ቅኝ አገዛዝ በቅኝ ገዢዎች አይን | የጋዜጦች አምድ | DW | 06.07.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ቅኝ አገዛዝ በቅኝ ገዢዎች አይን

ፈረንሳይና ሌሎች የአዉሮፓ አገሮች ባለስልጣኖቻቸዉንና የታሪክ ምሁራኖቻቸዉን በመጠቀም ቅኝ አገዛዝ ጥሩ ነገር እንደነበር ማስረገጥ ጀምረዋል። በተለይ በፈረንሳይ ፓርላማ ይህን የሚያፀድቅ ህግ በመዉጣቱ በቀድሞ ቅኝ ተገዢዎቿና በአንዳንድ ምሁራን አካባቢ ቅሬታ አሳድሯል።

በተለይ አልጀሪያ በቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ በአገሪቱ ህዝብ ላይ የተፈፀመዉን በማዉሳት በግንባር ቀደምነት ህጉን ተቃዉማለች። የፈረንሳይ ምሁራንም ህጉ ምንም የሚያመጣዉ የታሪክ ለዉጥ እንደማይኖር እየገለፁ ነዉ።
ባለፈዉ የካቲት ወር መጨረሻ ገደማ በአብላጫዉ የፕሬዝደንት ዣክ ሺራክ ፓርቲ በሚገኝበት የፈረንሳይ ፓርላማ የወጣዉ ህግ በአገሪቱ የሚገኙ መምህራንና የመማሪያ መፃህፍት በተለይ በሰሜን አፍሪካ ፈረንሳይ የተጫወተችዉን ገንቢ ሚና በአፅንዖት እንዲገልፁ ያዛል።
ይህም ማለት ፈረንሳይ በቅኝ ገዢነት በቆየችባቸዉ አገራት ሁሉ አገዛዝዋ መልካም እንደነበረ በማሳየት ቅኝ አገዛዝ ገንቢ ተግባር መፈፀሙን የሚሰብክ ነዉ።
ይህ እርምጃም በፈረንሳይ የታሪክ ምሁራን፤ በፓለቲካ ሰዎች፤ በመምህራንና በፈረንሳይ ቅኝ የተዙ አገራት ተወካዮች በተለይም በአልጀሪያ ሰዎች መካከል ክርክር ፈጥሯል።
በመጀመሪያ የአልጀሪያ መንግስት በፓርላማዉ የሚገኙ ሁለቱን ክንፎች ለልዩ ስብሰባ በመጥራት ፈረንሳይ ባወጣችዉ ህግ ዙሪያ ተወያይተዉ ምላሽ ለመስጠት ፈልጎ ነበር።
ሆኖም ፕሬዝደንት አብደልአዚዝ ቡቶፍሊካ የጋራና ልዩ ስብሰባዉን ወደ ጎን በማስቀረት ሁለቱም በጉዳዩ ላይ በየግል ተወያይተዉ በቅኝ ገዢዎች የተፈፀመዉን ወንጀል የሚያወግዝ የጋራ አቋም እንዲያወጡ አድርገዋል።
ሁኔታዉም አልጀሪያ ከቀድሞ ቅኝ ገዢዎቿ ጋር ጤናማ ግንኙነት ለመመስረት በምትጥርበት ወቅት በፈረንሳይ ለወጣዉ ህግ የተሰጠዉ ምላሽ ቅኝ ገዢዎች የፈፀሙት ቁስል ገና ያልሻረ መሆኑን እንደሚያመላክት ተጠቅሷል።
በፈረንሳይ በኩል የቅኝ አገዛዝን በጎነት የሚያጠይቅ ህግ እንደወጣ ወዲያዉ ነበር የአልጀሪያ ገዢ ፓርቲና አገሪቱን ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለማዉጣት የተንቀሳቀሰዉ ብሄራዊ የነፃነት ግንባር በእንግሊዝኛ ምህፃረ ቃሉ FLN ህጉን የሚያወግዝ መግለጫ ያወጣዉ።
የፈረንሳይ ህግ ይላል FLN ቅኝ አገዛዝን የሚያሞካሽና የታሪኩን ጎጂ ገፅታ የሚሸፍን ነዉ። በዚያም ላይ ቅኝ ገዢዉ የፈረንሳይ ኃይል በአልጀሪያ የፈፀመዉን ዘግናኝ ድርጊት ሁሉ ጨርሶ ሊደብቅ የሞከረ ነዉ።
ፓርቲዉ ያወጣዉ መግለጫም በዉጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብደልአዚዝ ቤልካህደም የተፈረመ ነዉ። ቤልካህደም የቡቶፍሊካ የቅርብ አማካሪ መሆናቸዉ የሚነገር ሲሆን የፓርቲዉ የክብር ፕሬዝደንት ናቸዉ።
መግለጫዉ ጨምሮ እንደጠቀሰዉ በነፃነት ታጋዮች ላይ የደረሰዉን በደል ለማድበስበስ የሞከረዉ ቅኝ አገዛዝን ለመደገፍ የወጣዉ የፈረንሳይ ህግ ሲታይ የናዚ ጀርመንን ታሪክ እንደገና ለመፃፍ መሞከር አይነት ነዉ ባይ ነዉ።
በአልጀሪያ የቅኝ ተገዢነት ታሪክ ዉስጥ ባሺር ቡማዛ በ1940ዎቹ የነፃን የትግል ዘመን ከፈረንሳይ ኃይል ጋር ሲታገሉ ከፍተኛ ስቃይ የተፈፀመባቸዉ የአልጀሪያ የነፃነት ታጋይ ነበሩ።
ቡማዛ ዘ ጋንግሪን በተሰኘዉ መፅሃፋቸዉም በፈረንሳይ የቅኝ ገዢ ኃይሎች የተፈፀመባቸዉ የማስቃየት ስልት እንዴት ያለ እንደነበር ገልፀዋል።
በእኝህ ታጋይና በሌሎችም የነፃነት አርበኞች ላይ ይህን መሰሉን ተግባር የፈፀሙት ቅኝ ገዢዎች ታሪክ በዓለም ተወግዞ ሳለ ዉዳሴ መጀመሩ በቅኝ ገዢዎችና ተገዢዎች መካከል ታሪካዊ ቅያሜዉን ከማርገብ ይልቅ እንዳዲስ እንዲያገረሽ ያደርገዋል ይላል።
በዚያም ላይ ቅኝ አገዛዝ የሰዉ ዘርን የሚያዋርድ ተግባር ነዉ የሚሉት ቡማዛ የሚያሳዝነዉ ፈረንሳይ አሁንም የቅኝ ገዢነት አስተሳሰቧን አልለወጠችም ይላሉ።
አልጀሪያ ለስምንት ዓመታት ከተካሄደ ከፍተኛ ደም መፋሰስና በፈረንሳይ ጦር የወረደባት የጭካኔ በትር በፀጋ ተቀብላ ነዉ በ1954ዓ.ም ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ነፃ የወጣችዉ።
በወቅቱም ፈላስፋዉ ዣን ፓል ሳርቴርንና የታሪክ አዋቂዉን ፒየር ቪዳል ናኩዌስን ጨምሮ በጣት የሚቆጠሩ የፈረንሳይ ምሁራን ናቸዉ ፈረንሳይ በአልጀሪያ የፈፀመችዉን ጥቃት የተቃወሙት።
የፈረንሳይ የታሪክ መምህራንና ምሁራን እንደሚሉት አዲሱ የፈረንሳይ ህግ በታሪክ የታወቀዉን ዕዉነታ ለማፅዳት የሞከረዉ ሁሉ የሚያመጣዉ ለዉጥ አይኖርም ባይ ናቸዉ።
ምንም እንኳን በሌላ ወገን ብሪታንያ በቅኝ ግዛትነት ይዛቸዉ የነበረዉ አገራት ወደየጋራ ብልፅግናዉ ህብረት በሳላማዊ መልክ ቢሸጋገሩም ህንድ፤ ኬንያና ዚምባቡዌ የነበራቸዉ ታሪክ ለየት ያለ ነዉ።
እናም ይላሉ እነዚህ ወገኖች ዝም ብለን ታሪክን ለታሪክ ትተን ለሰላማዊ ግንኙነት ብንጥርም በቅኝ ገዢዎች የተፈፀመዉ አስከፊ ተግባር የሚዘነጋ አይደለም።