በሐማሬሳ ግጭት 4 ሰዎች ሞተው 11 ቆሰሉ | ኢትዮጵያ | DW | 12.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

በሐማሬሳ ግጭት 4 ሰዎች ሞተው 11 ቆሰሉ

በሐማሬሳ የተፈናቃዮች መጠለያ ስፍራ ትላንት በተቀሰቀሰ ግጭት ሰዎች መሞታቸው እና መቁሰላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡ በመጠለያ ጣቢያው ዛሬም ተቃውሞ ቀጥሎ እንደነበር እና በአቅራቢያው በሚገኘው የሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ለተቃውሞ የወጡ ተማሪዎች በጸጥታ ኃይሎች እንዲበተኑ ተደርጓልም ተብሏል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:01

በሐማሬሳ መጠለያ ዛሬም ተቃውሞ ነበር

በሐማሬሳ የተፈናቃዮች መጠለያ ትላንት በተቀሰቀሰው ግጭት አራት ሰዎች ሞተው 11 ሰዎች መቁሰላቸውን የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አህመዴ ለዶይቼ ቬለ ገለጹ፡፡ ወደ 3‚500 ገደማ የሚሆኑ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች በተጠለሉበት በዚሁ ጣቢያ ዛሬም ተቃውሞ የነበረ ቢሆንም ጉዳት አለመድረሱንም ተናግረዋል፡፡ 

የትናንትናው ግጭት የተነሳው እህል ጭነው እየተጓዙ የነበሩ መኪኖች “በማይታወቁ ሰዎች ተይዘው ወደ ተፈናቃዮች መጠለያ እንዲገቡ በመደረጋቸው” እና የጸጥታ ኃይሎች እነርሱን ለማስለቀቅ ባደረጉት ሙከራ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የተፈጠረውን ደግሞ እንዲህ አስረድተዋል፡፡  

“የፌደራል የጸጥታ አካላት እና የክልል ጸጥታ አካላት (የሐረሪ እና የምስራቅ ሐረርጌ ዞን) አሉ፡፡ መጨረሻ ላይ እዚያ መከላከያ ገብቶ ነበር፡፡ እንግዲህ በዚህ መካከል በተፈጠረ ችግር ነው የሰው ህይወት ሊጠፋ የቻለው፡፡ ያንን መኪና ለማስለቀቅ በሚመጡ እና እዚያ መሃል ባለው ያው የሰው ህይወት ሊጠፋ ችሏል፡፡ አራት [ሰዎች]  ህይወታቸው ሲያልፍ ወደ 11 የሚሆኑ የቆሰሉት ናቸው” ብለዋል፡፡  

ከሟቾቹ ውስጥ አንድ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባል እና አንዲት ሴት እንደሚገኙበት አቶ ጀማል አስረድተዋል፡፡ በትናትናው ግጭት የቆሰሉት በሐረር ፋና ሆስፒታል ሕክምናቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ጀማል ቁስለኞቹ በደህና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ የሐረሪ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዛሬ በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ በሐማሬሳው ሁከት ሰባት እህል ጭነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከባድ መኪኖች እና ማሽኖች መቃጠላቸውን አስታውቋል፡፡ ድርጊቱ የፈጸሙት “የተደራጁ የፀረ ሰላም ኃይሎች” ነው ሲል ከስሷል።   

በሐማሬሳ መጠለያ ጣቢያ ዛሬም ተቃውሞ እንደነበር ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ በጣቢያው ተቃውሞ እንደነበር ያረጋገጡት አቶ ጀማል በግቢው ያሉ የመከላከያ ኃይሎች እንዲወጡ በመጠየቅ የተደረገ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ የዛሬውን ውሎ አስመልክቶም “ያለው ሁኔታ ጠዋት በግቢው የተወሰነ ግርግር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ገብተው ግቢውን እየጠበቁ ናቸው ያሉት፡፡ አሁን ከሀዘን ውጭ የተረጋጋ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው ማለት ይቻላል” ብለዋል፡፡

ከሐረር ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ የሚገኘው የሐማሬሳ መጠለያ ጣቢያ በሐረሪ ክልል ስር የሚገኝ ቢሆንም የጣቢያውን ጸጥታ ይቆጣጠር የነበረው እና ለተፈናቃዮች እርዳታ የሚያቀርበው የኦሮሚያ ክልል ነበር፡፡ የትላንትናውን ግጭት ተከትሎ በስፍራው ላይ የተገኙት የመከላከያ ሠራዊት አባላት «እንዴት ወደ ቦታው እንደመጡ መረጃው የለኝም» ሲሉ የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት አባላቱ «ግጭቱን በሌላ መልኩ ከመቆጣጠር ይልቅ የኃይል እርምጃ ወስደዋል» ስለመባሉ ጠይቀናቸው ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

“የችግሩ ሁኔታን ለማጣራት ብዙ ሰዓት ወስደን ስናጣራ ነበር፡፡ ሙሉ ዝርዝር መስጠት ስለማልችል ነው እንጂ ያየናቸው፣ የገመገምናቸው፣ በየቦታው የተፈጠሩ ችግሮች አይተናል፡፡ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ ኦሮሞዎች ያሉበት መጠለያ ነውና ለዚህ ነው የኦሮሚያ ፖሊስ እና ሌሎች የመስተዳድር አካላት እዚያ ላይ የሚሳተፉት እንጂ መስተዳድሩ የሌላ ክልል መስተዳድር እንደሆነ ብንገነዘብ ጥሩ ነው፡፡ አጠቃላይ ስለ እዚህ የምንግራችሁ ሌላ ቦታም ችግሮች ይከሰታሉ፤ እርሱ በራሱ መንገድ እየተጣራ ነው፡፡ በኦሮሚያ [ክልላዊ] መንግስትም፣ በሌሎች በኦህዴድም፣ በኢህአዴግም አጣርቶ ያው አቅጣጫ እየተቀመጠበት ነው ያለው፡፡ ከዚያ ውጭ ትላንትና በተፈጠረው ሁኔታ ጉዳዩ ተጣርቶ፣ በትክክልም የሰው ህይወት ያጠፋ አካል ተጠያቂ መሆን እንዳለበት የሁላችንም አቋም መሆን እንዳለበት መረዳት ጥሩ ነው ለማለት ነው” ይላሉ የዞኑ አስተዳዳሪ።

በሐማሬሳ ግጭት ሰዎች መሞታቸውን በመቃወም እና የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ ለመጠየቅ ከመጠለያው አቅራቢያ በሚገኘው ሀሮሚያ ዩኒቨርስቲ ያሉ ተማሪዎች ዛሬ ተቃውሞ አሰምተው ነበር፡፡ ተቃውሞ እንደነበር ያረጋገጡት አቶ ጀማል ተማሪዎችን ለመበተን ጥይት ተተኩሷል መባሉን ግን ያስተባብላሉ፡፡ የተተኮሰው ጥይት ሳይሆን የተሰበሰቡ ሰዎችን ለመበተን አገልግሎት ላይ የሚውለው «አስለቃሽ ጭስ ነው» ባይ ናቸው፡፡ ከምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሄዱ አመራሮች በስፍራው ተገኝተው ሁኔታውን ለማረጋጋት መሞከራቸውንም አስረድተዋል፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic