ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሲታወሱ | ባህል | DW | 15.08.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሲታወሱ

«የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የሞቱበት አርባኛ ዓመት» በሚል የተለያዩ የጀርመን ጋዜጦች የመጨረሻዉን የኢትዮጵያ ንጉስ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴን ታሪክና ከጀርመን ጋር የነበራቸዉን ቁርኝት አስታዉሰዋል። ጀርመናዉያን ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልዩ ቦታ ሲሰጡዋቸዉም ይታያል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:18

አፄ ኃይለ ሥላሴ


በጀርመን የሚታተሙ የተለያዩ ጋዜጦች ባለፈዉ ሳምንት ነሐሴ 21 የመጨረሻዉ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን በያዘዉ ወታደራዊ መንግሥት ከስልጣን ወርደዉ ከሞቱ አርባ ዓመት ሞላቸዉ ሲሉ፤ ንጉሰ ነገሥቱ በጀርመን ያላቸዉን ታዋቂነት አስነብበዋል።ጀርመናዉያን አፄ ኃይለ ሥላሴን የሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት በአበቃ በዘጠነኛዉ ዓመት እንዲሁም የፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክ «ምዕራብ ጀርመን» በተቋቋመ በአምስተኛዉ ዓመት፤ በጎርጎረሳዊዉ 1954 ዓ,ም ወደ ጀርመን የተጋበዙ የመጀመርያዉ ንጉሠ ነገሥት ነበሩ። ንጉሰ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ ጀርመንን ከሌላዉ ዓለም ጋር ያገናኙ ፈርቀዳጅ ፤ የአገር መሪ ሲሉ በክብር የሚያስቡዋቸዉ ጀርመናዉያን ጥቂት አይደሉም።
ባለፈዉ ዓመት በጀርመን የጃንሆይን የሕይወት ታሪክን « የመጨረሻዉ የአፍሪቃ ንጉሠ ነገሥት» በሚል በመጽሐፍ ለአንባብያን ያቀረቡት፤ የግርማዊነታቸዉ የቅርብ ዘመድና በጀርመን የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ፤ የታሪክ ምሑር ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ ካሳ እንደሚሉት ጃንሆይ በጀርመናዉያን ዘንድ የተከበሩ ናቸዉ።

Autorenlesung- Prinz Asfa-Wossen Asserate

የግርማዊነታቸዉ የቅርብ ዘመድና በጀርመን የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ፤ የታሪክ ምሑር ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ ካሳ


« የጀርመን ሕዝብ ሆነ የጀርመን መንግሥት ግርማዊ ኃይለሥላሴን እንደ ትልቅ ወዳጅና ለሀገሪቱ ከፍተኛ ግንኙነት የነበራቸዉ አድርገዉ ነዉ የሚያዩዋቸዉ። አብዛኛዉ የጀርመን ሕዝብ አብሶ ከስድሳ ዓመት በላይ የሆናቸዉ ጀርመናዉያን ዛሬ ድረስ እንደ ጎርጎረሳዊ አቆጣጠር 1954 ዓ,ም በጀርመን አገር አድርገዉት የነበረዉን ኦፊሴላዊ ጉብኝት በጣም አድርገዉ ያስታዉሳሉ። የግርማዊ ጃንሆይ ወደ ጀርመን አገር መምጣት በዝያን ጊዜ ከፍተኛ የምስራች ነበር። ምክንያቱም አንድ የዉጭ አገር ርዕሰ ብሔር ጀርመንን ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት በኃላ ለመጀመርያ ጊዜ ስለጎበኘ ነዉ። ከዚህም በላይ እንደ ትልቅ አንቲ ፋሽስት የታወቁት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፤ ጀርመን ሂትለርን ወደ ኃላ ትታ በአዲስ ሁኔታ የተመሰረተዉን አዲሲትዋን የጀርመን ዴሞክራቲክ መንግሥት ለብዙ ሰዉና በተለይ ለአብዛኛዉ የጀርመን ተወላጅ ከፍተኛ የደስታን ስሜት ስላመጣ በዚህ በጣም አድርገዉ ያስታዉሱዋቸዋል፤ በጣም አድርገዉም ያደንቁዋቸዋል።


ይህ ቀን በኢትዮጵያ እንብዛም አልተወሳም። ከሱ ይልቅ የልደታቸዉ ዕለት ትንሽ የማስታወሻ ዝግጅት ተካሂዶ ነበር፤ ያለን አንጋፋዉ ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ በበኩሉ፤ « ይህን ቀን ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዲታወስ ያደረኩት እኔ ነኝ እንጂ፤ በቤተሰብ ደረጃ ወይም ደግሞ የሳቸዉ ድርጅት የረፍታቸዉን ቀን መታሰብያ አስመልክቶ ምንም ያደረጉት ዝግጅት አልነበረም። ዳሩ ግን ባለፈዉ ሐምሌ 26 ቀን የጃንሆይ 123 ኛ የልደት በዓል ስናከብር በተደረገዉ ዝግጅት ላይ የረፍታቸዉን ቀን በማስታወስ

Buchcover - Prinz Asfa-Wossen Asserate

ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክ «ምዕራብ ጀርመን» በጎርጎረሳዊዉ 1973 ዓ,ም ከመራሄ መንግሥት ቪሊ ብራንድ ጋር ቦን ከተማ ላይ

አንስቼ ነበር። ይኸዉም ጃንሆይ የሞቱበት ቀን የፊታችን ነሐሴ 21 ቀን 40 ዓመት ብለናልና ፤ 40 ዓመት ይሆናል ብዬ ተናግሪ ነበር። »
ጀርመን ፌደራል ሪፐብሊክ ከተቋቋመ በኋላ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወደ ጀርመን ተጋብዘዉ ለመጀመርያ ጊዜ ቦን ከተማ አቀባበል ሲደረግላቸዉ በከፍተኛ ዝግጅት እንደነበር ልጅ አስፋወሰን አስራተ ይናገራሉ።
«ጀርመናዉያን ለግርማዊ ጃንሆይ ያሳዩት የፕሮቶኮል ሁኔታ ከዝያ በኃላ በጎርጎረሳዉያኑ 1965 ዓ,ም ለንግስት ኤልዛቤጥ አደረጉ እንጂ ለጃንሆይ እንተደረገዉ አቀባበል ለማንኛዉም አዉሮጳዊ ሆነ አሜሪካዊ ርዕሰ ብሔር እንዲህ አይነት አቀባበል ተደርጎ አይታወቅም። አንደኛ ለብዙ ቀናት ነዉ ጀርመንን የጎበኙት። በአሁኑ ጊዜ ከሁለት ቀናት በላይ ርዕሰ ብሄሮች አይቆሙም፤ ከዝያም በላይ በዝያን ጊዜ ቦን ከተማ አጠገብ የነበሩ የዱር አንበሳ እንደ ዝሆን አንበሳ ሁሉ በክብር አቀባበሉ ሥነ-ርዓቱ ላይ አደባባይ እንዲወጡ ተደርጎ ነበር። በተለይ የራይን ወንዝን የሚያሻግረዉ ትልቁን ድልድይ እጅግ አሸብርቀዉት ነበር። በተጨማሪ በዝያን ጊዜ ጀርመናዉያን በታላቁ ቤተ-መንግስታቸዉ ለመጀመርያ ጊዜ ከፍተኛ የአቀባበል ሥነ-ስርዓት አድርገዉ ከእንቅልፏ የተነሳችዋን ጀርመን አገር ሌላ አገር አድርገዋት ነበር ማለት ይቻላል።


ጃንሆይ በዝያን ጊዜ ለተቸገረዉ የጀርመን ሕዝብ ርዳታ ሰጥተዉ እንደነበርም ይነገርላቸዋል፤ ጀርመናዉያንም ይህንኑ ይናገራሉ?

Haile Selassie

ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በጎርጎረሳዊዉ 1974 ዓ,ም

« አዎ መርሳት የሌለብን በርግጥም በዝያን ጊዜ ግርማዊ ጃንሆይ ጀርመንን ከመጎብኘታቸዉ በፊት በ 1947 ዓ,ም ጀርመን በከፍተኛ ብርድና ረሀብ በተጠቃችበት ጊዜ ማለት ከሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት በኋላ ማለት ነዉ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጀርመን ሕዝብ 200 ሺ ዶላር የሚያወጣ ቡና እና ብርድ ልብስ ማበርከቱ የታወቀ ነበር። ስለዚህ ይህን ርዳታ የጀርመን ህዝብ ስላልረሳዉ በከፍተኛ ሁኔታና በደስታ ነዉ ፤ ንጉሰ ነገሥቱን የተቀበልዋቸዉ።
እርሶ የጃንሆይ የቅርብ ቤተ-ዘመድ ኖት። አሁን እሳቸዉን ለማስታወስ የምታደርጉት ዝግጅት አለ? ትገናኛላችሁ?
« አዎ በየጊዜዉ ሁላችንም በአንድ ላይ እንሰባሰባለን፤ በመካከላችን የቀረበ ግንኙነትም አለ፤ ከዚህም በላይ በልዑል ሳህለ ስላሴ ኤርምያስ የሚመራዉ የኢትዮጵያ የዘዉድ ምክር ቤት አሜሪካ ዉስጥ ይገኛል፤ ሥራዉን ይሰራል ። ግርማዊ አፄ ኃይለሥላሴም ስማቸዉ እየተጠራ እንዲቀጥል ብዙ ነገር እያደረጉ ነዉ።»


ዲያቆን ሳለ ስለጃንሆይ ብዙ ያቀኝ እንደነበር የሚገልጠዉ ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ በበኩሉ እንዲህ ያስታዉሳል።
« በርግጥ ስለንጉሰ ነገሥቱ ከኔ የበለጠ በቅርበት የሚያቁዋቸዉ መናገር ይችላሉ፤ እንደተባለዉ ነገሩ ፍላጎት አልያም ተነሳሽነት ባለመኖሩ ፤ ወይም መድረኩን ባለማግኘት ይሆናል። እንደተባለዉ ብዙዉን ጊዜ ጃንሆይን ማንም የሚያስታዉሳቸዉ የለም፤ እኔ እንግዲህ ዲያቆን የነበርኩ ጊዜ ጀምሮ፣ « የንጉስ ዲያቆን ነበርኩ ስዕል ቤት ባሃታ፤ ፀልዩ ስል የኖርኩ ጠዋትና ማታ። ምስባኩን ስሰብከዉ ንጉሴ ፊት ቆሜ አልጠግባትም ነበር ኢትዮጵያን አዚሜ።» እያልኩ ብዙ ጊዜ አስታዉሳቸዋለሁ። የሳቸዉ ሥራ ምን ተቆጥሮ ያልቃል፤ በትምህርቱ ነዉ ፤ በጤናዉ ነዉ፤ በስልጣኔዉ ነዉ፤ በብሔራዊ አንድነቱ ነዉ ፤ በነፃነቱ ነዉ፤ ብቻ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ምን ያላደረጉት ነገር አለ? እንደዉም እዚህ ባለፈዉ ሐምሌ 26 ዋቤ ሸበሌ ሆቴል ቤተሰቦቻቸዉም በተገኙበት በተከበረዉ የልደት በዓላቸዉ ላይ የቀድሞዉ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወልደጊዮርጊስ ተገኝተዉ ሃዉልታቸዉ እንዲቆም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስታወሻ እንደፃፉ አድርገዉ ሃሳብ ለዛ ለተሰበሰበዉ ህዝብ አቅርበዉ ነበር። እናም ሁላችንም ይህን ነገር በጉጉት እየጠበቅን ነዉ። አፄ ኃይለሥላሴን ያህል ንጉሰ ነገሥት አዲስ አበባ ዉስጥ እንዴት አንድ መታሰብያ አይኖራቸዉም? እጅግ በጣም የሚያሳዝን ነዉ!»

Äthiopischer Kaiser Haile Selassie zu Besuch in Bonn 1973

« ዴር ሌትዝተ ካይዘር ፎን አፍሪቃ፤ ማለትም የአፍሪቃ የመጨረሻዉ ንጉሰ ነገሥት» በሚል ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፤ 415 ገጾች ያሉት፤ ዳጎስ ያለ ታሪክ አዘል መጽሐፍ በጀርመንኛ ቋንቋ በዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ ካሳ


የልደታቸዉ አከባበር እንዴት ነበር? « እዚህ የእሳቸዉን ልደት ባከበርንበት ጊዜ ሰዎች እንባ በእንባ ሆነዉ ነዉ ነበር። ለምሳሌ « ኃይለሥላሴ ግርማዊ ልደት ዛሬ ነዉ ፤ ታሪክህ ታሪክህ ህያዉ ነዉ ስምህ» ,,,እያልን ያከበርነዉ የትምህርት ቤቱንም ሆነ የቤተ-ክርስትያኑን መዝሙር እያስታወስን ነዉ። እንደ ንጉሰ ነገስቱ አይነት ታላላቅ ሰዎች በሀገራቸዉ አይከበሩም። ይከብር ነብይ በሀገሩ ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፤ ነብይ በሀገሩ አይከበርም፤ በዘመዶቹም በቤተሰቦቹም። እንደ ኃይለሥላሴ ያሉ ነብያት የሆኑ ሰዎች በዉጭ አገር እንጂ በኛ አገር ይህን ያህል ክብር አይሰጣቸዉም።»

በዉጭ ዲፕሎማሲ ግንኙነታቸዉ የተዋጣላቸዉ እንደነበሩ የሚነገርላቸዉ አፄ ኃይለሥላሴ፤ በአስተዳደራቸዉ ዘመን በተከሰተዉ ረኃብ እና መዘዙን በተመለከተ ስማቸዉ ጎድፎአል። የጃንሆይ የቅርብ ዘመድ ልጅ አስፋወሰን አስራተ፤ በርግጥ ስህተት ተፈፅሞአል ሲሉ ይገልጻሉ።


« ርግጥ ነዉ የሰዉ ልጅ ሆኖ እንከን የሌለዉ ሰዉ አይገኝም፤ አብሶ በፖለቲካ አመራር ዉስጥ ያለ ሰዉ፤ ጠንካራና ደካማ ወገን ሊኖረዉ ይችላል። ስለ ኃይለሥላሴ ስንነጋገር በርግጥ ነዉ በመጨረሻዉ ዘመን ላይ 14 ዓመት በአልጋ ወራሽነት፤ ከዝያ በኃላ ከ40 ዓመት በበለጠ ጊዜ በንጉሰ ነግስትነት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ናቸዉ። በዚህ ጊዜ ዉስጥ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስህተቶች አልተሰሩም ማለት ያስቸግረናል። ዋናዉ ጉድፈትና ምናልባት ያቺ የ 3000 ዘምን እድሜ ያላትን ዘዉድ ወድቃ እንድትቀር የተደረገበት አንዱ ጥፋት ምናልባት እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 1960 ዓ,ም የተደረገዉ የግልበጣ ሙከራ ትምህርት ስላልሆነን ነዉ። ይሄ በተደረገ በማግስቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ እዉነተኛ ከላይ የመጣ ለዉጥ ያስፈልግ ነበር። ከሁሉምበላይ በዝያን ጊዜ የነበረዉ ሕገ- መንግስት መለወጥና መሻሻል ነበረበት። ንጉሰ ነገሥቱም ሙሉ ስልጣናቸዉን ትተዉ ስልጣኑን ከፓርላማ ጋር መካፈል ግዴታ ነበረባቸዉ። እነዚህ ነገሮች ባለመደረጋቸዉና የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት የዉስጣዊዉ የሀገራዊዉ ፖሊሲ በእዉነቱ በዝያን ጊዜ የነበሩትን በተለይ ከዉጭ አገር ትምህርት ተምረዉ የመጡትን ኢትዮጵያዉያን ራዕይ ሙሉ

Äthiopischer Kaiser Haile Selassie zu Besuch in Bonn 1954

ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የፌደራል ጀርመን ሪፐብሊክ «ምዕራብ ጀርመን» በተቋቋመ በአምስተኛዉ ዓመት በጎርጎረሳዊዉ 1954 ዓ,ም ወደ ጀርመን ቦን ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ የተጋበዙ ርዕሰ ብሄር ነበሩ።

በሙሉ ማሟላት ባለመቻሉ ያዉ አብዮት ኢትዮጵያ ላይ እንዲመጣ ሆነ። »
አንጋፋዉ ጋዜጠኛ ንጉሴ አክሊሉ ከስልጣን እንዴት እንደተነሱ እና የአገዳደላቸዉን ሁኔታ እንዲህ ይገልፃል።«እንግዲህ እሳቸዉ መስከረም ሁለት ቀን 1967 ዓ,ም የዛሬ 40 ዓመት ነዉ ከስልጣን የወረዱት። መጀመርያ ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ነዉ የተወሰዱት። የሚገርመዉ ለርሶ ደህንነት ሲባል ነዉ ተብለዉ በቮልስ ቫገን ነበር የወሰድዋቸዉ። ጀነራል ሉሉ በሚባሉ በሹፊራቸዉ ቮልስ ቫገን ነበር የተወሰዱት። ታድያ ለምን ድነዉ በቮልስ ቫገን የምትወስዱኝ ? ብለዉ አልጠየቁም። ግቡ አልዋቸዉ ገቡ ፤ ወሰድዋቸዉ ። ሲወስዱዋቸዉ ህዝቡ ሌባ ሌባ እያለ ይጮኽ ነበር። እና አብረዋቸዉ የነበሩትን መኮንኖች ህዝቡ ምን እያለ ነዉ? ሲሉ ጃንሆይ ጠየቁ። ከዝያም መኮንኖቹ ሌባ ሌባ ነዉ የሚለዉ ብለዉ መልስ ይሰጡዋቸዋል። ጃንሆይም መለስ አድርገዉ ፤ ታድያ ምን ያድርጉ በጠረራ ፀሐይ ንጉሳቸዉን ሰርቃችሁ ስትሄዱ ምን ያድርጉ ብለዉ አሉ ይባላል። ከዝያ በኋላ ጃንሆይን ወስደዉ አራተኛ ክፍለ ጦር አስቀመጥዋቸዉ። እንደገናም ወደ ታላቁ ቤተ- መንግስት አመጥዋቸዉ። ታላቁ ቤተ- መንግስት ስዕል ቤት ኪዳነ ምህረት እየፀለዩ ለብቻ እዝያ እየኖሩ ነበር። ከዝያም ድንገት ነሐሴ 21 ቀን አረፉ ተብሎ ተነገረ። ነገር ግን ከጠዋት ጀምሮ ቤተ ክርስትያኑ አካባቢ ጉድጓድ ይቆፈር እንደነበር ታዉቋል። እዝያ የነበሩ መነኮሳት ለምን ይህ ጉድጓድ ይቆፈር እንደነበር እንደማያቁ ተናግረዋል ። ከዝያ በኃላ ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ አንድ የቅርብ ሰዉ የነበር የመቃብር ቦታቸዉን ጠቁም ተብሎ ከአንድም ሁለት ቦታ አሳይቶ፤ በትክክል ሊያሳይ አልቻለም።

Kaiser Haile Selassie von Äthiopien und John F. Kennedy 1963

ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ከጆኔፍ ኬኔዲ ጋር

ምናልባት ይህ ሰዉ የሰሚ ሰሚ ይሆናል፤ ወይ አላየ ይሆናል፤ መጨረሻ ላይ ግን አሰቃይተዉት የጦቀመዉ ቦታ ኮነሬል መንግስቱ ቢሮ ከስር አፅማቸዉ እንደተገኘና እንደወጣ ነዉ የሚታወቀዉ። ከዝያም አፄ ምንሊክ ባረፉበት ቦታ አፅማቸዉ አረፈ። ከዝያም ከተወሰነ ዓመት በኃላ አፅማቸዉ ብሔራዊ ክብርም ሳይሰጠዉ አፍሪቃ ሕብረትን የመሰረቱ ጀግና የአፍሪቃ መሪዎች ሳይሸኝዋቸዉ ሳይቀብሩዋቸዉ የቀብሩ ሥነ- ስርዓት ተቻኩሎ በአሰሩት ቅድስት ስላሴ ቤተክርስትያን ተፈፅሞአል። እና ጃንሆይ ሞተዉ ተገኙ ነዉ፤ የተባለዉ ። ግን ጊዜና ታሪክ ብዙ የሚያወጣቸዉ ነገሮች አሉ። የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ብቻ አይደለም፤ የእንደዚህ አይነት ታላላቅ ኢትዮጵያዉያን አፅም የትነዉ የወደቀዉ ተብሎ የሚፈለግበት አንድ ቀን ይመጣል። ይህን ተስፋ እናደርጋለን።
እንድያም ሆኖ ይላሉ በጀርመን ነዋሪ የሆኑት የጃንሆይ የቅርብ ዘመድና በጀርመን የአፍሪቃ ጉዳይ አማካሪ፤ የታሪክ ምሑር ዶ/ር ልጅ አስፋዉ ወሰን አስራተ ካሳ፤ እንድያም ሆኖ ጃንሆይ ስማቸዉን በኢትዮጵያ በአፍሪቃ የታሪክ ማኅደር ትተዉልን ሄደዋል።
የአፍሪቃዉ የመጨረሻ ንጉሰ ነገሥት በሚል ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ አርባኛ ዓመት የሙት ቀንን አስታከን ያዘጋጀነዉ መሰናዶ እስከዚሁ ነበር ። ለቃለ-ምልልሱ የተባበሩን እያመሰገንን፤ ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

ጃኪ ዊልሰን/አዜብ ታደሰ


ነጋሽ መሃመድ

 ይህ ዘገባ አፍሪቃዊ ሥረ መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ልዩ ዝግጅት አካል ነው።

 This report is part of African Roots, a project realized in cooperation with the Gerda Henkel foundation.

Audios and videos on the topic