ቅጡ ያልለየው የሱዳን ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ | አፍሪቃ | DW | 13.04.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ቅጡ ያልለየው የሱዳን ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ

ሱዳንን ላለፉት 30 ዓመታት ሱዳን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ኦማር አልበሽርን ከስልጣን እንዲነሱ ለወራት ሲደረግ የነበረው ተቃውሞ በዚህ ሳምንት ፍሬ አፍርቷል። ሆኖም ሰላማዊ ሰልፈኞቹ አሁንም የጎዳና ተቃውሟቸውን አልገቱም። አልበሽርን ተክተው መሪነቱን የያዙት ወታደራዊ መኮንኖች ስልጣኑን ለሲቪል አስተዳደር እንዲያስረክብ መወትወታቸውን ቀጥለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:16

ቅጡ ያልለየው የሱዳን ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ

መጀመሪያ የዳቦ ጥያቄ ነበር። ዳቦ አለቅጥ ተወደደ የሚል። ቀጥሎ የነዳጅ ድጎማ መነሳት ጉዳይ ታከለበት። ቆየት ብሎ ፖለቲካዊ ለውጦች መጠየቅ ጀመሩ። በፍጥነትም የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ከስልጣን ይውረዱ ወደሚል ተሸጋገረ። ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ የመጣው ተቃውሞ በስተመጨረሻ ፕሬዝዳንቱ መኖሪያ ደጃፍ ደረሰ።

በሱዳን ባለፉት አራት ወራት ተከታትለው ያለፉ እነዚህ ሁነቶች እንደ ብረት የጠነከረ ነው የሚባልለትን የፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር የስልጣን ዘመን ከፍጻሜው ያደረሱ ሆኑ። ላለፉት 30 ዓመታት በሱዳን አዛዥ ናዛዥ ሆነው የቆዩት አልበሽር ትዕዛዛቸውን ተቀብሎ የሚፈጽም ጠፋ። እንደ ቀኝ እጃቸው የሚያዩት የሀገሪቱ ጦር ሰራዊትም ፊቱን አዞረባቸው። ይባስ ብሎ ከሶስት አስርት በፊት በሳዲቅ አልመሀዲ መንግስት ላይ የፈጸሙትን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በራሳቸው ላይ ደገመባቸው። 

“እኔ የመላከያ ሚስትር እና የጸጥታ ኮሚቴ ኃላፊ የዚህን መንግስት መመንገል እና ቁንጮውም መታሰራቸውን አሳውቃለሁ” ሲሉ ወታደራዊ የደንብ ልብሳቸውን ለብሰው እና ማዕረጋቸውን ደርድረው ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በቴሌቪዥን በተላለፈ የቀጥታ ስርጭት የተናገሩት የሱዳኑ መከላከያ ሚኒስትር ናቸው። ይህን ብዙዎች ሲጠብቁት የነበረውን መግለጫ ያሰሙት ሌፍተናት ጄነራል አዋድ ሞሃመድ ኢብን አውፍ አልበሽርን በቀጥታ በስም ከማንሳት ይልቅ የመንግስት ኃላፊነታቸውን መጥቀስ መርጠዋል። ፕሬዝዳንት አልበሽር መታሰራቸውን እና “ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ እንዲቀመጡ መደረጋቸውን” ገልጸዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ አልበሽር ይዘውት የነበረውን ኃላፊነት አዲስ የተቋቋመው ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት መረከቡን አስታውቀዋል። በሱዳን የደም መፋሰስን ለማስወገድም የጦር ሰራዊቱ ለሁለት ዓመታት ያህል ሀገሪቱን እንደሚመራ ይፋ አደርገዋል። ለ16 ሳምንታት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ የቆዩት ሰላማዊ ሰልፈኞች ግን የጦር ሰራዊቱ እርምጃ ከጎዳና ወደ ቤት እንዲመለሱ አላደረጋቸውም። የአልበሽር የስልጣን መነሳት በተነገረበት ዕለት ወታደራዊ ምክር ቤቱ የደነገገውን የሶስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና የሰዓት እላፊ ገደብ ችላ በማለት ተቃውሟቸውን ቀጥለዋል።

በሺህዎች የሚቆጠሩት ተቃዋሚዎች ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንዳደደረጉት ሁሉ ባለፈው ሐሙስም አዳራቸውን በመዲናዋ ካርቱም ከጦር ሰራዊቱ ዋና ጽህፈት ቤት እና መከላከያ ሚኒስቴር ፊት ካለው ጎዳና አድርገዋል። ተቃዋሚዎቹ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖቹ ከአልበሽር የነጠቁትን ስልጣን ለሲቪል ባለስልጣናት እንዲያስረከቡ ሲጠይቁ አንግተዋል። በፈረቃ በሚቀያየሩ ሰልፈኞች ሌትም ሆነ ቀን የማያቋረጠው ተቃውሞ ትላንት አርብም ቀጥሎ ውሏል።

በመላው ሱዳን የነበሩትን ሰላማዊ ሰልፎች በፊት አውራሪነት ሲመራ እና ሲያስተባብር የቆየው የሱዳን ባለሙያዎች ማህበርም ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፊት የሁለት ዓመት ወታደራዊ አገዛዝ እንደሚኖር መታወጁን ተከትሎ ተቃዋሚዎች ሰልፎቻቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርቧል። የማህበሩ ቃል አቃባይ ሳራ አብደልጋሊ ድርጅታቸው “ወታደራዊ አገዛዝን” እንደማይቀበል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አሁን ስልጣኑን የተረከቡት “የቀድሞው አገዛዝ ርዝራዞች ናቸው” ሲሉም ይተቻሉ። “ይህን ፍኖተ ካርታ አንቀበልም፤ እንደ መፈንቅለ መንግስትም እንቆጥረዋለን። የቀድሞው አገዛዝ አባላትን እንደገና በአዲስ መልክ ነው ያመጡት። ህዝቡ ላለፉት አራት ወራት የታገሉላቸውን ዓላማዎች ለማሳካት ትግላችንን እና አብዩቱን እንቀጥላለን” ብለዋል። 

ቃል አቃባይዋ ከዚህም ሌላ የሱዳን ወታደራዊ ምክር ቤትን ወክለው መግለጫ ሲሰጡ የታዩትን ሌፍተናት ጄነራል አዋድ ሞሃመድ ኢብን አውፍ “በሰላማዊ ሰዎች ግድያ ተሳትፎ አላቸው” በማለት ይወነጅሏቸዋል። በወታደራዊ ምክር ቤቱ ያሉት ሌሎች አባላትም ቢሆኑ በአልበሽር መንግስት የብሔራዊ የደህንነት አገልግሎት እና የወታደራዊ ደህንነት መስሪያ ቤት ውስጥ የሚሰሩ እንደነበሩ የሚናገሩት ሳራ ብዙዎቹ የጦር ወንጀሎችን እና በዜጎች ላይ ስቅይት የሚፈጽሙ ነበር ይላሉ። በዚህም ምክንያት በሱዳናውያን ዘንድ ተቀባይነትም ሆነ ውክልና እንደሌላቸው ይገልጻሉ። የእርሳቸው ማህበርም ሆነ ተቃዋሚዎች የሽግግር ጊዜ የሲቪል አስተዳደር በግዴታ መመስረት እንዳለበት እንደሚያምኑ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። 

በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ጥናት እና ምርምር የሚያደርገው አማኒ አፍሪካ የተሰኘው ተቋም መስራች ዶ/ር ሰለሞን አየለ ደርሶ ተቃዋሚዎቹ ይህን ጥያቄ ማንሳታቸው “እንግዳ ነገር አይደለም” ይላሉ። ሆኖም ተቃዋሚዎች ከጦር ሰራዊቱ ጋር የሚያደርጉት ግብግብ በጊዜ መፍሄ ካልተበጀለት አሳሳቢ መሆኑን ይጠቁማሉ። በተቃዋሚዎቹ እና በጦር ሰራዊቱ መካከል ከተፈጠረው ፍጥጫ ይልቅ ከአልበሽር ስልጣን መልቀቅ በኋላ ለሱዳን አስጊ እንደሆነ ተፈርቶ የነበረው በሀገሪቱ ባሉት የተለያዩ የጸጥታ ተቋማት መካከል ሊኖር ይችላል ተብሎ የተሰጋው “የእርስ በእርስ ሽኩቻ” ነበር።  የኢትዮጵያንም ሆነ የሱዳንን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት ብሪታንያዊው የፖለቲካ ተንታኝ አሌክስ ደ ዋል በቅርቡ ባሳተሟቸው ጽሁፎችም ለዚህ ጉዳይ አጽንኦት ሰጥተዋል።  

በሱዳን ወታደራዊ መሪዎች ከስልጣናቸው በተወገዱበት በጎርጎሮሳዊው1964 እና 1985 ህዝባዊ አመጾች ወቅት “በሀገሪቱ ወሳኝ ኃይል የነበረው ጦር ሰራዊቱ እንደነበር” የሚያስታውሱት አሌክስ ደ ዋል አሁን ጉዳዩ ሌላ መልክ እንደያዘ መረጃ እያጣቀሱ ይሞግታሉ። የሀገሪቱ የብሔራዊ የደህንነት እና የጸጥታ አገልግሎት የሚመራው ኃይል በተለይ በመዲናዋ ካርቱም በኃይለኛነቱ የሚነሳ እንደሆነ ይገልጻሉ። 

ቀደም ሲል በዳርፉር ተሰማርቶ የነበረው የነበረው የሚሊሺያ ኃይል አሁን “ፈጥኖ ደራሽ የድጋፍ ኃይል” በሚል እንደሚንቀሳቀስ ያስረዳሉ። ከእነዚህ ኃይሎች ጎን “የማዕከላዊ ተጠባባቂ ፖሊስ” የሚባል ኃይል እና የሱዳን ገዢ ፓርቲ “እስላማዊ ታጣቂ ቡድን” እንዳለም ያብራራሉ። እነዚህ ኃይሎች በሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ኳታር እንደሚደገፉ የሚገልጹት የፖለቲካ ተንታኙ ሁሉንም እንደ የጸባያቸው አቻችለው መምራት የቻሉት ፕሬዝዳንት አልበሽር ብቻ እንደነበሩ ያሰምሩበታል። ዶ/ር ሰለሞንም በዚህ ትንታኔ ይስማማሉ። 

በአልበሽር የመጨረሻ የስልጣን ቀናት በደህንነት ኃይሎች እና በጦር ሰራዊቱ መካከል፤ በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ እና አለመውሰድ ላይ አለመግባባት ተፈጥሮ እስከመታኮስ መዳረሳቸው የተነገረ ቢሆንም፤ ከዚያ በኋላ የጎላ ችግር ባለመከሰቱ ስጋቱ የቀነሰ መስሎ ነበር። ስልጣኑን የተረከበው ወታደራዊ ምክር ቤት ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸውን እስላማዊ ሚሊሺያዎች “ተቆጣጥሯል”መባሉም ስጋቱን አርግቦታል። 

በተለያዩት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ለጊዜውም ቢሆን ስምምነት ያለ ቢመስልም በጦር ሰራዊቱ ውስጥ ግን አሁንም አለመረጋጋቶች እንዳሉ ይነገራል። ለዚህም ይመስላል ከአልበሽር ስልጣን መነሳት በኋላ በመሪነት ብቅ ያሉት የሱዳኑ መከላከያ ሚኒስትር ስልጣናቸውን ከአንድ ቀን በኋላ ሳይጠበቅ ትላንት ምሽት ያስረከቡት። መከላከያ ሚኒስትሩን ሌፍተናት ጄነራል አዋድ ሞሃመድ ኢብን አውፍን የተኳቸው በተመሳሳይ ወታደራዊ የማዕረግ ደረጃ ያሉት አብደልፈታህ አልቡህራን ናቸው። ሹም ሽሩ ቀጥሎ ዛሬ ደግሞ የብሔራዊ የደህንነት እና የጸጥታ አገልግሎት ላፊው ኃላፊው ሳላህ አብደላ ጎሽ ስልጣናቸውን ለቅቀዋል።

 የሱዳንን መጻኢሁኔታ አቅጣጫ ለማስያዝ ዛሬን ጨምሮ ቀጣዩቹ ቀናት ወሳኝ መሆናቸውን የፖለቲካ ተንታኞች ያሳስባሉ። በሀገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ በፍጥነት በሚለዋወጥበት በዚህ ወቅት ከሱዳን ጋር ወደ 1600 ኪሎ ሜትር ገደማ ድንበር የምትዋሰነው ኢትዮጵያ ጉዳዩን የያዘችበትን መንገድ መጠየቅ የአባት ነው። ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቷ በኩል ባለፈው ሐሙስ ምሽት ካወጣችው አጭር መግለጫ ውጭ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራራያ አልሰጠችም። 

ኢትዮጵያ “በሱዳን እየተካሄደ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለች” መሆኑን የጠቀሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ “ሱዳናውያን አሁን ያሉበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በብቃት እንደሚወጡት ኢትዮጵያኑ ጽኑ እምነት አላት” ብሏል። ሀገሪቱ “የሱዳናውያን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ የምታከብር” መሆኗንም ጠቁሟል። የሱዳን ቀውስ ለኢትዮጵያ ያለውን አንደምታ እና የኢትዮጵያን “ቁጥብ አካሄድ” በተመለከተ የተጠየቁት የአማኒ አፍሪካው ዶ/ር ሰለሞን ምላሽ ሰጥተዋል። 

ሙሉ መሰናዶውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

Audios and videos on the topic