በሊቢያ ግንባታ የጀርመን ሚና | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 14.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

በሊቢያ ግንባታ የጀርመን ሚና

ሊቢያ ዉስጥ ህዝብ ወደጎዳና ግልብጥ ብሎ ወጥቶ በሀገሪቱ የለዉጥ ምዕራፍ ከጀመረ ሁለት ዓመት ሊሞላዉ ነዉ። በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበሩት ሞዐመር ኤል ጋዳፊም ከዚህ ዓለም ካለፉ ዓመት መንፈቃቸዉ ተቃርቧል። ዛሬም ግን የሊቢያ የወደፊት እጣ ፈንታ እንቆቅልሽ አልተፈታም።

default

የቀድሞዉ አማፂ ቡድን ስልጣን ይዟል። ቀደም ሲል አብዮት የተቀጣጠለበት የምሥራቁ ክፍል በማዕከላዊ መንግስት ላይ ያለዉ ቁጣ እየጨመረ ነዉ፤ በዚህም የመከፋፈል ሁኔታ ከወዲሁ መታየት ጀምሯል። በደቡብም ቢሆን የሀገሪቱን ድንበር መቆጣጠር ስላልተቻለ የሰከነ ሁኔታ አይታይም። የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዜጎች ወደሊቢያ እንዳይጓዙ እያስጠነቀቀ ቢሆንም ሀገሪቱን በማረጋጋትና በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታዉ ረገድ የጀርመን መንግስት ከአዉሮጳ ኅብረት ጋ በመተባበር እየሠራ ይገኛል።  በሊቢያ ከህዝባዊዉ አብዮት ወዲህ የተጠበቀዉ ለዉጥ እንደታሰበዉ ፈጥኖ ፍሬዉ የሚታይ አይመስልም። ምንም እንኳን ባለፈዉ ዓመት ሐምሌ የተካሄደዉ አጠቃላይ ምርጫና ዘንድሮ ጥቅምት ላይ የተከናወነዉ የመንግስት ምሥረታ ለዴሞክራሲ የመሠረት ድንጋይ መሆናቸዉ ባይካድም፤ ሊቢያ ዉስጥ ያለዉ ዉጥረት በቋፍ ያለዉን የፀጥታ ይዞታ እና የዴሞክራሲ ሂደት እንዳያጨናግፍ ያሰጋል።

በምስራቅም ሆነ በደቡብ አካባቢ ከሚታየዉ አለመረጋጋት በተጨማሪ ከጎረቤት አካባቢ ከማሊ የተሳደዱት አማፅያን የሊቢያን ድንበር ጥሰዉ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ አለ። ይህን ለማስወገድም የጀርመን መንግስት በአዉሮጳ ኅብረት ፕሮጀክት ሥር ሊቢያ የደቡብ ድንበሯን ፀጥታ የምታስጠብቅበትን ሂደት ይደግፋል። በዚህ ፕሮጀትም የሊቢያ ኃይሎች ይህን ኃላፊነት እንዲረከቡ ስልጠና ይሰጣል። ጀርመን ከአዉሮጳ ኅብረት ጋ በመተባበር በሚያካሂደዉ ፕሮጀክት አማካኝነትም ለዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ወደ4,3 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ቀርቧል።

የጂኦኤኮኖሚ ፕሮፌሰር እና በማይንዝ ጀርመን የአረቡ ዓለም ምርምር ማዕከል ኃላፊ ጉንተር ማየር እንደሚሉት ከተቋማቱ መካከልም አንድ ኮሚሽን ተቋቁሞ ለሀገሪቱ ህገመንግስት እያረቀቀ ነዉ፤ በጀርመን ድጋፍ በሚዘጋጀዉ አዲስ ህገመንግስት መሠረትም በያዝነዉ የጎርጎሮሳዊ ዓመት 2013 አጋማሽ ላይ የምክር ቤት አባላትና ፕሬዝደንት ይመረጣል።

«ጀርመን በተለይ በዴሞክራሲ ግንባታዉ ሂደት፤ በምርጫ፤ በምርጫ ዝግጅት የጀርመን የምርጫ ጉዳይ አዋቂዎች በሚሳተፉበት ሁኔታ ታግዛለች። ከአዉሮጳ ኅብረት ጋ በመተባበርም የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከሩ ላይ ትሠራለች።»

Dossierbild Trptychon Libyen Bundesaußenminister Guido Westerwelle und Bundesentwicklungsminister Dirk Niebel Teil 2

ሊቢያ ዉስጥ የቀላል ጦር መሳሪያዎች ዝዉዉር እጅግ ከፍተኛ ነዉ። የሊቢያ ባለስልጣናት ያልበረደዉን አመጽ ለመቆጣጠር እንዲችሉም የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከመሳሪያ ቁጥጥር አንስቶ የተቀበሩ ፈንጂዎችን የማምከን እና ያለፈዉ ጦርነት ቅሪት ለማስወገዱ ተግባር ድጋፍ እየሰጠ ይገኛል።

ሊቢያ ዉስጥ አዲስ የፖለቲካ ስርዓት ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን መልሶ የመገንባት ተግባርም እየተከናወነ ይገኛል። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ማዕቀቦች ቢነሱም ኤኮኖሚዉ እንዲጠናከር ሊሠሩ የሚገባቸዉ በርካታ ተግባራት ከፊት ተደቅነዋል።

Firma Wintershall Produktionsanlagen nahe der Oase Jakhira in der libyschen Wüste

በሰሜን አፍሪቃ የጀርመን ኢንዱስትሪና ንግድ ማኅበር ተጠሪ ሽቴፈን ቤህም እንደሚሉት ግን የጀርመን ኩባንያዎች በዚህ ለመሳተፍ ዋስትና ያጡ ይመስላል፤

«ንግዱ በርግጥ እየተካሄደ ነዉ ነገር ግን ባለ ወረቶች ገንዘባቸዉን እዚያ ሥራ ላይ ለማዋል ቁጥብነት ይታይባቸዋል። ምክንያቱም በአካባቢዉ ካለዉ ያለመረጋጋት ሁኔታ በመነሳት እርግጠኛ መሆን አልቻሉም።»

እሳቸዉ እንደሚሉትም በጎርጎሮሳዊዉ 2012ዓ,ም ጀርመን ወደሊቢያ የ650 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ ንግድ አካሂዳለች። ከህዝባዊ አመፁ አስቀድሞ ይህ ንግድ  አንድ ቢሊዮን ዮሮ ይደርስ ነበር። ሊቢያ ከጀርመን በብዛት የምትገዛዉ የግንባታ መሣሪዎችን ነበር። አሁን ግን በሚሊሻዎች መካከል ለስልጣን የሚካሄደዉ ዉጊያ ለግንባታ ይደረግ የነበረዉን ርብርብ ገትቶታል። ንግዱም ቀዝቅዟል። በግማሽ ተገንብተዉ የቆሙ የመስሪያ ቤት እና የመኖሪያ ህንፃዎች ከምንም በላይ በመታደስ ላይ የነበረዉ የትሪፖሊ አዉሮፕላን ማረፊያ ያለ ተመልካች በጅምር ከቀሩት የግንባታ ሥራዎች ይጠቀሳሉ። ሽቴፈን ቦህም እንደሚሉትም የጀርመን የግንባታ ኢንዱስትሪዎች ባልተረጋጋዉ የሊቢያ ይዞታ ዉስጥ ገብተዉ ለመሥራት ፍላጎት የላቸዉም። ለነገሩ ገንዘቡ ቀርቦ ወደተግባራዊ እንቅስቃሴ ይገባ ቢባልም እንኳ የፀጥታዉ ሁኔታ እጅግ በርካታ ባለሙያዎችና ሠራተኞችን አሳጥቷታል።

ዲያና ሆዳሊ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic