ቆጮን በማሽን | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 09.06.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ቆጮን በማሽን

በደቡባዊ ኢትዮጲያ በምግብነት የሚዘወተረው የቆጮ አመራረቱ አድካሚ፣ አዘገጃጀቱም አታካች እንደሆነ ይነገርለታል። ይህን መነሻ ያደረገው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን የፈጠረው የእንሰት መፋቂያ ማሽን የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዝግጅታችን ትኩረት ነው። ዝግጁቱን አሰናድቶ የላከልን የሀዋሳው ወኪላችን ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ ነው አብረን እንከታተል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:38

የእናቶችን ልፋት በእጅጉ ይቀንሳል

አንዳንዶች ያልተዘመረለት የኢትዮጵያ ሲሳይ በማለት ያንቆላጳጽሱታል፣ ከእንሰት ተክል የሚመረተውን የቆጮ ምግብ፡፡ ምግቡ አሁን አሁን ወትሮ በስፋት ይዘወተርበት ከነበረው የደቡባዊ ኢትዮጵያ አካባቢ በተጨማሪ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎችም እየተለመደ ይገኛል፡፡ በበርካታ ከተሞች በሚገኙ ዘመናዊ ሆቴሎችም በምግብ አማራጭነት እየቀረበ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ቆጮ ለምግብነት ያለውን ጠቀሜታ ያህል አመራረቱ አድካሚ፣ አዘገጃጀቱም አታካች እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ የሰው ጉልበትና ጊዜ የሚበላውን የቆጮ አመራረት ለማሻሻል በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋሟት የተለያዩ የሙከራ ሥራዎች እየተከናወነ ይገኛሉ፡፡

ይህን መነሻ ያደረገው የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በፈጠራ የሠራውን የእንሰት መፋቂያ ማሽን ሰሞኑን አነሆ ይለናል። በዩኒቨርስቲው የኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል የተሠራው ይህ ማሽን የእንሰት ግንዱን በመፋቅ ለምግብነት የሚውለውን የቆጮ ምርት ከተረፈ ምርቱ በመለየት ያወጣል፡፡ የቆጮ ምግብ ለማምረት በሴቶች ላይ የሚደርሰውን የጉልበትና የጊዜ ጫና ያቃልላል የሚል ተስፋ የተጣለበት ይህ የፈጠራ ቴክኖሎጂ የተሠራው የትምህርት ክፍሉ መምህራን በሆኑት ባህረዲን አብደላና ሳህሌ መክቴ አማካኝነት ነው፡፡ 

ቆጮ ለምግብነት ያለውን ጠቀሜታ ያህል አሠራሩ አድካሚ ስለመሆኑ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ መምህራንና የፈጠራ ባለሞያዎቹ ባህረዲንና ሳህሌ ይናገራሉ፡፡ በተለይ የእንሰት ግንዱን የመቁረጥና የመጭመቅ ሥራ በአብዛኛው በእናቶችና በሴት ልጆች ትከሻ ላይ የወደቀ ነው፡፡ በፈጠራ ቴክኖሎጂ የተሠራው ይህ ማሽን ታዲያ እነኚህን ጫናዎች እንደሚያቃልል በተግባር ማረጋገጣቸውን ነው መምህር ባህረዲን የሚናገሩት፡፡

በሀዋሣ ዩኒቨርስቲ የኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ትምህርት ክፍል መምህራን የተሠራው የእንሰት መፋቂያ ማሽን ከቆጮ ምርት በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው መምህራኑ ይናገራሉ፡፡ በተለይ ለቆጮ ለምግብነት የሚውለው የእንሰትና የሙዝ ተክል ግንዶች ተቀራራቢ ባህሪያት እንዳላቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ሙከራ የተካሄደበት ይህ ማሽን በሁለቱም የግንድ አይነቶች ውስጥ የሚገኘውን ቃጫ መሰል ክር በተረፈ ምርትነት ለየቶ እንደሚያወጣ ገልፀዋል፡፡ በዚህም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውለውን ተረፈ ምርት በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ሊያስገኝ እንደሚችል ነው መምህር ሳህሌ የሚናገሩት፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡ አሁን የቀረበው የእንሰት መፋቂያም የዚሁ ጥረት አካል እንደሆነ በዩኒቨርስቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የቢዝነስ ማበልፀጊያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አባተ ኃይሉ ያስረዳሉ፡፡

በእንሰት መፋቂያ ማሽን የፈጠራ ሥራ ሂደት ውስጥ በማሽኑ አጠቃቀም ዙሪያ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች ቀድመው መለየታቸውን የፈጠራ ባለሞያዎቹና መምህራን ተናግረዋል፡፡ በተለይም የፈጠራ ሥራው በገጠር አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውስንነትን ታሳቢ ማድረጉን የሚናገሩት ባህረዲን ለዚህም ማሽኑን በእጅ በመዘወር ፣ በጄነሬተር ወይም በሌሎች የሀይል አማራጮች ለማንቀሳቀስ በሚያስችል መልኩ አሻሽሎ ለማምረት መታቀዱን ገልፀዋል፡፡

የእንሰት ማፋቂያ ማሽኑ ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎችን ለመስራት ትምህርት የተገኘበትና የተነሳሽነት ሥሜትን የፈጠረ እንደሆነ መምህራኑ ይናገራሉ፡፡ በቀጣይ የፈጠራ ሥራው ባለቤትነት የሚያገኝበትና ለማህበረሰብ የሚቀርብበት ሥራዎች በሂደት ላይ እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡

የፈጠራ ሥራዎች የማሕበረሰቡን ችግሮች መነሻ ማድረግ እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ በዚህ መነሻ የቀረበው የእንሰት ማፋቂያ ማሽን የቆጮ ምግብ ለማምረት የሚወጣውን ጉልበት ይቀንሳል፣ ጊዜንም ያሳጥራል ይላሉ በዩኒቨርስቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የቢዝነስ ማበልፀጊያ ማዕከል ሃላፊው አቶ አባተ። በቀጣይ የፈጠራ ሥራው በቴክኖሎጂ ሽግግር አማካኝነት ወደ ማኅበረሰቡ እንደሚሰራጭ ተናግረዋል፡፡

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ 
ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ  

Audios and videos on the topic