ቀጠር የቀረቡላት ጥያቄዎች | ዓለም | DW | 29.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ቀጠር የቀረቡላት ጥያቄዎች

ሳውዲ አረብያ እና አጋሮቿ በአልጀዚራ ዘገባዎች ላይ የሙስሊም ወንድማማቾች ማህበር ተወካዮች በየጊዜው መቅረረባቸውን አይደግፉም። ስለ አረቡ ዓለም አብዮት የሚቀርቡ ዝግጅቶችም የአብዮቱን ጥሩነት የሚያጎሉ እና በግልጽ ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው ሲሉ ይቃወማሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:36

የቀጠር እና ጎረቤቶቿ ውዝግብ

ሳውዲ አረብያ እና አጋሮቿ  ከቀጠር ጋር የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት ያስችላል ያሉትን  ባለ አሥራ ሶስት ነጥብ ጥያቄ ለዶሀ ካቀረቡ አንድ ሳምንት አልፏል። ቀጠር ግን እነዚህን ጥያቄዎች ለማሟላት የምትችል አይመስልም። 
ከቀጠር ጋር ማናቸውንም ግንኙነት ያቋረጡት ሳውዲ አረብያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፣ግብፅ እና ባህሬይን  ከቀጠር ጋር የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት ያስችላሉ ያሏቸውን ባለ 13 ጥያቄዎች ቢያቀርቡም እስካሁን ከቀጠር በኩል የተሰማ ዝርዝር ነገር የለም። ይሁን እና ዩናይትድ ስቴትስ ወደ  መፍትሄ የሚያመራ ውይይት ለማካሄድ መሠረት የሆኑ ጉዳዮች መነሳታቸውን በበጎ ተመልክታዋለች። በርግጥ ለቀጠር የቀረበው ዝርዝር ጥያቄ ለመሪዎቿ ራስ ምታት መሆኑ አይቀርም። ትንሽትዋ ቀጠር ከጎረቤቶችዋ ጋር ሰለማዊ ግንኙነት እንዲኖራት የቀረቡላትን ባለ 13 ነጥብ ጥያቄዎች ማሟላት ይኖርባታል። ሳውዲ አረብያ እና አጋሮቿ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ቀጠር ከኢራን ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን መቀነስ እንዲሁም የኢራን ጦር ኃያል አካል የሆነውን የኢራን አብዮታዊ ዘብ  አባላት ማስወጣት አለባት። ከኢራን ጋር የጋራ ወታደራዊ ወይም የስለላ ትብብሮችንም እንድታቆም እና በአሁኑ ጊዜ በግንባታ ላይ የሚገኙ የቱርክ ወታደራዊ

የጦር ሰፈሮችንም እንድትዘጋ እና በአጠቃላይ ከቱርክ ጋር ያላትን ወታደራዊ ትብብር በሙሉ እንድታቆም ተጠይቃለች። ከዚህ ሌላ ዶሀ ለብዙዎቹ የዓረብ ሀገራት የዓይን እሾህ የሆነባቸውን ዓለም አቀፉን የቴሌቪዥን ጣቢያ አልጀዚራን እንድትዘጋም ጥያቄ ቀርቦላታል። ሳውዲ አረብያ እና አጋሮቿ በአልጀዚራ ዘገባዎች ላይ የሙስሊም ወንድማማቾች ማህበር ተወካዮች በየጊዜው መቅረረባቸውን አይደግፉም። ስለ አረቡ ዓለም አብዮት የሚቀርቡ ዝግጅቶችም የአብዮቱን ጥሩነት የሚያጎሉ እና በግልጽ ድጋፍ የሚሰጡ ናቸው ሲሉ ይቃወማሉ። ሀገራቱ ለቀጠር ያቀረቡት ዝርዝር ይህ ብቻ አይደለም። ቀጠር አሸባሪ ከሚባሉት ከአልቃይዳ ወይም  ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ከሚጠራው ድርጅት ፣ሳውዲ አረብያ እና አጋሮቿ እንዲሁም ግብጽ አሸባሪ ከሚሏቸው ከሊባኖሱ ሄዝቦላም ሆነ ከግብጹ የሙስሊም ወንድማማቾች ማህበር ጋር ግንኙነት ማቋረጥ ይኖርባታል።በስም የተዘረዘሩ አሸባሪ የተባሉ ሰዎችን አሳልፋ እንድትሰጥ እና ከአራቱ አረብ ሀገራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ያላትን ግንኑነቶች እንድታቋርጥም ተጠይቃለች። በጀርመን የውጭ ጉዳዮች ማህበር የመካከለኛው ምሥራቅ የፖለቲካ ጉዳዮች አጭኚ ሴባሳትያን ዞንስ እንደሚሉት የቀጠር የፖለቲካ አካሄድ ከሳውዲ አረብያ የተለየ ነው።
«ቀጠር በአካባቢው ከሚገኙ የአረብ ሀገራት በተለየ  ራስዋን ከሁሉም ጋር መነጋገር የምትችል ተዋናይ አድርጋ ነው ለማቅረብ የምትሞክረው። ከሳውዲ አረብያ በተለየ ለምሳሌ በጣም ግልጽ ናት፤ ሰላም ማምጣት ውይይት ማካሄድ ትፈልጋለች። ይህ ደግሞ ከሃማስም ከታሊባንም ጋር ተግባራዊ የምታደርገው ነው። እነዚህን ቡድኖች ማግለል ትርጉም አይሰጥም ይላሉ። ግጭቶችን ለማስወገድ ከሰዎች ጋር መነጋገር ይፈልጋሉ። እነዚህ ቡድኖች አክራሪ እንዳይሆኑ መከላከል ነው የሚፈልጉት።»

ኢራን ለሳውዲ አረብያ  በአካባቢው ዋነኛ የፖለቲካ እና የሃይማኖት ተጻጻሪ ናት። ሁለቱ ሀገሮች በየመን እና በሶሪያ የውክልና ጦርነት ያካሂዳሉ። የሁለቱም ዓላማ በአካባቢው ኅያላቸውን ማጠናከር ነው። በዚህ ፉክክር ኢራን አሁን ቀዳሚውን ቦታ ይዛለች። ኢራን አብዮታዊ ዘቧ በኢራቅ እና በሶሪያ እንዲሁም እሥራኤል ድንበር ድረስ በሚንቀሳቀሰው የገንዘብ ድጋፍ በምታደርግለት እና በመሰረተችውም በሌባኖሱ ሄዝቦላ ላይ ተጽእኖዋን አጠናክራለች። ከምንም በላይ ሳውዲ አረብያ እና አጋሮቿ፣ ዶሀ ከኢራን ጋር ያላት የቅርብ ግንኙነት ያበሳጫቸዋል። በኤኮኖሚው ረገድ በፋርስ ባህረ ሰላጤ በጋራ የሚያካሂዷቸው የነዳጅ ዘይት ሥራዎች እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን አይወዱትም። ቀጠር ከሙስሊም ወንድማማቾች ማህበር ጋር ረዥም ጊዜ የዘለቀ ቅርብ ግንኙነት አላት። ቡድኑ በጎርጎሮሳዊው 2012ቱ የግብጽ ምርጫ ብዙ ድምጽ ሲያገኝ ቀጠር ከካይሮ ጋር ፖለቲካዊ ግንኙነትዋን ለማጠናከር ሞክራ ነበር። በ2013 ቡድኑ ሲወድቅ ጥረቱ ቆመ። የሳውዲ መንግሥት የሙስሊም ወንድማማቾች ማህበር ለአረብ ባህረ ሰላጤ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ስርዓት አደጋ አድርጎ ነው የሚያየው። በዚህ የተነሳም ቀጠር አሁን የተጠየቀችውን ሁሉ ማሟላት አስቸጋሪ ነው የሚሆንባት ይላሉ ዞንስ። ያምሆኖ ግን 
«ቀጠር ራስዋን ከኢራን ልታገል ትችል ይሆናል። ወይም ደግሞ ከአረብ ወንድሞቿ ጋር ጋር እንደ እስካሁኑ ጥሩውን ግንኙነት አጠናክራ ልትቀጥልም ትፈልግ ይሆናል። ከጥቂት ቀናት በፊት የቀጠር አምባሳደር በርሊን ውስጥ ቀጠሮች እና ሳውዲዎች በመሠረቱ አንድ ቤተሰብ ናቸው ብለው ነበር። በዚህ ውዝግብ ውስጥ የሚካፈሉት ወገኖች ገጽታቸውን ሳያበላሹ ከዚህ ውዝግብ የሚላቀቁበትን መንገድ ነው የሚፈልጉት። በዛም ሆነ በዚህ ግን ቀጠር የተጠየቀችውን ታሟላላቸው ብዮ አላስብም።» 

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic