ቃለ ምልልስ ከኮሎኔል እያሱ አንጋሱ እና ስዩም ተሾመ ጋር | ኢትዮጵያ | DW | 16.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ቃለ ምልልስ ከኮሎኔል እያሱ አንጋሱ እና ስዩም ተሾመ ጋር

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፋችኋል በሚል ታስረው ከነበሩ ግለሰቦች መካከል በአሮሚያ ክልል የአድማ በታኝ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል እያሱ አንጋሱ፣ የክልሉ የፍትህ ቢሮ የኮሙዩኒኬሼን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታዬ ዳንዳኣና በአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህርና ጦማሪ አቶ ስዩም ተሾመ ዛሬ ከእስር ተፈትተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:15

ቃለ ምልልስ ከኮሎኔል እያሱ አንጋሱ እና ጦማሪ ስዩም ተሾመ ጋር

በአሮሚያ ክልል የአድማ በታኝ ፖሊስ ምክትል አዛዥ ኮሎኔል እያሱ አንጋሱ የቀረበባቸውን ክስ አለመፈጸማቸውን የሚገልጽ ሰነድ ፈርመው ከእስር መለቀቃቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ከኢትዮጵያ መንግሥት ወገን ስለተለቀቁበት ሁኔታ ምንም የተነገራቸው ነገር አለመኖሩን የገለጹት ኮሎኔል እያሱ "የክልሌም ሆነ የኮሚሽኑ አባላት እና አመራሮች ከእኔ አልተለዩም። የወጣሁት በእነሱ ጥረት እና በእነሱ ብርታት ነው" ሲሉ አስረድተዋል። ኮሎኔል እያሱ በሙሉ የመተማመን መንፈስ ወደ ሥራቸው እንደሚመለሱ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። 

ሕዝብን በማነሳሳት ተጠርጥረው የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በሐረር ከተማ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ያስታወሱት ኮሎኔል እያሱ በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ ይጠራ በነበረው የፌድራል ፖሊስ የምርመራ ቢሮ መታሰራቸውን ተናግረዋል። ኮሎኔሉ እንዳሉት በሐረር ከተማ በቁጥጥር ሥር የዋሉት "ከመንግሥት የተሰጠኝን ተልዕኮ ይዤ ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የተለያዩ ቢሮዎች ጋር የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ መሐል አገር ለማምጣት" በተጓዙበት ወቅት ነው። 

"ኹከት እና ብጥብጥ ሲመሩ ነበር፤ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ብሔር እና ብሔር እንዲጋጭ አድርገዋል" የሚል ክስ ያቀረቡባቸው መርማሪዎች ፍርድ ቤት አቅርበው ጉዳዩን ለማጣራት ተጨማሪ 14 ቀናት መጠየቃቸውን ኮሎኔሉ አስረድተዋል። ፍርድ ቤት የቀረበለት ጥያቄ ተቀብሎ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። ኮሎኔል እያሱ "እናንተ መደበኛ ፍርድ ቤት አትቀርቡም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፍርድ ቤት እስኪቋቋም ትቀመጣላችሁ" የሚል ምክንያት ተሰጥቷቸው እስከ ዛሬ ሚያዝያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በእስር ላይ መቆየታቸውን አስረድተዋል። 

ስቅየት ይፈጸምበታል ይባል በነበረው ማዕከላዊ የምርመራ ቢሮ በቆዩበት ወቅት የደረሰባቸው ነገር አለመኖሩን የተናገሩት ኮሎኔሉ "ጊዜ እና ወቅቱ የሚፈቅድም አይመስለኝም። አሁን ያለው ሁኔታ ለዛ ዕድል የሚሰጥ አይመስለኝም" ሲሉ አክለዋል። መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ከጊዮርጊስ አደባባይ ከፍ ብሎ የሚገኘው ማዕከላዊ የምርመራ ቢሮ ሲዘጋ በተዘዋወሩበት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን "ያለው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ ነው። እዛ የሚታሰር ሰው የሚደረገው አደጋዎች አሉ። በበሽታ ካልሆነ በስተቀር እኛ ላይ አልደረሰም" ሲሉ የታዘቡትን ገልጸዋል። 

ዛሬ ከእስር የተለቀቁት የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር፣ የአምደ-መረብ ጸሀፊ እና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ ስዩም ተሾመ ወሊሶ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በጸጥታ ኃይሎች ተወስደው የታሰሩት በየካቲት 29 ቀን 2010 ዓ ም ነው። አቶ ስዩም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰዋል በሚል መታሰራቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በተመሳሳይ መዝገብ ተከሰው የታሰሩ ሌሎች እስረኞች ቢኖሩም ዛሬ ከእርሳቸው ጋር የተለቀቁት ኮሎኔል እያሱ እና አቶ አቶ ታዬ ብቻ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

አቶ ስዩም ኢትዮ ቲንክ ታንክ በተሰኘው ድረገጻቸው በሚጽፏቸው አስተያየቶች እና በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በሚሰጧቸው የፖለቲካ ትንተናዎች ይታወቃሉ። ባለፈው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ለሶስት ወራት ገደማ ታስረው መፈታታቸው ይታወሳል። 

ሙሉ ቃለ ምልልሱን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ። 

ተስፋለም ወልደየስ 

ነጋሽ መሐመድ 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች