1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሁለት ክልሎች የታየዉ የድጋፍ እና የተቃዉሞ ሰልፎች ጉዳይ

ሰኞ፣ መጋቢት 25 2015

በኦሮሚያ ክልል መንግሥትን የሚደግፍ ፣ በአማራ ክልል ደግሞ መንግሥትን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። በኢትዮጵያ በሁለት ክልሎች ውስጥ የተለያየ ግብ የነበራቸው የተቃዉሞ እና የድጋፍ ከፍተኛ ሰልፎች ሲካሄዱ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ። እነዚህ ሰልፎች ይህ በሃገሪቱ ፖለቲካ እና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ምን አንደምታ ይኖረዉ ይሆን ?

https://p.dw.com/p/4PdVj
Äthiopien | Unterstützer der Prosperity Party Ethiopia
ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

ደም ያፋሰሰው ጦርነት በተኩስ አቁም ስምምነት ሲቋጭ፣ ሌሎች የፖለቲካ ውጥረቶች ግን ሊረግቡ የቻሉ አይመስልም።

በኦሮሚያ ክልል መንግሥትን የሚደግፍ ፣ በአማራ ክልል ደግሞ መንግሥትን የሚቃወም ሰላማዊ ሰልፎች ተካሂደዋል። በኢትዮጵያ በሁለት ክልሎች ውስጥ የተለያየ ግብ የነበራቸው የተቃዉሞ እና የድጋፍ ከፍተኛ ሰልፎች ሲካሄዱ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት በአማራ እና በኦሮሞ ብሔር ልህቃኖች፣ ፓለቲከኞች እና ያገባናል ባዮች መካከል የታየዉ ትስስር በተለይ ህወሓትን ከማዕከላዊ ስልጣን የገፋ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማጠናከርን ያለመ የፖለቲካ ትብብር ተደርጎ ነበር። ይህ ለሃገሪቱ የፖለቲካ እና ማህበራዊ ጉዳይ ላይ ምን አንደምታ ይኖረዉ ይሆን ?

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የፖለቲካ ተንታኞች "ኦሮማራ" ይባል የነበረው የአማራ እና ኦሮሞ ፖለቲከኞች ትብብር ከጅምሩ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ፣ ጊዜያዊ እና በጥርጣሬ መተያየትን በዘላቂነት የፈታ ስላልነበር አሁን ላይ ውጥረት የሚመስል ግንኙነት እንዳይታይ ማድረግ አለመቻሉን ገልፀዋል። ያነጋገርናቸው እንዲህ ያለው ውጥረት በዚሁ ከቀጠለ በጠቅላላው የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ ማበላሸቱ አይቀርም የሚለውን ሥጋት በመያዝ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል የሚል ሀሳብም ሰንዝረዋል። አክለውም ነገሩን አቅልሎ ባለማየት ተቀራርቦ በመነጋገር መፍትሔ መፈለግ ያስፈልጋል ብለዋል።  

Äthiopien | Premierminister Abiy Ahmed Ali
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

ቲም ለማ እና ኦሮማራ ይባሉ የነበሩ የፖለቲካ ትብብር ናቸው ተብለው በአንድ በኩል ተስፋ ፣ በሌላ በኩል ሥጋት ፈጥረው የተስተዋሉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዐውድ ልውጠቶች ድህረ ነባራዊ ሁኔታው ሕወሓትን ከማዕከላዊ መንግሥት ከመግፋት ባለፈ የእርስ በርስ ጦርነት አስከትሎ ፣ የዜጎች ያልተቋረጠ ሞት፣ መፈናቀል ፣ የሀብት እና ንብረት ውድመት ማስከተሉ አልቀረም።

ደም ያፋሰሰው ጦርነት በተኩስ አቁም ስምምነት ሲቋጭ፣ ሌሎች የፖለቲካ ውጥረቶች ግን ሊረግቡ የቻሉ አይመስልም። ይህንን በግላጭ ያሳዩ ገዢው መንግሥትን የሚደግፉ እና የሚያወግዙ ሰላማዊ ሰልፎች ትናንት ከላይ የተገለፀውን የፖለቲካ ትብብር የፈፀሙ ወገኖች ማህበራዊ መሠረት ናቸው በሚባሉ አካባቢዎች ተደርገዋል።

ይህ ለምን ሊፈጠር ቻለ የሚለውን በቅድሚያ የጠየቅናቸው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን ነው። "ኦሮማራን ሲፈራረሙ ለገዢው ፓርቲ መጠቀሚያ እንጂ ምንም የረባ ነገር ስላልነበረበት ብዙ ከመሬት የሚነሳ ነገር አልነበረውም። አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ሁሉም ማህበረሰቦች ልኂቃን የሚባሉት የዴሞክራሲያዊ አጀንዳን በጋራ ወደፊት መግፋት አልቻሉም" ። ብለዋል። ምክንያት ያሉትን ሲገልፁ።

ሌላኛው የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ እና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቱ መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ የችግሩን መነሻ በሁለቱ ብሔሮች ዐዋቆች መካከል የሚታይ "የመተማመን አለመኖር" አድርገው ገልፀውታል።

"ይህ ታስቦበት በደንብ ያልተሠራ ነገር እና ጊዜያዊ ትብብር ዘላቂነት እንዲኖረው መሥራት ነበረባቸው፣ አልሠሩም። ለምን ቢባል ሁለቱም ቡድኖች ባንድም ይሁን በሌላ መልኩ እርስ በርስም በጥርጣሬ ዐይን የሚተያይ አይነት ባሕርይ ያላቸው ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።

የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና "በሀቅ ለመደራደር እና ለመነጋገር የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል" በማለት ከጊዜያዊ ትልም ያለፈ ሥራ መሥራት የሚታይ መፍትሔ ነው ብለዋል። "የሁለቱም ወገን ፖለቲከኞች በሰከነ መልኩ የሕዝቦችን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሥራ ሊሠሩ ይገባል" የሚሉት ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ ደግሞ ከይስሙላ ሥራ መውጣት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

መሣሪያ አንግበው ይታገሉ የነበሩ ወገኖች ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ እና ወደ አገራዊ መግባባት እየተመለሱ ባለበት በዚህ ወቅት እንዴት በጎውን ማድረግ ይሳናል የሚሉት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ደክተር መብራቱ ዓለሙ መንግሥትን በተመለከተ ትናንት በተቃራኒ ጎራ የተስተዋለው ድጋፍ እና ተቃውሞ "የአገሪቱን ፓለቲካ የሚያበላሽ" አዝማሚያ በመሆኑ ጥንቃቄ የተሞላው ንግግር ከማድረግ ባለፈ "ነገሩን አቅልሎ መመልከት ተገቢ አይደለም" በማለት የነገሩን ክብደት ጭምር አመልክተዋል።

Äthiopien Parteianhänger Amhara Oromia Region
የድጋፍ ሰልፍ በኦሮምያ ምስል Seyoum Getu/DW

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ እሳቸው በሚመሩት መንግሥት አደጋ ውስጥ እየገባች መሆኑ ተገልጾ ባለፈው ሳምንት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ኢትዮጵያ እየፈረሰች ነው በሚሉ ሰዎች አዕምሮ ውስጥ እንጂ በተግባር በብልጽግና ጎዳና ላይ መሆኗን ተናግረው ነበር።

የአገሪቱን ገዢ  ፓርቲ የመሪነት ሥልጣን ከጨበጡ ትናንት መጋቢት 24 አምስት ዓመታት የሞላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና መንግሥታቸ ላይ ትናንት በኦሮሚያ ድጋፍ ፣ በአማራ ተቃውሞ ሲደረግበት በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ግን በግልጽ የተስተዋለ የአደባባይ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አልነበረም።

"ኦሮማራ" የተባለውን የፖለቲካ ትብብር በወቅቱ የነበሩት የትግራይ የፖለቲካ መሪዎች "ያልተቀደሰ ጋብቻ" በማለት ማጣጣላቸው አይዘነጋም። እኒሁ የትግራይ አመራሮች ከጦርነት ማግስት የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ሰሞኑን ከገዢው መንግሥት ጋር ሰፊ ግንኙነት መጀመራቸው ተስተውሏል።

 

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ