ቀውስ ባልራቃት ደቡብ ሱዳን የነጻነት በዓል | አፍሪቃ | DW | 11.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ቀውስ ባልራቃት ደቡብ ሱዳን የነጻነት በዓል

ለበርካታ ዓመታት በአስከፊ የርስ በርስ ጦርነት አልፋለች፤ ነፃ ከመውጣቷ በፊት ከ2,5 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎቿን ለጦርነቱ ገብራለች። ደቡብ ሱዳን። ነፃ ከወጣች በኋላም ቢሆን ነዋሪዎቿ በጦርነቱ ወላፈን ከመርገፍ አልተረፉም። ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ከ50,000 ያላነሱ ነዋሪዎቿ ለሞት ተዳርገዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:36
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:36 ደቂቃ

ቀውስ ባልራቃት ደቡብ ሱዳን የነጻነት በዓል

ወትሮም ቢሆን የመንግስታዊ አወቃቀርም ይሁን መሰረተ-ልማት ያልነበራት ይኽች አፍሪቃዊት ሀገር ከአራት ዓመታት በፊት ነጻ ብትወጣም እነሆ በሁለት እግር መቆም ግን ተስኗታል።

አዲሲቱ አገር ከሱዳን ስትገነጠል ቀድሞ በነጻነት ናፋቂ ዜጎቿ እና መገንጠልን ባቀነቀኑ ምዕራባውያን ዘንድ እንደ ትልቅ ስኬት ታይቶ ነበር። በአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት እና በሱዳን ህዝቦች አርነት ንቅናቄ (Sudan People’s Liberation Movement) ውስጥ ስር የሰደደው ሙስና፤ እንዲሁም ከሱዳን ጋር የገባችበት የነዳጅ ሽያጭ ክፍፍል እሰጥ አገባ የአዲሲቱ አገር ተስፋ የመጀመሪያ ፈተናዎች ሆኑ። ከአስራ ዘጠኝ ወራት በፊት በፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር እና በያኔው ምክትል ፕሬዝዳንት የአሁኑ የአማጽያን መሪ ሪየክ ማቻር መካከል የተፈጠረው ልዩነት ወደ ተከታዮቻቸው ተዛምቶ በጁባ ጎዳናዎች ፈነዳ። የሁለቱን መሪዎች ነገዶች ዲንካና ኑዌሮችን አቃቃረ። በድህነት የሚማቅቁትን 2 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን እግር ለስደት እና መፈናቀል ዳረገ። 4.6 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያንን ደግሞ ለረሀብ ሊዳርግ ይችላል ተብሎለታል፤ ይኸው ከባለሥልጣናቱ የጀመረው የሁለቱ ወገን ግጭት።

የፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና ሪየክ ማቻር አለመግባባትና ጦር መማዘዝ ከ2.25 ሚሊዮን በላይ ደቡብ ሱዳናውያን ሕይወት ማመሳቀሉን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን የአፍሪካ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ካሪን ደ ግሩይል ይናገራሉ።

«ደቡብ ሱዳን ከ225,000 በላይ ሰዎች በማያባራ ግጭት ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው 730,000 ሰዎች አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል።ብዙዎቹ የደቡብ ሱዳን አጎራባች ወደ ሆኑት ኢትዮጵያ፤ ኬንያና ኡጋንዳ የተሰደዱ ናቸው። 1.5 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ በዚያው በአገራቸው ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለው በደቡብ ሱዳን የድንበር አካባቢዎች ይገኛሉ።»

ተወልደው ባደጉበት የተፈናቀሉት 1.5 ሚሊዮን ዜጎችን መርዳት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ፈተና ሆኗል። ማብቂያ ያጣው ግጭት እና የመሰረተ-ልማት እጦት ለካሪን ደ ግሩይል ተቋም መሰናክል ናቸው።ደቡብ ሱዳናውያን ነጻ የወጡበትን አራተኛ አመት ያክብሩ እንጂ ሰላምና እርጋታ እንደጎደለ ነጻነቱም ጣዕም አልባ እንደሆነ አላጡትም። በዋና ከተማዋ ጁባ የጆን ጋራንግ አደባባይ በተከበረውና የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒና በሺዎች ከሚቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ዜጎች ታድመውበታል የተባለው የነጻነት በዓል እንደ ኢድሙን ያካኒ ባሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።«አሁን የምንደሰትበት አንዳችም ነገር የለም ያሉት» ኢድሙንድ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል፤ንብረት ወድሟል። ሰብዓዊ ቀውሱም መፍትሄ አላገኘም።» ይላሉ። ሲትዝን የተባለዉ ጋዜጣ አዘጋጅ ቪክቶር ኬኒዋኒ ለአስራ ዘጠኝ ወራት በዘለቀው የርስ በርስ ግጭት ምክንያት አራተኛው የነጻነት በዓል ትርጉም ማጣቱን ይናገራል።

«ብዙ ሰዎች አሁን በጦርነቱ ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ወደ ሱዳን ተመልሰው መሄድ አይፈልጉም። ደቡብ ሱዳን ከካርቱም በመገንጠሏ የሚጸጸት የለም። ይሁንና ደቡብ ሱዳን በጥሩ ሁኔታ ላይ ብትገኝ ኖሮ ከፍተኛ ፈንጠዝያ በኖረ ነበር። ብዙ ሰዎች የሰላም ስምምነት ቢፈረም ኖሮ ደስተታው ከፍተኛ ይሆን ነበር ብለው ያምናሉ።»

የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላትን የሚያሸማግለው ኢትዮጵያ፤ኬንያ እና ኡጋንዳን ያካተተው የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት በምኅፃሩ ኢጋድ እሳካሁን ጠብ ያደረገው ነገር የለም። በድርድሩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸውና እጃቸውን ያስገቡት አሜሪካ፤ኖርዌይ የአፍሪቃ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሳልቫ ኪርና ሪየክ ማቻር ላይ ጫና ማሳደር ተስኗቸዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዚሕ ቀደም የአውሮጳ ህብረትና አሜሪካ የጉዞና የሃብት ማዕቀብ በተጣሉባቸው ስድስት የጦር መሪዎች ላይ ድጋሚ ማዕቀብ ጥሏል። ማዕቀቡም ይሁን በአዲስ አበባ ለወራት የዘለቀው የድርድር ሂደት እንስቶችን ከመደፈር ልጆችን ከግዳጅ ውትድርና አልታደጋቸውም። በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ማስፈን ካስፈለገ ተፋላሚ ኃይላቱ ለውሳኔና ድርጊቶቻቸው ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል የሚሉት የደቡብ ሱዳንን ቀውስ የሚከታተሉ ተንታኞች በተለይ ሁለቱን ጉምቱ ባለስልጣናት ዓለም ከሚገባው በላይ ታግሷቸዋል ሲሉ ይተቻሉ።ቪክቶር ኬኒዋኒ ደቡብ ሱዳናውያን በተቀናቃኞቹ አሸማጋዮች ገለልተኝነት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ይናገራል።

«ሰዎች ሲጋጩ ወገንተኝነት የሌላቸው እንደ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት-ኢጋድ አይነት አሸማጋዮች ያስፈልጋሉ። አንዳንድ ሰዎች ግን የምስምራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ-መንግስታት-ኢጋድ አሸማጋዮች ለአንደኛው ወገንተና ናቸው የሚል ቅሬታ አላቸው። ጦርነቱ ሲካሄድ አስራ ዘጠኝ ወራት አስቆጠረ። ይህ ጊዜ የሰላም ቢሆኑ ኖሮ በርካታ ስራዎች በተሰሩ ነበር። አሁን መንገዶች የሉንም። ነጻነት ቢኖረንም ግዛቶቹን የሚያገናኙ መንገዶች ሊኖሩን ይገባል።»

የደቡብ ሱዳን ዘላቂ ሰላም ለአስራ ዘጠኝ ወራት የዘለቀውን ግጭት በመፍታት ብቻ የሚመለስ አይደለም የሚሉት የፖለቲካ ተንታኞች ሀገሪቱ ነጻ ከመውጣቷ በፊት የነበሩት ውስብስብ ችግሮች መፍትኄ እንደሚያሻቸው ይወተውታሉ። ሙስና፤የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝቅጠት፤በጎሳዎች መካከል ያለው የሻከረ ግንኙነትና ከሱዳን ጋር በነዳጅ ሽያጭ ክፍፍልና የግዛት ይገባኛል ጥያቄ የተፈጠረውን ውጥረት በቀዳሚነት ይጠቅሳሉ።

በመንግስትና በገዢው ፓርቲ ውስጥ በተንሰራፋው ሙስና ምክንያት የመሰረተ-ልማት፤ትምህርት እና ጤና ሥራዎች አልተከወኑም። ወጣት ደቡብ ሱዳናውያን የሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት ችግሮች አሉባቸው። በተለይም በነዳጅ ሃብት የበለጸገው የላይኛው ናይል ግዛት ነዋሪዎች ከተፈጥሮ ችሮታቸው የሚያገኙት አንዳች ነገር የለም። በሥራ አጥነትና የኑሮ ውድነት የሚሰቃዩት ወጣቶች የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት በሚሯሯጡ የጦር መኮንኖች በውትድርና የመመልመል እጣ ይገጥማቸዋል።ካሪን ደ ግሩይል እና ተቋማቸው የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን መፍትኄ ያጣው ቀውስ አሁንም ዜጎችን ለስደት መዳረጉን ይቀጥላል የሚል ስጋት ገብቷቸዋል።

«እንደ አለመታደል ሆኖ ግጭቱን ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ሲመክን ተመልክተናል።የሰብዓዊ ቀውሱም አስከፊ እየሆነ ነው። አሁንም የመኖሪያ ቀያቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት አገሮች የሚሰደዱ ደቡብ ሱዳናውያን ቁጥር እየጨመረ ነው። በመጪዎቹ ጊዜያትም ይህ ቁጥር ይጨምራል የሚል ስጋት አለን። ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ ለመቀበልም ራሳችንን እያዘጋጀን ነው።በኢትዮጵያና በኬንያ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎችን እያዘጋጀን ነው።

ተፋላሚ ኃይላቱ አሁን በናይል ወንዝ ግራና ቀኝ ተፋጠዋል። አንዳቸው ወደ ሌላው የሞርታር ጥይቶችን ያስወነጭፋሉ። ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ከተቀዳጀች አራት ዓመታትን አስቆጥራለች።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች