በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች እንግልት | አፍሪቃ | DW | 14.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

በሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች እንግልት

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች መርማሪ ኮሚሽን ይፋ የሆነው መረጃ አስደንጋጭ ገጽታን ይዟል። መረጃው ሊቢያ የሚገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ፈላጊዎች ከፍተኛ የመብቶች ጥሰት እየተፈጸመባቸው መሆኑን ያሳያል። ጉዳዩን የመረመረው የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለሙያዎች ድርጊቱን በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ተብሎ ሊቆጠር እንደሚችል ገልጸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:22

«የተመድ ምርመራ አካሂዷል»

ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ሊቢያ ውስጥ ባለፉት ቀናት ስደተኞች ላይ ያነጣጠረ የጅምላ አፈሳና እስር እንደተካሄደ አረጋግጠዋል። ስደተኞች ለአደጋ ተጋልጠዋል ያሉት እነዚህ ድርጅቶች የአውሮጳ ሃገራት ሊቢያ ውስጥ ከሚገኙ ተጓዳኞች ጋር በትብብር እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል። አሳሳቢውን መረጃ ይፋ ያደረገው የተመድ ብቻ አይደለም። ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶችም ተመሳሳይ ስጋታቸውን ያሰማሉ።

«ይኽ በቅርብ ዓመታት ሊቢያ ውስጥ ስደተኞች ላይ የተካሄደ የዘፈቀደ እስራት ነው። ስደተኞችን በብዛት ሰብስበው ሲያስሩ ይኽ የመጀመሪያ አይደለም። አሁን ከ5000 ሺህ የሚበልጡ ስደተኞች ሴቶች እና ሕጻናት ሳይቀሩ እስር ቤት ገብተዋል።»

ይላሉ አሌክሳንድራ ሳአይህ በሊቢያ የኖርዌይ የስደተኞች ኮሚሽን ተጠሪ። በሰሜን አፍሪቃዊቱ ሀገር የሚገኙ አብዛኞቹ ስደተኞች በከፍተኛ ፍርሃት ላይ ናቸው።

«ሁኔታው በጣም ውጥረት የበዛበት ነው። ከእኛ ጋር ግንኙነት ያላቸው ስደተኞች እንደሚነግሩን ከቤታቸው ለመውጣት ሁሉ ፈርተዋል። አስተማማኝ ስላልሆነ ሊቢያውያን ጎረቤቶቻቸው ከቤታችሁ አትውጡ እያሉ እንደሚነግሯቸው ሰምተናል። ስለዚህ ሰዎቹ በጣም ፍርሃት አድሮባቸዋል።»

ድንበር የለሽ የሃኪሞች ድርጅትም የጅምላ እስር መካሄዱን ካረጋገጡት አንዱ ነው። ባለፈው ሳምንት ብቻ በዋና ከተማ ትሪፖሊ በሚገኘው ማጎሪያ ስፍራ የታሰሩት ስደተኞች ቁጥር በሦስት እጅ ከፍ ብሏል። ስደተኞቹ በታሰሩበት ቦታም ውኃም ሆነ ምግብ የለም። በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባለሙያዎች የተካሄደው ምርምራ ውጤት ይፋ እንዳደረገው ግድያ፣ ቁም ስቅል ፣ ባርነት እና አስገድዶ መድፈር ስደተኞቹ ላይ ተፈጽሟል። ሰለባዎቹ ሊቢያ ውስጥ የመጨረሻዎቹ ደካማዎች ከምንም በላይ ስደተኞች መሆናቸውን ምርመራውን ካደረገው የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብባዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች አንዱ ቻሎካ በያኒ ይናገራሉ።

«ምርመራችን አክሎም ስደተኞች እና ጥገኝነት ፈላጊዎች በእስር ቤቱ ውስጥ እና በሕገወጥ አሸጋጋሪዎች  ለተለያዩ ወከባና ጥቃቶች መጋለጣቸውን ያሳያል። ይኽ ጥቃትም በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተዋናዮች በተቀናጀ ሁኔታ በመንግሥት ድጋፍ የሚፈጸም ነው።»

ሊቢያ በታጣቂ ሚሊሺያዎች፣ በጎሳዎች ወይም በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ተጽዕኖ ስር የተከፋፈለች መሆኗን ከመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለሙያዎች አንዱ የሆኑት ትራሲ ሮቢንሰን ይናገራሉ። እሳቸው እንደሚሉት ስደተኞች ላይ የዘፈቀደ እስር የሚፈጸመው በሚሊሺያዎቹ እና በመንግሥት ነው። ሊቢያ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እና በተቀናጀ መልኩ ይደረጋል ያሉት ይኽ የመብት ጥሰትም በሰብዓዊነት ላይ እንደተፈጸመ ወንጀል የሚቆጠር መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

በመርማሪዎቹ የቀረበው ዘገባ አክሎም ስደተኞቹን እያሰቃዩ ወደ እስር ቤት በመላኩ በኩል የሊቢያ የባሕር ጠረፍ ጠባዊዎችም እጅ እንዳለበት አመልክቷል። የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች ስልጠናም ሆነ ትጥቅ ያገኙበት በአውሮጳ ሕብረት ነው። በዚህም ምክንያት የረድኤት ድርጅቶቹ ሕብረቱ ሊቢያ ውስጥ ያሉ አጋሮቹን ጉዳይ ዳግም እንዲያስብበት ጥሪ አቅርበዋል።

«ለጋሽ ሃገራት በተለይ በአውሮጳ የሚገኙት ብዙ ሊያደርጉ ይገባል ይኽ ሊቢያ ውስጥ ስደተኞችን እጅግ ለሚያሰጋው ሁኔታ የማንቂያ ጥሪ ነው፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ጣልቃ ሊገባ ይገባል።»

ሸዋዬ ለገሠ/ዮርገን ስትሪያክ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic