቀን በመቐለ ማዕከላዊ ክፍል ባለሥልጣናት የሚያዘወትሩት ፕላኔት ሆቴል አካባቢ እንደተፈጸመ የዜና ወኪሉ ዘግቧል። የህወሓት ቃል-አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በተረጋገጠ የትዊተር ገጻቸው የአየር ድብደባው መፈጸሙን አረጋግጠው "ሰኞ በመቐለ የገበያ ቀን ነው። [የጥቃቱ] ዓላማ ግልጽ ነው" ብለዋል። 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን በጉዳዩ ላይ የሰጡት መግለጫ የለም። በጥቃቱ የደረሰው ጉዳትን በተመለከተ በመቐለ ከሚገኙ የሕክምና ተቋማት ማረጋገጫ አልተገኘም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ተፈጸመ የተባለውን የአየር ድብደባ አስተባብሏል። የመንግሥት ኮምዩንኬሽን አገልግሎት ኃላፊ ለገሰ ቱሉ "መንግሥት ለምን የራሱን ከተማ ያጠቃል? መቐለ የኢትዮጵያ ከተማ ነች" ሲሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል።