ቆይታ ከአንጋፋዉ ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ጋር | ባህል | DW | 05.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ቆይታ ከአንጋፋዉ ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ጋር

ጋዜጠኛ ያቆብ የተወልዱት እንደ አዉሮጳ አቆጣጠር ሰኔ 19 ቀን 1929 ዓ/ም ከአዲስ አበባ ወደ 320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ነቀምቴ ከተማ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:10
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:10 ደቂቃ

ቆይታ ከአንጋፋዉ ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ጋር

አንጋፋዉ ጋዜጠኛዉ ያዕቆብ ከአባታቸዉ ከአቶ ወልደማርያም ሹባ ሌቃ፣ እንዲሁም ከእናታቸዉ ከወ/ሮ ወለተሚካኤል ሰንቤቶ ጋርባ እንደ አዉሮፕያኖቹ አቆጣጠር ሰኔ 19 ቀን 1929 ዓ/ም በነቀምቴ ከተማ ተወለዱ። የአባታቸዉ ስም አያና እንደነበረ ግን በጊዜዉ ሁኔታ የክርስትና ስም ወልደማርያም እንደተሰጣቸዉም ጋዜጠኛዉ ያቆብ አስታዉሰውኛል። አባታቸዉ አቶ ወልደማርያም የነቀምቴ ሰዉ ሲሆኑ የሲዊድኑ ኤቫንጄልካል ሚሺን ያሰራዉ ሐኪም-ቤት ዉስጥ ሲሰሩ እንደነበረ ይናገራሉ። እናታቸዉ ወ/ሮ ወለተሚካኤል ከግምቢ ከተማ ወደ ነቀምቴ  ለሕክምና ሲመጡ ከአቶ ወልደማርያም ጋር በፍቅር ተዋደቁ። ይህ ሐኪም-ቤት ሁለቱንም ፍቅረኛሞች ከማገናኘቱም ባሻገር ለጋዜጠኛዉ ያዕቆብ የትውልድ ስፍራ በመሆኑ ትልቅ ትዉስታ እንዳለዉም ነግረውኛል።

ነቀምቴ ከተማ የተወለደዉ ወጣቱ ያዕቆብ ወልደ ማርያም ከልጅነቱ ኤሌክትሪካል ኢንጂኒየር የመሆን ሕልም ቢኖረዉም፤ አንጋፋ ጋዜጠኛ ይሆናል ተብሎ አልነበረም ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤት የተላከዉ። በትምህርት ዘመኑ ግን በተለይ እንግሊዝኛ ቋንቋን ለመማር የነበረዉን ግን ዛሬም ያስታዉሱታል።

Kaiser Haile Selassie von Äthiopien (picture-alliance/dpa)

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተሰደዉ ከነበረቡበት ከታላቋ ብርታንያ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኃላ

እንደ አዉሮጵያኖቹ አቆጣጠር በ1941 ዓ/ም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተሰደዉ ከነበረቡበት ከታላቋ ብርታንያ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። እሳቸዉ እስኪመለሱ ድረስ የነበሩት ትምህርት-ቤቶች ከ1ኛ-6ኛ ክፍል ድረስ ብቻ እንደነበረ ጋዜጤኛዉ ያዕቆብ ይናገራሉ። ከሁለት ዓመት በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ በኮቶቤ አካባቢ በስማቸዉ የመጀመርያዉን ሁለተኛ ደረጃ፣ ማለትም ከ8ኛ-12ኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምር ትምህርት-ቤት ከፈቱ። ይህም ለያኔዉ ወጣት ያዕቆብና ለሌሎች ከፍተኛ ትምህርትን ለመማር አቅምና ፍላጎቱ ለነበራቸዉ በር ከፈተ።

ይሁን እንጅ፣ በዛን እድሜ ከቤተሰብ መራቁ ከባድ ቢሆንም፣ ከነቀምቴ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣትም መንገዱ ቀላል አንዳልነበረም ያስታዉሱታል። ዛሬ ከነቀምቴ ተነስቶ አድስ አበባ ለመድረስ የግማሽ ቀን ጉዞ ነዉ። የዛሬዉን አያድርገዉና በዛን ግዜ ጉዞዉ እስከ ሰባት ቀን ስወስድ እንደነበር ጋዝጤኛዉ ያቆብ አጋርቶኛል።

ጉዞ ወደ ላንደን

በግዜዉ አገሪቱ የተማረና ማስተማር የሚችል የሰዉ ጉለበት እጥረት እንደነበራት የታሪክ መዝገቦች ያሳያሉ። በግዜዉ ለአንደኛም ሆነ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት-ቤቶች መምሕራኖች ከደቡብ አፍርቃ፣ ከአሜርካ፣ ከታላቋ-ብርትንያ እንዲሁም ከሕንድ መንግስት ስያስመጣ እንደነበረም አንስተዋል። ይህን ችግር ለመፍታት ታዲያ ጎበዞቹን ተማሪዎች ወደ ዉጭ ልኮ ማስተማር ተጀመረ። ከእነሱ አንዱ ወጣቱ ያቆብ ነበር። ያኔም ሰባት ሆነዉ ነበር ወደ ለንደን ያቀኑት። ለትምህርት ሲላኩ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ እንዲማሩ ትዕዛዝ ተሰጣቸዉ። የኔ መርጫ አልነበረም ይላሉ፣ ጋዜጠኛዉ ያቆብ።

መንግስት ጥሩ ዉጤት ያላቸዉ ተማርዎችን መልምሎ ወደ አሜርካና ወደ ታላቋ-ብርታንያ ልኮ ትምህርታቸዉን እንድካታተሉ መንግስት ስያደርግ ነበር። እንደ አዉሮጵያኖቹ በመስከረም ወር በ1950 ዓ/ም ተማርዉ ያቆብ ወደ ላንደን የሚወስደዉን የማትርክ ፈተና ተፈተነ። ፈተናዉን ከተፈተኑት ከ85 ተማርዎች ዉስጥ ሁለተኛ በመዉጣት ከሌሎች ሰባት ተማርዎች ጋር ወደ ላንደን እንዳቀኑ ይናገራሉ።

በደቡብ-ምዕራብ ለንደን የሚገኘዉ በክንግስቶን አፕ-ኦን ቴምስ እንጅኔርንግ ለመማር የሚያዘጋጃቸዉን የሒሳብ ትምህርትን ጨምሮ ከፍተኛ ተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን ወሰዱ። በነዚህ ትምህርቶች ንድፈ ሐሳባዊ ላይ ጥሩ ዉጤት ቢያስመዘግቡም ወደ ትግበራዉ ሲመጣ ከባድ እንደሆነባቸዉም አልደበቁም።

በለንደን ቆይታቸዉም እንደነ ዘ-ኦብስርቬር፣ ዘ-ደይል ቴሌግራፍ፣ ዘ-ማንቼስቴር ጋርድያን/ አሁን ዘ-ጋርድያን  እና ሌሎች መፅሔቶችን ያነቡ ነበር። የYMCA/የክርስትያን ወንድ ወጣቶች ማህበር/ አባል ስለነበሩም እግር ኳዋስ ከነሱ ጋር ይጨወታሉ፣ በሩጫዎች በመሳተፍ ጋዜጠኛዉ ያዕቆብ ግዜያቸዉን በለንደን አጣጥመዋል።

ይሁን እንጂ የራስ ሕመም ስለነበራቸዉ ወደ ሐኪም ጋር ሄዱ፣ እረፍት እንደሚያስፈልጋቸዉ ነገራቸዉ። ይህም ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ምክንያት ሆነ።  የሃኪም ማስረጃም ትምህርታቸዉን በገንዘብ ይደግፍ ወደ ነበረዉ ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪ ኃይል ባለስልጣን ተላከ። ይህ ሁኔታ እንዳበሳጫቸዉ ይናገራሉ።

ሌላ ትምህርት ለመማር ወደ ለንደን እንደምመለሱም ቃል ቢገባላቸዉም በብዙ ምክንያቶች ያ ሳያስካ ቀርተዋል። ከዛም በአድስ አበባ የነበረዉ የአመሃ ደስታ ትምህርት-ቤት፣ እንድሁም በነቀምቴ ዉስጥ በመምህርነት እንደ አዉሮፕያኖቹ አቆጣጠር በ50ዎቹ አጋማሽ ለአራት ዓመት አገልግለዋል።

ጋዜጠኛ ያቆብ ወልደማርያም በቅጥር ግብያቸዉ

ጋዜጠኛ ያቆብ ወልደማርያም በቅጥር ግብያቸዉ

ከኢንጅኔርንግ ወደ ጋዜጠኝነት

በነቀምቴ ከተማ በመምህርነት ኢያገለገሉ በነበሩበት ወቅት መምህር ያዕቆብ ከአከባብዉ ባለስልጣን ጋር ተጋጩ። ወደ አዲስ አበባም በመመለስ እንደአዉሮፕያኖቹ አቆጣጠር በ1959 ዓ/ም በኢትዮጵያ የኤሌክትርክና ሃይል ባለስልጣን ስራ አገኙ።

ጋዜጠኛ ያዕቆብ በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ባለስልጣን ሥር የኤሌክትሪክ ፖል ተከላ ሥራም አገልግለዋል። ሥራዉ ግን ቀላል አልነበረም።

ወደ አዲስ አበባ ቢመለሱም ከባለስልጣኑ ጋር የነበራቸዉ ዉይይት ዉጤታማ አልነበረም። ያላቸዉን የስነጽሑፍ ክህሎት የሚያዉቁ የቅርብ ጓደኛቸዉ ያኔ የኢትዮጵያ ሄራልድ ዋና አዘጋጅ የነበሩትን አፍሮ-አሜርካዊዉ ዶክተር ደቭድ ታልቦትን እንዲያነጋግሩ ጠቆሟቸዉ።

በ50ዎቹ መጨረሻ ጋዜጠኛዉ ያዕቆብ፣ ከዶክተር ታልቦት በኋላ፣ የመጀመርያዉ ኢትዮጵያዊ የጋዜጣዉ ዋና አዘጋጅ ሆኑ። ጎበዝ ከሚሏቸዉ የሥራ ባልደረቦቻቸዉም እነ ነጋሽ ገብረ ማርያም፣ አያሌዉ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ስዩም አየለ እና ግሆን ሃጎስን ያስታዉሱታል። የፊዉዳሉን ሥረዓት በርዕስ-አንቀፅ መተቸት ይቅርና ወንጀል መዘገብ እንደማይችሉ የሚናገሩት ጋዜጠኛዉ ያዕቆብ አብዛኛዉ ሥራቸዉ በአፄ ሃኃይለ ሥላሴ እንቅስቃሴዎች ላይ ያተከረ እንደነበረ ይናገራሉ። እሳቸዉ በዚህ ሥራ ብዙም ሳይቆዩ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከስልጣን ተወገዱ።

Portraitbild von Äthiopiens Ex-Diktator Mengistu Haile Mariam (picture alliance/dpa)

ኮሌኔል መንግስቱ ሃይለ ማርያም

ኮሌኔል መንግስቱ ሃይለ ማርያም በ1967 ስልጣን ከተቆጣጠሩት በኋላ በፃፉት ትችት ጋዜጠኛዉ ያዕቆብ በዋና አዘጋጅነት ሥራቸዉ አልቀጠሉም።

ከዛን ግዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሄራልድ ርዕስ-አንቀፅ አንብበዉ እንደማያዉቁም ነግረዉኛል። ከሄራልድ ከወጡ በኋላ በአዘገጅነት መነንና የካቲት የሚባሉ የእንግሊዝኛ መፅሄቶች ላይ ሰርተዋል።

ሦስት ተከታታይ መንግሥታትን ያዩት ጋዜጠኛዉ ያዕቆብ በአገሪቱ የጋዜጠኝነት እድገት-ሂደት አዝጋሚ የሆነዉ በመሪዎቹ «ግፍ» ምክንያት ነዉ ይላሉ።

አፋን ኦሮሞን፣ አማርኛን፣ እንግሊዝኛንና የፈረንሳይ ቋንቋ አቀላጥፈዉ የሚናገሩት ጋዜጠኛዉ ያዕቆብ በጣልያንኛም አልታማም ይላሉ። የአዉሮጳ ሃገራትን፣ አሜርካንና ሌሎች አገሮችንም ጎብኝተዋል። በአዉሮጳዉያኖቹ አቆጣጠር በ1963 እና በ1975 ዓ/ም ወደ ጀርመን መጥቼ አሳማዉን ባልበላም ቢራቸዉን ጠጥቻለዉ ይላሉ።

Ethiopia, Veteran Yacob Woldemariam (Yabo Woldemariam)

ጋዜጠኛ ያቆብ ከልጅ ልጆቻቸዉ ጋር

 የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳሉ ፒያኖ እና ቫዮሊን እንደተማሩ ያወጉኝ ጋዜጠኛዉ ያዕቆብ የሞዛርትና የቤትሆኸንን ሙዚቃዎች፣ እንዲሁም የሮዝንና የፌርድ ኦፔራ አዘዉትረዉ ማደመጥ ይወዳሉ። ምግብን በተመለከተ ግን ከእንጀራና ወጥ ዉጭ የሚያረካኝ የለም ይላሉ።

በመጨረሻም ሊያስተላልፉ የሚፈልጉ መልክት ካለ አልኳቸዉ? የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ከጥንት ጀምሮ በአሉባልታ ላይ የተመሰረተ ነዉ አሉ። መንግሥትም የሕዝቡን የልብ ትርታ ለማዳመጥ እንዲሁም ለፕሮፖጋንዳ ለመጠቀም ሆን ብሎ አሉባልታን እንደሚያሰረጭ ያምናሉ። ግን የጋዜጠኞች ዋና ሥራ መሆን ያለበት አሉባልታዉን ከእዉነቱ አጣርቶ፣ አበጥሮ ለማሕበረሰቡ ማቅረብ መሆኑን መታወስ እንደሚኖርበት ተስፋቸዉ ነዉ።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሠ

    

   
 

Audios and videos on the topic