ቀኝ ፅንፈኛው የናዚዎች ቡድንና የፍርዱ ሂደት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 23.04.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ቀኝ ፅንፈኛው የናዚዎች ቡድንና የፍርዱ ሂደት

የሟች ቤተሰቦች እናት ባሏን ፣ ልጆች አባታቸውን በነፍሰ ገዳይ መነጠቃቸው የደረሰባቸው ድንጋጤና መራር ሃዘን ሳያንስ ፣ ጋሜዝና እናቷ ሜህሜት በተገደሉ በማግሥቱ ፖሊስ ለ 6 ሰዓታት በተናጠል ያቀረበላቸው ጥያቄ ቅስማቸውን ሰብሯል

ጀርመን ውስጥ በህቡዕ ሲንቀሳቀስ የቆየው በጀርመንኛው ምህፃር NSU በመባል የሚታወቀው የናዚዎች ቡድን ለተጠረጠረባቸው ግድያዎች ተጠያቂ ከተባሉት የአንዷ የፍርድ ሂደት ከ 12 ቀናት በኋላ ይጀመራል ። 9 የውጭ ተወላጆችና 1 ፖሊስ ገድሏል የተባለው ይህ ቡድን የፈማቸው ወንጀሎች ና በቅርቡ የሚጀመረው ችሎት የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው።

የ20 አመትዋ ወጣት ጋምዜ ኩባሲክ አባቷ እንዲያርፉ በማሰብ ማክሰኞ በጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 4 2006 ዓም ፣ ታናሽ ወንድሟን ሜሬትን ጠዋት መዋዕለ ህፃናት እንደምታደርሰው ነግራቸው አስደስታቸው ተለያዩ ። ከሰዓት በኋላ ደግሞ አባቷን ተክታ መሥራት ነበረባትና አገር ሰላም ብላ ሰሜናዊ ዶርትሙንድ ወደ ሚገኘው ክዮስካቸው ስትደርስ በውኗም በህልሟም ያልጠበቀችው ነገር ገጠማት ። አካባቢው ሰው እንዳያልፍ ታጥሮ በሰፈሩም አምቡላንስና የፖሊስ መኪናዎች ፈሰው ነበር የደረሰችው ። ጋምዜ ወደ ውስጥ ለመግባት ብትሞክርም በፖሊስ ተከለከለች ።

« በእድሜ ገፋ ያሉ ፖሊስ ወደ ኔ መጡ እስከዚያ ድረስ ምንም አልተናገሩም ነበር። ወይዘሪት ኩባሲክ አባትሽ ሞቷል አሉኝ ። ያሉት ሁሉ ገብቶኛል ፣ ሁሉንም ሰምቻለሁም ፤ ሆኖም በዚያ ቅፅበት ግን እኔ ራሴን አልነበርኩም ። »

Gamze Kubasik Tochter des NSU Mordopfers Mehmet Kubasik

ሜህሜት ከልጆቹ ጋር

ጋምዜ ለመጨረሻ ጊዜ አባቷን ያየችው የዚያኑ ለት ጠዋት ታናሽ ወንድሟን መዋዕለ ህፃናት እንደምታደርሰው ስትነግራቸው ሲያመሰግኗት ነበር ። አባቷ ሜህመት ኩባሲክ NSU በተባለው የአፍቃሪ ናዚዎች ነፍሰ ገዳይ ቡድን ክዌስካቸው ውስጥ ያን እለት በፖሊስ ግምት ከቀኑ 6 ሰዓት እስከ 7 ሰዓት ባለው ጊዜ የተገደሉ ስምንተኛው ሰለባ ነበሩ ። የአባቷን መገደል ስትሰማ ብርክ ያዛት ። ወዲያውኑ ግን አባቷ ከማንም ጋር ችግር ገጥሟቸው አያውቅምና ማን ሊገድለው ይችላል የሚለው ጥያቄ በዐዕምሮዋ ብልጭ አለ ።

« በጣም ተጫዋች ነበር ሁላችንም ብዙ ጊዜ ከርሱ ጋር እንስቃለን ። ከሁሉም ጋር ተግባቢ ነበር ። ከአባቴ ጋር ከተማ ውስጥ ስንዘዋወር መላው የዶርትሙንድ ህዝብ ይህን ያውቃል የሚል ስሜት አለኝ ።»

ኩርዳዊው የቱርክ ዜጋ ሜህሜት ኩባሲክ ጀርመን ለ 15 ዓመታት ኖረዋል ። በ1980 ዎቹ መጨረሻ በመኖሪያቸው በደቡባዊቷ ቱርክዋ አናታልያ ከተማ አስተማማኝ ህይወት መግፋት ባለመቻላቸው ወደ ጀርመን ዶርትሙንድ መጥተው ተገን ጠይቀው ተሳካላቸው ። እርሳቸውና ቤተሰባቸው እጎአ በ2003 የጀርመን ዜግነት አግኝተዋል ። ጋምዜ ስለአባትዋ ስትናገር አዲሷን መኖሪያቸውን ጀርመንን በጣም ነበር የሚወዷት

« ለአባቴ ፣ ጀርመን ልዩ አገር ነበር ። ጀርመንን እንደ ሃገሩ ነበር የሚቆጥረው ። ከእናቴና ከእኔ ጋር ወደ እዚህ ሃገር መጥቶ በነፃነት መኖር በመቻሉ በዴሞክራሲ የሚያምነው አባቴ በዲሞክራሲያዊት ሃገር በመኖሩ ይረካ ነበር ፤ »

Rechtsextremistische Terroristin Beate Zschäpe

ቤአተ ትሼፐ

ሜህሜት NSU ሲል ራሱን የሚጠራው ቡድን እጎአ ከመስከረም 9 2000 እስከ ሚያዚያ 6 2007 ከገደላቸው 8 ቱርኮችና 1 ግሪካዊ እንዲሁም አንዲት ጀርመናዊት ፖሊስ መካከል አንዱ ናቸው ። እ.ጎ.አ ህዳር 2011 በስውር እንደሚንቀሳቀስ የተደረሰበት NSU ከነፍስ ግድያው ሌላ እጎአ ከ2001 እስከ 2004 ኮሎኝ ውስጥ የቦምብ ጥቃቶች በማድረስ 14 የባንክ ዘረፋዎች በመፈፀም እንዲሁም የውጭ ዜጎች መኖሪያዎችን በማቃጠልም ተጠርጥሯል ። የጀርመን አቃቤ ህግ እንዳለው ቀኝ ፅንፈኛው NSU ግድያውን የፈፀመው በውጭ ዜጎች ጥላቻ መንስኤ ነው ። የሟች ቤተሰቦች እናት ባሏን ፣ ልጆች አባታቸውን በነፍሰ ገዳይ መነጠቃቸው የደረሰባቸው ድንጋጤና መራር ሃዘን ሳያንስ ፣ ጋሜዝና እናቷ ሜህሜት በተገደሉ በማግሥቱ ፖሊስ ለ 6 ሰዓታት በተናጠል ያቀረበላቸው ጥያቄ ቅስማቸውን ሰብሯል ። ጥያቄዎቹም ግራ የሚያጋቡ ነበሩ ለጋሜዝ ። አባትሽ አደንዛዥ እፅ ይጠቀም ነበር ወይ ? ይሸጥስ ነበር ወይ ? ከማፍያም ሆነ PKK ከተባለው ከታገደው የኩርድ ሠራተኞች ፓርቲ ጋር ግንኙነት ነበረው ወይ ? ሲሉ ፖሊሶች ያቀረቡላት ጥያቄዎች አስደንግጠዋታል ። የሜህሜት ቤት በአነፍናፊ ውሻ ተፈትሿል ፤መኪናቸውም ለምርመራ እንዲገነጣጠል ተደርጎ ነበር ። ምንም አልተገኘባቸውም እንጂ የጋሜዝና የ 2ቱ ታናናሽ ወንድሞቿ ምራቅ ሳይቀር ለምርመራ ተወስዷል ። ጋምዜ ለፖሊሶቹ ምናልባት ገዳዮቹ ቀኝ አክራሪዎች ሊሆኑ ይችላሉ ብላቸውም ነበር ። ይህን የሚያመለክት ማስረጃ የለም የሚል መልስ ነበር የተሰጣት ። ሜህሜት በተገደሉ በ2ተኛው ቀን የ21 አመቱ ቱርካዊ የካስል ነዋሪ ሃልያት ዮዝጋት ሜህሜት በተገደሉበት ተመሳሳይ ሽጉጥ ተገድሎ ተገኘ ። በተመሳሳይ መንገድ የተገደለ 8 ተኛው ቱርካዊ መሆኑ ነው ። መገናኛ ብዙሃን ሁለቱ ሟቾች ከአንድ አካል ጋር በድብቅ በጀመሩት ንግድ መንስኤ ሳይገደሉ እንዳልቀረ ማናፈስ ያዙ ። ይህ ጥርጣሬ ከቤተሰቡ በስተጀርባ የሰዉ መንሸኳሾክያ በመሆኑ አባትዋም ነፃ መሆናቸውን ለማራገጋጥ አለመቻሏ ጋሜዝን በእጅጉ ያንገበግባት ነበር ። ይህ ሆድ ሆዷን ሲበላት የከረመው ጋሜዝ ከ 5 አመት በኋላ የገዳዮቹ ማንነት እንደተደረሰበት ሲገለፅ ሸክሟ ከላይዋ ላይ የወረደ ያህል ነው የተሰማት።

በሌላ በኩል ሰዎች በፀጉራቸው ቀለም ወይም የተለየ ሃይማኖት በመከተላቸው ብቻ መገደላቸው አሁንም ያስደነግጣታል ። በምርመራው ሂደት መርማሪዎችና የፌደራል የህገ መንግሥት ጠባቂ መስሪያ ቤት የፈፀሙት ስህተት ያናድዳታል ። የነፍሰ ገዳዮቹ ማንነት ከታወቀ በኋላ ጠቃሚ የሆኑ ሰነዶች እንዲጠፉ መደረጉ ከስህተቶቹ አንዱ ነው እንደ ጋምዜ ። ጀርመን ፍራንክፈርት ነዋሪ የሆኑት የህግና ፖለቲካ ሳይንስ ምሁር እንዲሁም የጀርመንኛ ቋንቋ መምህር ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ ጉዳዩ መጣራት ከመጀመሩ በፊት ሰነዶች እንዲጠፉ መደረጉ ያስከተለውን መዘዝና ያስደረውን ተፅእኖ ያብራራሉ ።

ለተገደሉት ሰዎች መታሰቢያ በተደረገበት ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ወንጀሉን ለማጋለጥ ሁሉም ነገር ይደረጋል ብለው ቃል ገብተው ይህ በመፈፀሙ አባቷ የተገደሉባት ጋሜዝ ያስገርማታል ። ከዛሬ 13 አመት አንስቶ በተከታታይ ለ 8 አመታት 9 የውጭ ዜጎችና አንድ ፖሊስ በስውር ይንቀሳቀስ በነበረው NSU መገደላቸው ለረዥም ጊዜ አለመታወቁ ብዙዎችን እስካሁን የሚያነጋገግር ጉዳይ ነው ። ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ የነፍስ ግድያው ሳይደረሰበት እስከ ዛሬ አንድ አመት ተኩል ገደማ ድረስ መቆየቱ አነጋጋሪ የሆነበትን ምክንያት ያብራራሉ ።

የ 10 ሰዎች ግድያ በማቀነባበርና በመፈፀም የተጠረጠሩት Uwe Mundlos and Uwe Böhnhardt የተባሉት የውጭ ዜጎችን እያሳደደ የሚገድለው የነፍሰ ገዳዩ ቡድን አባላት በጎርጎሮሳውያኑ ህዳር 4 ፣ 2011 ዓ ም አይዘናህ በተባለ ከተማ ባንክ ከዘረፉ በኋላ እንደ ቤትም ይጠቀሙበት የነበረው መኪና በእሳት ካያዙ ካደረጉ በኋላ የራሳቸውን ማጥፋታቸን ፖሊስ አስታውቋል ። በመኪና ውስጥ በነርሱ የተገደለችው ሴት ፖሊስ ሽጉጥ ሲገኝ የዚያኑ ዕለት ስቪካው በተባለው ከተማ ውስጥ ሟቾቹ

Beate Zschäpe ከተባለችው አሁን በቁጥጥር ሥር ከምትገኘው የቡድኑ አባል ጋር በሌላ ስም ተከራይተው ይኖሩበት የነበረው ቤታቸው በእሳት ጋይቷል ። ራሷን ለፖሊስ አሳልፋ የሰጠችው Zschäpe ቤቱን በማቃጠልተጠርጥራለች ።

ነፍሰ ገዳዮቹ የውጭ ተወላጆችን ለመግደል የተጠቀሙበት ድምፅ አልባ ሽጉጥና ሌሎችም በርካታ ሽጉጦች በተቃጠለው ቤት ውስጥ ከተገኙ በኋላ ነበር የ 9ኙ የውጭ ዜጎች ግድያም በነርሱ ሳይፈፀም እንዳልቀረ ይፋ የተደረገው ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ በዋነኛዋ ተጠርጣሪና በሌሎችም ተባባሪዎች ላይ ምርመራው ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ፣ በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደረጃም ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚሽን ተቋቁሞ ሥራውን እያካሄደ ነው ። በነፍሰ ግድያ በዋነኛነት ከሚጠረጠሩት በአንዷ Beate Zschäpe እንዲሁምበተለያየ መንገድ ቀኝ ፅንፈኞቹን ረድተዋል በተባሉ ሰዎች ላይ ከ 12 ቀናት በኋላ የፍርድ ሂደት ይጀመራል ።

የፍርዱ ሂደት ሊጀመር የታሰበው ያለፈው ሳምንት ረቡዕ ነበር ። ሆኖም ዳኞች ለጋዜጠኞች እንዲያዝ የፈቀዱት ቦታ ለውጭ ዜጎች ባለመዳረሱ ውዝግብ አስከትሎ ቀኑ በሳምንታት እንዲገፋ ተደርጓል ፣ በተለይ አንድ የቱርክ ጋዜጠኛ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ያስገባው ክስ ተቀባይነት አግኝቶ አሁን ለቱርክ ጋዜጠኞች 4 መቀመጫዎች ተይዘውላቸዋል ። ለግሪክ ፕሬስ አንድ እንዲሁም ለፐርሽያ ቋንቋም እንዲሁ አንድ ቦታ ተመድቧል ። ሙኒክ ውስጥ በሚገኘው የአውራጃ ፍርድ ቤት በጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 6 2013 ከሚጀመረው ችሎት እነ ጋሜዝ እውነትና ፍትህ ይጠብቃሉ ። ዶክተር ለማም ከችሎቱ የሚጠብቁትን ተናግረዋል ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic