በሂትለር ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ 70ኛው ዓመት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 21.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

በሂትለር ላይ የተቃጣው የግድያ ሙከራ 70ኛው ዓመት

የብሔራዊው ሶሻሊስት ጦር መኮንኖች እአአ ሀምሌ 20፣ 1944 ዓም አዶልፍ ሂትለርን ለመግደል ያደረጉት ሙከራ ሰባኛ ዓመት ትናንት በበርሊን ፕሬዚደንት ዮአኺም ጋውክ እና የመከላከያ ሚንስትር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ፣ እንዲሁም ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ታስቦ ዋለ።

ጥቂት የጦር መኮንኖች ያኔ የያዙት የግድያ ሙከራቸው ዕቅድ ይዘው ነበር። ዕቅዳቸው ግን ከሸፈ። ሂትለርን በመጠኑ ከማቁሰል ያላለፈ ውጤት አላስገኘላቸውም ነበር። ምንም እንኳን ይኸው ሙከራቸው ትልቅ የታሪክ ሂደትቢሆንም፣ ጀርመናውያን ለብዙ ጊዜ ግድያውን ላሴሩት እና በሂትለር ለተረሸኑት አርበኞች የሚገባቸውን አክብሮት ለመስጠት ፈቃደኞች አልነበሩም።

የብሔራዊ ሶሻሊዝም ወይም የናዚን አገዛዝ ለማብቃት በሂትለር አንፃር የተካሄደውን ሙከራ አድናቆት መስጠቱ እጅግ ከብዷቸው ነበር። ዛሬ እንደ ብዙ የማያነጋግረው ታሪካዊ ድርጊት የረጅም እና አከራካሪ ሂደት ውጤት መሆኑን በሂትለር አንፃር በዚያን ጊዜ ተቃውሞ ያሳዩ ጀርመናውያን ያካሄዱትን ታሪክ ለማስታወስ የተቋቋመው የበርሊኑ ማዕከል ኃላፊ ዮሐንስ ቱኽል አስታውቀዋል። ያኔ የተፈጸመው ኢሰብዓዊ ድርጊት ቸላ ተብሎ እና ሆን ተብሎ እንደተረሳ ቱኽል ያስታውሳሉ።

እአአ ሀምሌ፣ 1944 ሂትለርን ለመግደል የተደረገው ሙከራ በናዚ ዘመን የተካሄደው ዋነኛው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነበር። ይህንኑ የመፈንቅለ መንግስቱን ሙከራ ያካሄዱት በብዛት ከመሣፍንታዊ ቤተሰብ እና ከራሱ ከጦሩ አመራር የተውጣጡ መኮንኖች ነበሩ። ክላውስ ፎን ሽታውፍንበርግ እና ተባባሪዎቻቸው ነበሩ ሂትለርን ያኔ በአሁኗ ፖላንድ ውስጥ በሚገኘው በቮልፍሻንሰ በሚገኘው ጽህፈት ቤቱ ፈንጂበማንጎድ ሊገድሉት የሞከሩት። ሙከራው ከሸፈ። ሽታውፍንቤርግ ለነገታው ተረሸኑ። በቀጠሉት ቀናትም ስጥ ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጋ ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ አንድ መቶ አሥር የጦር መኮንኖችም የሽታውፍንበርግ ዕጣ ገጠማቸው።

Claus Graf Schenk von Stauffenberg

ክላውስ ሽታውፍንበርግ

ለሂትለር ታማኝነትን በሰንደቃላማቸው የፈጸሙትን መሀላ ያላከበሩ ሀገረ ከሃዲዎች ነበር የታዩት። ብዙዎቹ ጀርመናውያንም ይህን አስተሳሰብ በመደገፍ ሴረኞቹን ከሀዲዎች አድረገው ተመልክተዋቸዋል። ይህ በጀርመናውያኑ ዘንድ የአስተሳሰብ ለውጥ መታየት የጀመረው ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ የመጀመሪያው የጀርመን ፕሬዚደንት የነበሩት ቴዎዶር ሆይስ እአአ በ1954 ሀገር ክህደት እንዳልነበረ እና የሽታውፍንበርግም ስራ የጎበዝ ሀገር ወዳድ አርበኛ ስራ መሆኑን የተቃውሞው አሥረኛ መታቢያ ዓመት ላይ ከተናገሩ በኋላ ነው።

« የጦር መኮንኖቹ ሀገራቸውን ለመከላከል በሰንደቃላማቸው መሀላ የፈፀሙለት ሰው፣ ማለትም ፣ሂትለር ራሱ ብዙ ጊዜ ቃለ መሀላውን በሕጋዊ፣ ሞራላዊ እና ታሪካዊ መንገድ ያፈረሰ ግለሰብ ነበር። »

ያኔ ነበር የሀምሌ 20፣ 1944 ዓም ተቃውሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የታሰበው።

በሂትለር ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ አሥር ዓመት ሲሆነው ሆይስ ያሰሙት ዲስኩር የጀርመናውያኑን የታሪክ አመለካከት እንደቀየረውየሕግ ባለሙያው ሩዲገር ፎን ፎስም ለዶይቸ ቬለ አስረድተዋል።

« በዚህም የተነሳ የ1954 ዓም የቴዎዶር ሆይስ ዲስኩር በጀርመናውያን ዘንድ ስለተቃውሞው ታሪክ የነበረውን አመለካከት በመቀየሩ ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቶዋል። »

ሩዲገር ፎን ፎስ ከሴረኞቹ አንዱ የነበሩት ፎን ፎስ ልጅ ሲሆኑ፣ በበርሊን ያለው የሀምሌ 20፣ 1944 ዓምን የምርምር ተቋምውስጥ በሚያከናውኑት ተግባር የአባታቸው ፎን ፎስ፣ የነክላውስ ፎን ሽታውፍንቤርግ እና የአቻዎቻቸው ታሪካዊ ስራ እንዳይረሳ አበርክተዋል።

ሩዲገር ፎን ፎስ ለዚሁ ሰቫኛ መታሰቢያ ብለውይኸውታሪካዊ ዕለት በይፋ በታሰቡባቸው ያለፉት ዓመታት ስነ ስርዓት ላይ የቀረቡ ዲስኩሮችንእና እነዚህ ዲስኩሮች ሀምሌ 20፣ 1944 ን በተመለከተ የነበረውን አስተሳሰብ በመቀየሩ አኳያ የያዙትንትርጓሜ የሚያስረዳ አንድ መጽሐፍ አውጥተዋል።

እንደ ደራሲው ካርል ሱክማየር አስተያየት፣ ሩዲገር ፎን ፎስ ያሳተሙት መጽሐፍ በሂትለር ላይ የተደረገው የግድያ ሙከራ ለብዙ ዓመታት እንደትልቅ ታሪካዊ ሂደታ ያልታየበትን ሁኔታ በግልጽ አስቀምጦዋል።

« ዲስኩሮቹን የሚያነብ ግለሰብ በሂትለር አንፃር የነበረውን ተቃውሞ በተመለከተ በኛ በጀርመናውያን ዘንድ የተካሄደውን ሰፊ ክርክር እና ይህም አንዱ የታሪካችን አካል መሆኑን የሚያሳይ ጥሩ ሥዕል ሊያገኝ ይችላል። »

ሞኒካ ዲትሪኽ/አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic