ቀጠር ሚና አረብና አፍሪቃ | ዓለም | DW | 30.01.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ቀጠር ሚና አረብና አፍሪቃ

ድልብ ሐብቷ፣ ከትልቅ መወዳጀትዋ ትልቅ-አስመስሏት በተለይ ከ1995 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ወዲሕ የሌለችበት ግጭት-ዉዝግብ የለም።ቀጠር

default

አሚሩ


ዶሐ የሚታተመዉ የአል-ዓአረብ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አብዱል አዚዝ አል ማሕሙዳ «ድሮ ቀጠርን የሚያዉቅ ብዙም አልነበረም።»አለ «አሁን ግን» ቀጠለ «ከቀጠር ነኝ በል፥ ማንም ያዉቅሐል።»በቆዳ ሥፋቷ፣ በሕዝብ ብዛቷ፣ በጦር አቅሟም-የትንሾች ትንሽ ናት።ግን ሐብታም እና የሐያላን ወዳጅ። ድልብ ሐብቷ፣ ከትልቅ መወዳጀትዋ ትልቅ-አስመስሏት በተለይ ከ1995 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎሮጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ወዲሕ የሌለችበት ግጭት-ዉዝግብ የለም።ቀጠር።የትንሺቱ ሐገር ትልቅ እርምጃ፥ የሒደት ዉጤቱ እንዴትነት ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።


የቀጠር ገዢዎች የሰሞኑ አብይ ትኩረት ሶሪያ ናት።«የሶሪያ ሁኔታ በዚሕ ከቀጠለ፥ ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ዉጪ ይሆናል ብለን እኛ አረቦች እንሰጋለን።»የቀጠር ጠቅላይና ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሐማድ ቢን ጃስሚን ቢን ጀባር አ-ሳኒ።የሶሪያ ሁኔታ ባለበት እንዳይቀጥል፥ የዶሐ መሪዎች የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት የዉጪ ሐይል ጣልቃ እንዲገባ የሚፈቀድ ዉሳኔ ማሳለፍ አለበት ባይ ናቸዉ።እርግጥ ነዉ ሐሳቡ የዋሽንግተን፥ ለንደን፥ ብራስልሶች በጣሙን የዋሽግተን መሪዎች ነዉ።

ሞስኮዎች በተደጋጋሚ ቢቃወሙትም ምዕራባዉያን ሐገራት የፕሬዝዳት በሽር-አል አሰድን መንግሥት የሚያስወግድ፥ ወይም ለማስወገድ የሚረዳ ረቂቅ-ዉሳኔ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ለማቅረብ ሞክረዋልም።ሐሳቡ የምዕራባዉያን በመሆኑ ከአማን እስከ ኩዌይት፥ ከማናማ እስከ ሪያድ፥ ከራባት እስከ ሙስካት ያሉ የምዕራባዉያን የቅርብ ወዳጆች አረብ ሐገራት መደገፋቸዉ አልቀረም።

Karte der Straße von Hormus welche die Verbindung zwischen dem Golf von Oman und dem Persischen Golf darstellt. Durchschnittliche Leistung 2011: 17 Millionen Barrel Öl täglich Entspricht: 35% des Seehandels mit Öl 20% des weltweiten Ölhandels DW-Grafik: Peter Steinmetz

ቀጠርግን ማን እንደ ዶሖ።እንደገና ቢን ጃስሚን

«የምንሰራዉ ሥራ በሙሉ ጣልቃ ገብነትን ለማስወገድ ነዉ።ይሁንና ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ይሕን አቋማችንን በቅጡ ተረድቶ ዉጤት ካላመጣ ጣልቃ-ገብነት እንደማይኖር ዋስትና ለመስጠት አልችልም።»በዉርስ፥ በዘር፥ በቤተ-መንግሥት ደባ፥ የየሐገሩን ፖለቲካዊ-ሥልጣን የሚፈራረቁበት፥ ሐቡቱን በዉልድ-በዘመድ-አዝማድ፥ በአምቻ-ጋብቻ የሚቆጣጠሩት፥የየሐገሩን የደለብ ሐብት የሚመዘብሩት ነገስታት ሕዝባዊ አመፅን ደጋፊ፥ አምባገነኖችን ተቃዋሚ መምሰላቸዉ በርግጥ ብዙ አነጋጋሪ፥ ግራ አጋቢም ነዉ።

የነገስታቱ የጋራ-ፍላጎት አላማ አነጋገረም-ግራ አጋባ፥-ቀጠር የአረብን ፖለቲካ ከሾፌሩ ወንበር ተቀምጣ መዘወሯ ብዙ አላጠያየቅም።ትንሽ-ልሳነ ምድር ናት።የቆዳ ስፋትዋ፥ አስራ-ሁለት ሺሕ ስኩዌር ኪሎ ሜትር አይሞላም።አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ከሚገመተዉ ነዋሪዋ አንጡሯ ዜጎችዋ ሰወስት መቶ ሺሕ አይደርሱም።ከምድር በታች የተነጠፈዉ የጋዝ ሐብቷ-ግን ከመላ ሐገሪቱ የቆዳ ስፋት እኩል ሊሆን ትንሽ ነዉ-የሚቀረዉ።የነዳጅ ዘይት ክምችቷ ደግሞ አስራ-አምስት ቢሊዮን በርሚል ይገመታል።


የቆዳ-ስፋትዋ፥ የሕዝብ ብዛዛትዋ፥ትንሽነት ወይም በተቃራኒዉ የነዳጅ-ጋስ ሐብቷ ትልቅነት የዛሬ-ወይም የትናንት እዉነት አይደለም።ጋዜጠኛ አብድል አዚዝ አልማሕሙዳ እንዳለዉ ትንሺቱ ልሳነ-ምድር የታወቀችዉ ግን በቅርቡ ነዉ።ኢትዮጵያዊዉ የምሥራቅ አፍሪቃና የመካከለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ ጉዳይ ተንታኝ ዩሱፍ ያሲን እንዳሉት ትንሺቱ ሐገር ትልቅ ያደረጓት ወይም የሚያስመስሏት ካሁኑም ከድሮዉም የተቀየጡ አራት ነገሮች ናቸዉ።


አሚሩ፥-የአንድ ሐገር አልጋወራሽ ንጉስ አባቱን በመፈንቅለ መንግሥት የማስወገድ ወይም፣ አባት በልጁ የተቀማዉን ዙፋን ለማስመለስ አፀፋ-መፈንቅለ መንግሥት የመሞከር አስደናቂ ድራማ በቅርቡ የዓለም ታሪክ ለዓለም ያሳዩት የአሳኒ ቤተሰቦች ናቸዉ።በ1995ቱ የልጅ-አባት መፈንቅለ መንግሥት፥ አፀፋ መፈንቅለ መንግሥት ድራማ ሰበብ በአለም የናኘ ስሟ በዚዉ ግመት እንዲቀጥል ለማድረግ አዲሱ አሚር ጊዜ አላጠፉም።

የአባታቸዉን ዙፋን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸዉን ባረጋገጡ በመንፈቁ አል-ጀዚራ የተሰኘዉን አለም አቀፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ የአረቢኛ ሥርጭት አስጀመሩ።1996።ከዚያ በፊት የብሪታንያዉ ማሰራጪያ ጣቢያ ቢቢሲን ያክል በአረቡ አለም የሚታወቅ የአረብኛ ቴሌቪዥን ጣቢያ አልነበረም።ለቢቢሲ የአረብኛ ስርጭት ጠቀም ያላዉን ገንዘብ ይከፍሉ የነበሩት የከስዑዲ አረቢያዉ ንጉስ ፈሕድ ያጎት ልጅ ልዑል ኸሊፋ ክፍያዉን በማቆማቸዉ ቢቢሲ ስርጭቱን ሲያቋረጥ ሁለት መቶ ከሚደርሱ ጋዜጠኞቹ አብዛኞቹን አል-ጀዚሪያ «አሕለን-ወሳሕለን» አላቸዉ።

A Qatari employee of Al Jazeera Arabic language TV news channel passes by the logo of Al Jazeera in Doha, Qatar, Wednesday Nov. 1, 2006. The English language offshoot of Qatar based pan-Arab television news channel Al Jazeera said on Tuesday it will start broadcasting on November 15, 2006. (AP Photo/Kamran Jebreili)

አል ጀዚራ

አሚሩ ቀጠሉ።በመጀመሪያዉ የባሕረ-ሠላጤዉ ጦርነት ወቅት ኢራቅን ለመወጋት ቀጠር የሠፈረዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በቋሚነት እዚያዉ እንዲቆይ አዲሱ አሚር የዩናይትድ ስቴት ጠየቁ። ጥያቄዉ ለያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ለቢል ክሊንተን መስተዳድር የምሥራች፥የአሜሪካ ጦር በግዛታቸዉ በማስፈራቸዉ ከፍተኛ ተቃዉሞ ለገጠማቸዉ ለሪያድ ነገስታት እፎይታ ነበር።

የዚያኑ ያክል የትንሺቱ ሐገር የትላልቅ ጎረቤቶችዋን ነባር ሥፍራ እተየካች በትላልቆቹ የዓለም ዘዋሪዎች እቅፍ «ጠበቅ» የመደረጓ ጅምር።ዩናይትድ ስቴትስ በአሸባሪዎች በተመታች ማግሥት ጦሯን አፍቃኒስታን ሥታዘምት፥ዶሐ-አጠገብ አል-ሳሊያሕ የሚገኘዉ የጦር ሠፈሯ አፍቃኒስታንን ለሚደድቡ የጦር አዉሮፕላኖች መነሻና ማረፊያ ነበር-ነዉም።

አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት የቀጠር ግዛት ባለቤት፥የቅምጥ ሐብቷ ተጠቃሚም ሕዝቧ ነዉ ማለት ያሳስታል።


በሁለት ሺሕ ሁለት ዩናይትድ ስቴትስ ኢራቅን ለመዉረር ስትዘጋጅ አሚር ሐማድ ቢን ኸሊፋ አል-ሳኒ በአንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ አል-ኡዳይድ በተባለዉ አካባቢ ልዩ የጦር ሠፈር አስገንብተዉ ለአሜሪካ አየር ሐይል አስረከቡ።የአል-ጀዚሪያ ቴሌቪዥን ጣቢያን በአንድ መቶ ሰላሳ-ሰባት ሚሊዮን ዶላር ያስከፈቱት አሜሩ ነበሩ።

አሜሪካን ለሚያክል ሐያል ሐብታም ሐገር ከትንሺቱ ሐገር ትንሽ ምድር ቀንሰዉ ትልቅ የጦር-ሠፈር፥ ከድልብ ሐብቷ ትንሽ ቦጭቀዉ የጦር ሠፈር ማስገንቢያ የሰጡትም አሚር ሐማድ ቢን ኸሊፋ አሳኒ ናቸዉ።የኢራቁ ጦርነት በጋመበት በ2003 አጋማሽ የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ኮሊን ፓዉል «አል-ጀዚራ በጎ ጥረታችንን በአሉታዊ መልኩ እያቀረበ ነዉ» በማለት ወቅሰዉ ነበር።አሜሩ ከሰጡት፥ ምድር፥ ካሰገነቡት ጦር ሠፈር የሚበሩ፥ ወይም የሚታዘዙት የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ጄቶችና ወታደሮች ኢራቅና አፍቃኒስታን ዉስጥ በአሜሩ ገንዘብ የተቋቋመዉን የአል-ጀዚራ ፅሕፈት ቤቶችን ደብድበዋል።ጋዜጠኞችን ገድለዋልም።አስረዋልም።

የዶሐ-ገዢዎች የማስታረቅ፥ተፅዕኖ የማሳረፍ ይሁን የዓለም ሐያላንን ትኩረት የመሳብ ሙከራ ሩጫቸዉ ኒዮርክ ታይምስ የተሰኘዉ የአሜሪካ ጋዜጣ በሁለት ሺሕ ስምንት እንደዘገበዉ አንዳዴ በተቃርኖ ያሳርጋል።ጁቡቲና ኤርትራን እናስታርቃለን-ሲሉ የአካባቢዉን ትልቅ ሐገር ምናልባትም የሁለቱ ትናንሽ ሐገራት ጠብ ምክንያት የሆነችዉን ኢትዮጵያን አግልለዉ ነበር።

ዶሐዎች ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በደረሰዉ በኤርትራና በጅቡቲ ዉዝግብ መሐል የገቡት የዳርፉር አማፂያንና የካርቱም መንግሥት ለማስታረቅ የጀመሩትን ሽምግልና አጠልጥለዉ ነበር። የጁቡቲ-ኤርትራ ሽምግልና ኢትዮጵያን አስኮርፎ፥ የዳርፉሩ ድርድር ገሚስ ላይ እንደተንጠለጠለ ሱዳን ለሁለት ልትገመስ ቀን ስታሰላ፥ ዶኸዎች የየመን አማፂያንና ከፕሬዝዳት ዓሊ አብደላ ሳሌሕ መንግሥት ጋር ለማስታረቅ ድርድር አስጀመሩ።


የየመን ተቀናቃኝ ሐይላት በሁለት ሺሕ ስምንት ተስማሙ ከመባሉ ባለፍ የስምምነቱ ገቢራዊነት ሳይታወቅ-የየመን ሕዝብ የፕሬዝዳት ዓሊ አብደላ ሳሌሕን አገዛዝ ለማስወገድ በአደባባይ ይሰለፍ ያዘ። እዚሕም ቀጠሮች ነበሩ።ዓሊ አብደላ ሳሌሕ ሥልጣን እንዲለቁ ግፊት ያደረገዉ የባሕረ-ሠላጤዉ አካባቢ ሐገራት ምክር ቤት የተመራዉ በቀጠር ነበር።

የባሕሬን ሕዝብ በረዥም ጊዜ ገዚዎቹ ላይ የቀሰቀሰዉን ሕዝባዊ አመፅ የሚደፈልቅ ጦር ከነስዑዲ አረቢያ ጋር ሆነዉ ለማዝመት ዶሐዎችን የቀደመ የለም።ከቤን ዓሊና ከሁስኒ ሙባረክ ጀርባ የነበረዉ ሐይል ማንነት ጠንቅቀዉ ስለሚያዉቁ ቤን-ዓሊ ሙባረክን ዶሐዎች በቀጥታ አልተጋፈጧቸዉም።

የቀድሞዉ የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊ የኤች.አ.ቪ ቫይረስ አሰራጭተዋል በማለት ሞት ያስፈረዱባቸዉን የምሥራቅ አዉሮጳ ነርሶች ለማስፈታት የሸመገሉት ዶሐዎች ነበሩ።ቃዛፊን ከስልጣን ላስወገዱ፥ ላስገደሉት ሐይላት ከቴሌቪዥን ሥርጭት እስከ ተዋጊ ጄት የረዱትም ዶሐዎች ናቸዉ።የዶሐና የትሪፖሊ ወዳጅነት እንዳጀማማሩ አልቀጠለም።የሊቢያን የሽግግር መንግሥት ሥልጣን ከያዙት ቡድናት አንዳዶቹ ቀጠረን እያወገዙ ነዉ።

በሁለት ሺሕ ስምንት የሊባኖስ የሱኒ፥ የሺዓ፥ የክርስቲያን ተቀናቃኝ ፖለቲከኞችን የአስራ-ስምንት ወራት ንትርክ ቁርቁስ አስወግደዉ ያስታረቁት ዶሐዎች ናቸዉ።የዚያኑ ሰሞኑ በሊባኖስ ጉዳይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ለምታሳርፈዉ ለሶሪያዉ ፕሬዝዳት ለበሽር አል-አሰድ የቀጠሩ አሜር ልዩ አየር ባስ አዉሮፕላን ሸልመዋቸዉ ነበር።ዛሬ ግን አሜር ሐማድ ቢን ኸሊፋ አ-ሳኒ የአሰድ ቀንደኛ ጠላት ናቸዉ።

ስዑዲ አረቢያ በሐይማኖት መፍለቂያነት፥ በቅዱስ ስፍራዎች አስተናጋጅነት፥ በቆዳ ስፋት፥በመልከዓ ምድር አቀማመጥ ከሁሉም በላይ ከርሰ ምድሯ በቋጠረዉ የነዳጅ ዘይት ሐይቅ-ስፋትና ጥልቀት ምክንያት የአረቦችን ፖለቲካ ብትዘዉር አይበዛባትም ባዮች ብዙ ናቸዉ።አሁን ግን የስዑዲ አረቢያ ይሁን በሕዝብ ብዛት፥ በጦር አቅም፥ በቴክኖሎጂም የምትሻለዉን የግብፅን ሚና ባብዛኛዉ ቀጠር ተቆጣጥራዋለች።ዶዎች ከዚሕ የደረሱት አቶ ዩሱፍ ያሲን እንደሚሉት በራሳቸዉ ፍላጎት ጥረት ብቻ አይደለም።

ቀጠር የምትዘዉረዉ የአረብ ፖለቲካ፥ የመከካለኛዉ ምሥራቅ የፖለቲካ ጉዳይ አዋቂ ፉዓዝ ጊርጊስ ባለፈዉ ሳምንት እሁድ እንዳሉት ደግሞ ልዩነቱ የአረብ ሊግን ከጋራ ማሕበርነት ይልቅ የሁለት ሐይላት መፋተጊያ አድርጎታል።«ዛሬ ያየነዉ በጣም የጎላዉ ነገር በአረብ ሊግ ዉስጥ ባሉ ሁለት ጥምረት በምላቸዉ ሐይላት መካካል ያለዉ ልዩነት መስፋቱን ነዉ።ባንድ በኩል በስዑዲ አረቢያ እና በቀጠር የሚመሩት የባሕረ-ሠላጤዉ መንግሥታት-የሶሪያ ጉዳይ ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መቅረብ አለበት-ይላሉ።በሌላ በኩል በግብፅ፣ በአልዤርና በኢራቅ የሚመሩት ለሶሪያ ጉዳይ አረባዊ መፍትሔ ይለግ ባዮች ናቸዉ።»

የፖለቲካ፥ምጣኔ ሐብታዊ፥ ሐይማኖታዊ፥ ሽኩቻ ከዓመት ዓመት የሚንጠዉ መካከለኛዉ ምሥራቅ የፍልስጤም እስራኤሎች ዉዝግብ በሕዝባዊ አመፅ አዳፍኖ፥ የትላልቆቹን ነባር ሥፍራ ለትናንሾቹ እያስረከበ፥ ፋርስን-ከእስራል አሜሪካኖች ጋር አፋጧል።ፍጥጫ፣ ግጭት፥ ዉዝግብ ፍትጊያዉ እንዲሕ በጭሩ ማብቂ ይኖረዋል ተብሎ አይታሰብም።ቀጣዩ-ምን እንዴት ይሆን-ይሆን ጥያቄ እንጂ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ላዛሬዉ ይብቃን።


ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ
Audios and videos on the topic